የ«ታላቊ የሕዳሴ ግድብ» የሦስትዮሽ ድርድር
ቅዳሜ፣ ሰኔ 6 2012
የ«ታላቊ የሕዳሴ ግድብ» የሦስትዮሽ ንግግር በኢትዮጵያ፤ ግብፅ እና ሱዳን መካከል ዳግም መከናወን ጀምሯል። ውይይቱን በተመለከተ የኢትዮጵያ የውኃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚንሥትር ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ፦ድርድሩ ከኹለት ቀናት በኋላ ቅዳሜ ዳግም እንደሚጀምር ገልጦ ነበር። በመግለጫውም ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ ኹለቱ ሃገራትን ማለትም ሱዳን እና ግብፅን የመጎዳት ዓላማ እንደሌላት ጠቅሷል።
ይልቊንም ኢትዮጵያ የሦስቱንም ሃገራት ሕዝቦች የጋራ ጥቅም የሚያስጠብቅ ብቸኛው መንገድ የቴክኒካል ድርድሩ ላይ ነው ያለው ብላለች። ሦስቱም ሃገራት በጥሩ መተማመን እና ቊርጠኝነት የጋር ጥቅም የሚያስገኝ ውጤት ላይ ለመድረስ የመሥራቱን አስፈላጊነት ኢትዮጵያ ያሰመረችበት መኾኑንም ጠቅሷል። ግድቡ ውኃ መሞላት የሚጀምርበትን የመጀመሪያ ጊዜ እና ዓመታዊ አለቃቅን በተመለከተ ታዛቢዎች በተገኙበት የተከናወነውን የቪዲዮ ጉባኤ ድርድር ሐሙስ ዕለት የመራችው ኢትዮጵያ ናት። የቅዳሜውን የቪዲዮ ጉባኤ ሱዳን እንደምትመራው ተገልጧል።
በድርድሩ ከሦስቱ ሃገራት የውኃ የመስኖ እና ኢነርጂ ሚንስትሮች በተጨማሪ ቀደም ሲል ታዛቢ ተብለው ወደ አደራዳሪነት ሚናቸውን ከቀየሩት ዩናይትድ ስቴትስ እና የዓለም ባንክ መካከል ዩናይትድ ስቴትስ ዳግም ተገኝታለች። በተጨማሪም ደቡብ አፍሪቃ እና የአውሮጳ ኅብረት ታዛቢዎች ነበሩ። ኢትዮጵያ ሐሙስ ዕለት ዳግም የጀመረው ንግግር ላይ የውጭ አካላት ሚና የተገደበ እንዲኾን ትፈልጋለች ሲል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። በባለፈው የዋሽንግተን ንግግር የዩናይትድ ስቴትስ ጣልቃ ገብነት እና ጫና ኢትዮጵያ በመጨረሻው ሰዓት ከድርድሩ እንድትቀር ማድረጉም ይታወሳል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ