1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የታራሚዎች አያያዝ ዘገባ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 11 2015

ዶ/ር ሚዛኔ በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በሲዳማ ክልሎች ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር በዋሉ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት አለመቅረብ፣ በፖሊስ ጣቢያዎች የምግብ፣ የፍራሽ እና የአልባሳት አቅርቦት አለመኖር፣ማደሪያዎች በእስረኞች የተጨናነቁ መሆናቸው፣ በቂ ምግብ አለማቅረቡና የንጽህና ጉድለት ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል ናቸው ብሏል ኮሚሽኑ።

Äthiopien Menschenrechtskommission
ምስል Solomon Muche/DW

«የታራሚዎች በተጨናነቀ ሁኔታ መያዝ አሳሳቢ ነው»«የታራሚዎች በተጨናነቀ ሁኔታ መያዝ አሳሳቢ ነው»የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ውስጥ ለማረሚያ ተቋማት የሚመደብ በጀት ዝቅተኛ መሆን እና ወጥ የሆነ የታራሚዎች አያያዝ እና አጠባበቅ ሕግ አለመኖር ዋነኛ ችግሮች ናቸው ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ለዚህ ማሳያ በሲዳማ ክልል ይርጋለም ማረሚያ ተቋም ከማደሪያ ክፍል ጥበት፣ ከንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ንጽህና ጉድለት ሰበብ በተከሰቱ በሽታዎች ቁጥራቸው ያልተገለጸ ታራሚዎች ለከፍተኛ ሕመም እና ሞት መዳረጋቸውን ገልጿል። ባለፈው ሳምንት የተጠቃለለ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ የምርመራ ዘገባውን ይፋ ያደረገው ኢሰመኮ በጥቅሉ ኢትዮጵያ ውስጥ "በሰብዓዊ መብት አያያዝ ረገድ ወደኋላ የመንሸራተት ሥጋት እና አዝማሚያ ታይቷል" ብሏል።ሆኖም በፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች ላይ ከትግራይ ክልል በስተቀር ባደረገው ክትትል ትርጉም ያላቸው የአያያዝ መሻሻሎች የታየባቸው የመብት ጉዳዮች የመኖራቸውን ያህል አሳሳቢነታቸው ትኩረት የሚሹ መሆኑንም አስታውቋል። 
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ በዓመቱ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች የማረሚያ ቤቶች እና የፖሊስ ጣቢያዎች ነባራዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ምርመራ መደረጉን ገልፀዋል። 
ለማረሚያ ተቋማት የሚመደብ በጀት በቂ አለመሆን፣ ወጥ የሆነ የታራሚዎች አያያዝ እና አጠባበቅ ሕግ አለመኖር ዋና ዋና የችግር ምንጭ የሆኑ ጉዳዮች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ምስል Solomon Muche/DW

በተለይ በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በሲዳማ ክልሎች በሚገኙ 75 ፖሊስ ጣቢያዎች እና 21 ማረሚያ ቤቶች በተደረገ ክትትል ብዙ አወንታዊ ለውጦች መኖራቸውን የገለፁት ኃላፊው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር በዋሉ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት አለመቅረብ፣ በፖሊስ ጣቢያዎች የምግብ፣ የፍራሽ እና የአልባሳት አቅርቦት አለመኖር፣ የተጠርጣሪዎች የማደሪያ ክፍሎች በእስረኞች የተጨናነቁ፣ በቂ አየር እና ብርሃን የማያስገቡ መሆናቸው፣ በማረሚያ ቤቶች በቂ ምግብ ለማቅረብ አለመቻሉ፣ ከፍተኛ የታራሚ ክፍሎች ጥበትና የንጽሕና ጉድለቶች መኖራቸው በቂ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም በሀገሪቱ ወጥ የሆነ የይቅርታ አሰጣጥ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩን እና በይርጋለም ማረሚያ ተቋም ከማደሪያ ክፍል ጥበት፣ ከንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ንፅህና ጉድለት መነሻ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተከሰቱ በሽታዎች ምን ያህል እንደሆኑ ባይገልፁም ታራሚዎች ለከፍተኛ ህመም እና ሞት መዳረጋቸው ተጠቁሟል፡፡ ባለፈው ሳምንት የተጠቃለለ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት ምርመራ ዘገባውን ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ያደረገው ኢሰመኮ ኢትዮጵያ ውስጥ "በሰብዓዊ መብት አያያዝ ረገድ ወደኋላ የመንሸራተት ሥጋት እና አዝማሚያ ታይቷል" ሲል አመልክቶ ነበር። ያም ሆኖ ግን በማረሚያ ቤቶች አያያዝ መሻሻል እንደተስተዋለ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ መግለፃቸው ይታወሳል። 
ኮሚሽኑ ከሰኔ 2014 እስከ ሰኔ 2015 ዓ. ም ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በዳሰሰበት ዘገባው "በሀገሪቱ ከዚህ በፊት ያልታዩ ይያላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተስተውለዋል፣ መጠናቸው እና አሳሳቢነታቸውም ሰፍቷል" ብሎ ነበር። ይህን መሳይ ችግሮች በተለይ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ጎልተው መታየታቸውንም አስቷውቆ ነበር።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ 
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW