የታኅሣሥ 10 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 10 2015የዛሬው የስፖርት ጥንቅራችን ዋነኛ ትኩረት አርጀንቲና ፈረንሳይን ትናንት በመለያ ምት 4 ለ2 ድል ያደረገችበት የካታር የዓለም እግር ኳስ ጨዋታ አስደማሚ የመዝጊያ ስነ ሥርዓት ነው። እጅግ ደማቅ በሆነ ሁኔታ ትናንት የተጠናቀቀው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያ በፍጻሜ ተፎካካሪዎቹ አርጀንቲና እና ፈረንሳይ መካከል በተለይ ከመደበኛው ጨዋታ አጋማሽ በኋላ እጅግ ብርቱ ፉክክር የታየበት ነበር። አዘጋጇ ካታር ዘንድሮ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን ማሰናዳቷ ምን አይነት ዐበይት ጉዳዮችን ጥሎ አልፏል?
የኳስ ጠቢባኑ እነ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶናን፣ ሊዮኔል ሜሲ እና ሌሎችን አፍርታ ዓለምን ያዝናናችው አርጀንቲና የመጀመሪያ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን መጨበጥ የቻለችው እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ1978 ነበር። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1986 ደግሞ ሁለተኛዋን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ድል ተቀዳጅታለች። ዘንድሮ የ35 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲን በካታር የእግር ኳስ ሜዳዎች ከፊት መስመር ያሰለፈችው አርጀንቲና የዓለም እግር ኳስ ወርቃማ ዋንጫውን ለማንሳት 36 ዓመታትን መጠበቅ ተገዳ ነበር። የትናንት ምሽቱን ጨምሮ የደቡብ አሜሪካዊቷ አርጀንቲና ሦስት የዓለም እግር ኳስ ዋንጫዎችን በድል ወደ ቦነስ አይረስ መውሰድ ችላለች።
በትናንቱ የፍጻሜ ግጥሚያ አርጀንቲና አሸነፈች ሲባል የፈረንሳዩ ፈጣን አጥቂ ኪሊያን እምባፔ ድንቅ ግቦችን እያስቆጠረ አቻ ሲወጡ የበርካቶች ልብ ተሰቅሎ ነበር። በፓሪስ ሳንጃርሞ ቡድን ከኬሊያን እምባፔ ጋር በአንድ ቡድን በጋራ የሚጫወተው ሊዮኔል ሜሲ አርጀንቲናን ለድል አበቃ ሲባል ደግሞ መልሶ ያው እምባፔ በሉሳይል ስታዲዬም ሲምነሸነሽ አምሽቷል።
የሊዮኔል ሜሲ አርጀንቲና የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ሆነች
90 ደቂቃ መደበኛ የጨዋታ ክፍለጊዜውም ሆነ ጭማሪው የተጠናቀቀው ሦስት እኩል ነበር። ወደ መለያ ምት ሲገቡ ግን ወትሮም የኳስ ቀበኛ የነበረው የአርጀንቲናው ግብ ጠባቂ ኤሚሊዮ ማርቲኔዝ ከፈረንሳዩ ሁጎ ሉሪ የተሻለ ብቃቱን ዐሳይቷል። አርጀንቲናም በመለያ ምቱ 4 ለ2 ለድል እንድትበቃ ከፍተኛውን አስተዋጽዖ አበርክቷል። አንድ ኳስ አጨናግፎ አንደኛዋ መሬት ለመሬት በቋሚው ጥግ ከግቡ ውጪ እንድትመታ ማስደረግ ችሏል። በዚህ ብቃቱም የዓለም ዋንጫ ምርጥ ግብ ጠባቂ በሚል የአዲዳስ የወርቅ ጓንት ተሸላሚ ሆኗል።
ለፈረንሳይ የፍጹም ቅጣት ምቱን ጨምሮ አራቱንም ግቦች ያስቆጠረው ኬሊያን እምባፔ የአዲዳስ የወርቅ ጫማን እንዲሁም የብር ኳስ ሲሸለም፤ የዕለቱ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ደግሞ የወርቅ ኳሷን በእጁ አስገብቷል። የነሐስ ኳስ ተሸላሚው ሞሮኮን አሸንፋ ሦስተኛ የወጣው ክሮሺያ አጥቂ የ37 ዓመቱ ሉካ ሞድሪች ነው። ሉካ ሞድሪች ያለፈው የዓለም ዋንጫ የወርቅ ጫማ ተሸላሚ ነበር።
የቃለ መጠይቁ ሙሉ ይዘት በድምጽ ከታች ይገኛል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ