የታኅሣሥ 19 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 19 2013ሊዮኔል ሜሲ ከባርሴሎና ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሊያቀና እንደሚችል እየተነገረ ነው። ሊቨርፑል ወራጅ ቃጣና ታች ከሚገኝ ቡድን ጋር ተጋጥሞ ማሸነፍ ተስኖታል፤ ሆኖም የፕሬሚየር ሊጉን እየመራ ነው። በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ አራተኛ ዙር ግጥሚያም መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ቀንቶታል። የኢትዮጵያ ቡና ዛሬ ባደረገው ግጥሚያ ሽንፈት ገጥሞታል። በሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ያለፉት 20 ዓመታት ታሪክ 20 ጊዜ ባለድል የነበረው ታዋቂው ተጨዋች ሮጄር ፌዴሬር በጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ አይሳተፍም። በኮሮና ተሐዋሲ ምክንያት ይካኼድ አይካኼድ ርግጠኛ መሆን ያልተቻለበት የቶኪዮ ኦሎምፒክ ከወዲሁ ዝግጅት ተጀምሯል።
በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ ሰበታ ከተማን 4 ለ2 በኾነ ውጤት አሸንፏል። በጌታነህ ከበደ ቀዳሚ ግብ 37ኛ ደቂቃ ላይ መመራት የጀመረው ሰበታ ከተማ 50ኛው ደቂቃ ላይ እስራኤል እሸቱ ባስቆጠራት ግብ አቻ ወጥቶ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች በተከታታይ ባስቆጠሯቸው ግቦች 4 ለ1 ሊሸነፍ የነበረው ሰበታ ከተማ መደበኛ 90 ደቂቃው ተጠናቆ በጭማሪ ሰአት ላይ በተገኘ ፍጹም ቅጣት ምት ነበር ሁለተኛዋን ግብ ማስቆጠር የቻለው። ለቅዱስ ጊዮርጊስ፦ አቤል ያለው፣ ጋዲሳ መብራቱ እና ጌታነህ ከበደ በተከታታይ አስቆጥረዋል። ጌታነህ 65ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ግብ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ በመሆን ጨዋታው ተጠናቋል።
ዛሬ ከሰአት ላይ የኢትዮጵያ ቡና እና ሐዋሳ ከተማ ባከናወኑት ግጥሚያ ደግሞ፦ ሐዋሳ ከነማ በብሩክ በየነ ብቸኛ ግብ አሸንፏል። በዚህም መሰረት የፕሬሚየር ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ9 ነጥብ ይመራል። ሀዲያ ሆሳዕና በተመሳሳይ 9 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ የደረጃ ሰንጠረዡን የመምራት ዕድል የነበረው ኢትዮጵያ ቡና በ7 ነጥቡ እና የሦስተኛ ደረጃው ላይ ተወስኗል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሲዳማ ቡና በ0 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ይገኛል።
ቡንደስሊጋ
ቡንደስሊጋው ለገና ሰሞን እና አዲስ ዓመት ረፍት ላይ ነው። የቡንደስሊጋውን በ30 ነጥብ የሚመራው ባየር ሙይንሽን በጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት ቀዳሚ እሁድ ማይንትስን ይገጥማል። 28 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ በሁለተኛነት የሚገኘው ባየር ሌቨርኩሰን በአዲስ ዓመት ዋዜማ የፊታችን ቅዳሜ ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር ይፋለማል። 17 ነጥብ ያለው አይንትራኅት ፍራንክፉርት 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በተመሳሳይ 28 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ የሦስተኛ ደረጃን የተቆናጠጠው ላይፕትሲሽ ደግሞ ቅዳሜ ማታ ሽቱትጋርትን ይገጥማል። የፊታችን እሁድ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከቮልፍስቡርግ ጋር የሚያደርጉት ግጥሚያም ይጠበቃል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በቮልፍስቡርግ በ2 ነጥብ ይበለጣል፤ 22 ነጥብ ይዞ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
4 ነጥብ ብቻ ይዞ በ18ኛ ደረጃ የቡንደስሊጋው የመጨረሻ ግርጌ ላይ የሚገኘው ሻልከ ቅዳሜ ዕለት ሔርታ ቤርሊንን ይገጥማል። አዲሱ አሰልጣኝ ክርስቲያን ግሮስ ሊሰናበት ጫፍ ላይ የደረሰው ሻልከን በቀጣይ የውድድር ዘመን በቡንደስሊጋው የማቆየት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። የ66 ዓመቱ የሻልከ አዲስ አሰልጣኝ ቡድኑን ከመውረድ ለመታደግ ከምንም በላይ ከተጨዋቾች ጋር መነጋገርን እንደሚያስቀድሙ ዛሬ ዐሳውቀዋል።
የባየር ሙይንሽን አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ «ኪከር» በተሰኘው መጽሄት «የዓመቱ ምርጥ ሰው» ተብለው ተወደሱ። ሐንሲ ፍሊክ ቡድናቸው ባየር ሙይንሽን የቡንደስሊጋውን፣ የሻምፒዮንስ ሊጉን እና የሱፐር ካፑን ዋንጫዎች እንዲወስድ በማስቻላቸው ነው የዓመቱ ምርጥ የተሰኙት። አምና በዚሁ መጽሄት የዓመቱ ምርጥ ሰው የተባሉት የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ነበሩ።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዡን በ32 ነጥብ የሚመራው ሊቨርፑል የወራጅ ቃጣና ውስጥ ከሚገኘው ዌስት ብሮሚች ጋር ትናንት ባደረገው ግጥሚያ በአስደናቂ ሁኔታ አንድ እኩል ተለያየ። በጠንካራ መከላከል እና መልሶ ማጥቃት ስልት ወደሜዳ የገቡት ዌስት ብሮሚቾች ከሊቨርፑል ጋር ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት የቆረጡ ይመስሉ ነበር። አብዛኛውን ጊዜም ተጨዋቾቻቸው በአጠቃላይ ወደ ግብ ግብ ክልላቸው በማፈግፈግ ሲከላከሉ ቆይተዋል። ዌስት ብሮሚች እስካሁን ባደረጋቸው 15 ግጥሚያዎች ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። የሊቨርፑልን ጨምሮ አምስት ግጥሚያዎችን አቻ ወጥቷል፤ በዘጠኙ ተሸንፏል። 8 ነጥብ ብቻ ይዞ 19ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከበታቹ የሚገኘው ባለ 2 ነጥቡ ሼፊልድ ዩናይትድ ብቻ ነው።
ሊቨርፑል በአንጻሩ፦ እስካሁን ባደረጋቸው ግጥሚያዎች አንድ ጊዜ ተሸንፎ፤ አምስት ጊዜ አቻ ወጥቷል፣ 9ኙን አሸንፏል። እናም በዚህ ሁኔታ ከዌስት ብሮሚች ጋር አቻ መውጣቱ በርካቶችን አስገርሟል። በእርግጥ ፊርሚኖ 90ኛው ደቂቃ ላይ ከመቀየሩ በፊት በግንባሩ ገጭቶ ከመሬታ ጋር በማላተም ወደ ግብ የላካትን ኳስ ግብ ጠባቂው ከመረብ እንዳታርፍ የተከላከለው እንደምንም በጣቶቹ ጫፎች ነበር።
ዛሬ ማታ ቸልሲ ከአስቶን ቪላ ጋር የሚያደርገው ግጥሚያ በደረጃ ሰንጠረዡ የሦስተኛ ቦታን ከላይስተር ሲቲ ለመቀማት የሚያስችል ነው። በተለይ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት አስቶን ቪላ እንደ ቸልሲ 25 ነጥብ ይዞ 7ኛ ደረጃ ላይ በመገኘቱ ዕድሉ ሰፊ ነው። 15 ጨዋታዎችን ያከናወነው ላይስተር ሲቲ 28 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኤቨርተን በ29 ነጥብ ሁለተኛ ነው። ማንቸስተር ሲቲ እና ኤቨርተንም ከእነ ቸልሲ ቀጥለው ዛሬ ማታ ይጋጠማሉ። ኤቨርተን 16ኛ ጨዋታውን ሲያከናውን ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ተስተካካይ 15ኛ ጨዋታውን ነው ዛሬ ማታ የሚያከናውነው።
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች፦ በሚኬል አርቴታ የሚሰለጥነው አርሰናል ቸልሲ ላይ ድል ተቀዳጅቷል። ከአሌክሳንደር ላካዜቴ እና ግራኒ ሻቃ ቀጥሎ ሦስተኛዋን ግብ በ56ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው የ19 ዓመቱ ታዳጊ ቡካዮ ሳካ የዕለቱ ምርጥ ተጨዋች ኾኖ አምሽቷል። ቸልሲ 91ኛው ደቂቃ ላይ ያገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ጆርጂኒዮ እንዲመታው ቢደረግም ጀርመናዊው ግብ ጠባቂ ቤርንድ ሬኖ ግን አጨናግፎበታል።
በቅዳሜው ግጥሚያ አርሰናል ቸልሲን 3 ለ1 በሆነ ሰፋ ያለ ውጤት ነው ያሸነፈው። ኾኖም በደርቢው ፉክክር ድል ሲያደርግ ከስምንት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ነው። አርሰናል ከዚህ ቀደም ያሸነፈው ጥቅምት 22 ቀን ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ነበር። በወቅቱ አርሰናል በፒዬር ኤመሪክ ኦውባማያንግ 69ኛ ደቂቃ ላይ የተቆጠረች ብቸኛ ግብ 1 ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል። ከዚያን ጊዜ በኋላ አርሰናል ድል ርቆት ቆይቷል። በለንደን ደርቢ ቅዳሜ ዕለት ድል የቀናው አርሰናል በአሁኑ ወቅት በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ከሚገኘው ሼፊልድ ዩናይትድ በ15 ነጥብ ልዩነት 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ዛሬ ማታ ከአይበር ጋር ይጋጠማል። ባርሴሎና 24 ነጥብ ይዞ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከበላዩ ቪላሪያል፣ ሪያል ሶሲዬዳድ፣ ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ከ4ኛ እስከ 1ኛ ተደርድረዋል። የባርሴሎናው የረዥም ዘመን አጥቂ አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ በአንድ ወቅት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አቅንቶ እዚያ ለሚገኝ ቡድን የመጫወት ተስፋ እንዳለው ገልጧል። የ33 ዓመቱ አርጀንቲናዊ አጥቂ ትናንት በቴሌቪዥን ቀርቦ ባደረገው ቃለ መጠይቅ፦ በእርግጠኝነት መናገር ባይችልም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መኖር ፍላጎቱ እንደሆነ ግን አልሸሸገም። ሊዮኔል ሜሲ ከ13 ዓመቱ አንስቶ ከተጫወተበት የልጅነት ቡድኑ ራሱን ለማሰናበት ተዘጋጅቶ እንደነበር ባሳወቀበት ወቅት ከፍተኛ ወቀሳ ቀርቦበት ነበር።
ቀጣዩ የኦሎምፒክ ስፖርት ጃፓን ቶክዮ ውስጥ በጎርጎሪዮሱ 2021 ለመካኼዱ ርግጠኛ ባይኮንም ቶኪዮ ከወዲሁ ዝግጅት መጀመሯ ተገልጧል። በኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት የተነሳ በቶኪዮ ሊካኼዱ የነበሩት የኦሎምፒክ እና ፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ከታቀደላቸው ጊዜ ውጪ እንዲሸጋሸጉ ተደርጓል። ሂሮሺ ሳካዚ ውስጥ ለኦሎምፒክ ጨዋታዎች ዝግጅት የፈጠራ ሥራዎችን የሚከውኑ ድርጅቶች ሥራቸውን ጀምረዋል። በከተማዪቱ ሰባት አባላት ያሉት የፈጠራ ሥራዊች ቡድን መቋቋሙም ተገልጧል።
የሜዳ ቴኒስ
በአውስትራሊያ የሚዳ ቴኒስ የፍጻሜ ግጥሚያ ሮጀር ፌዴሬር እንደማይሳተፍ ተገለጠ። የስድስት ጊዜያት ባለድሉ ዘንድሮ በአውስትራሊያ የፍጻሜ ውድድር እንደማይሳተፍ መነገሩ የሜዳ ቴኒስ አፍቃሪያንን ቅር አሰኝቷል። የ39 ዓመቱ ሮጄር ፌዴሬር በዓለም የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ለ20 ጊዜያት ድል ተቀዳጅቷል። ሮጄር ፌዴሬር ካለፈው ጥር ወር አንስቶ ባከናወናቸው የቀዶ ጥገናዎች የተነሳ ነው በቀጣዩ ውድድር መሳተፍ ያልቻለው። ምናልባት ግን የካቲት ወር ላይ ዘግይቶም ቢሆን በአውስትራሊያ የሜልቦርን ውድድር ለመሳተፍ ተስፋ ሰንቋል። ለ21 ዓመታት ያህል በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ ያለማቋረጥ የተሳተፈው ሮጄር ፌዴሬር ከውድድር ውጪ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ