የታኅሣሥ 24 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 24 2015ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ የኳስ ንጉሡ ፔሌ ስንብት ዛሬ እየተካሄደ ነው። በኅመም ምክንያት ባለፈው ሐሙስ ከዚህ ዓለም የተለየው የ82 ዓመቱ ብራዚሊያዊ የኳስ ንጉሥን አድናቂዎቹ እንዲሰናበቱ አስክሬኑን የያዘው ሳጥን ሳንቶስ ስታዲየም ደርሷል። ከዓለማችን ድንቅ ተጨዋቾች አንዱ የሆነው ፖርቹጋላዊ አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለሳዑዲ ዓረቢያው አል ናስር መፈረሙ ቡድኑን በማኅበራዊ መገናኛ አውታር እጅግ ዝነኛ አድርጎታል። በኢንስታግራም ብቻ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች የነበሩት አል ናስር ቡድን ሮናልዶ ከፈረመ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከ6 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ማፍራት ችሏል። ቸልሲ ከሜዳው ውጪ ማሸነፍ አልቻለም። ሊቨርፑል 5ኛ ደረጃውን ከቶትንሀም ሆስፐርስ ለመረከብ ዛሬ ብሬንትፎርድን ማሸነፍ ይጠበቅበታል።ማንቸስተር ሲቲ ነጥብ ሲጥል የመሪው አርሰናል ግስጋሴን ግን የሚገታ አልተገኘም። የአትሌቲክስ እና ሌሎች የስፖርት መረጃዎንም አካተናል።
አትሌቲክስ፦
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት ዋዜማ ስፔን ባርሴሎና ውስጥ በተደረገ የአምስት ሺህ ሜትር የሩጫ ፉክክር በወንዶችም በሴቶችም ድል ቀንቷቸዋል። በሴቶች ፉክክር አትሌት እጅጋየሁ ታየ 14:21 በመሮጥ ለድል ስትበቃ በወንዶች ውድድርም ኢትዮጵያዊው አትሌት አዲሱ ግርማ በ13:25 የአንደኛነት ድል ተቀዳጅቷል። በሴቶች ፉክክር ጀርመናዊቷ ኮንስታንትሴ ክሎስተርሃልፈን ከ31 ሰከንድ በኋላ በማጠናቀቅ የሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። የኖርዌዩዋ ካሮሊን ግሮብዳል በበኩሏ ኬኒያዊቷ ማሪያም ቼቤትን በ30 ሰከንድ ቀድማ ሦስተኛ ደረጃን መያዝ ችላለች። የገባችበት ሰአትም 15:06 ነው። ማሪያም ቼቤት 4ኛ ደረጃን ይዛለች። ለስፔን የሚሮጠው ኤሊያስ ፊፋ እና የስዊትዘርላንዱ አትሌት ዮናስ ራኤስ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን አግኝተዋል።
በስፔን ማድሪድ የ10,000 ሜትር የሩጫ ፉክክር ደግሞ ኡጋንዳዊው አትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጊ ድል ቀንቶታል። ጆሹዋ ውድድሩን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ 27:09 ነው። ስፔንያውያኑ ሞሐመድካታሪ እና ጄሱስ ራሞስ ተከታትለው ሁለተኛ እና ሦስተና ደረጃ አግኝተዋል። በሴቶች ተመሳሳይ ፉክክርም ኡጋንዳዊቷ ፕሪስካ ቼሳንግ ለድል በቅታለች። ፕሪስካ 30:19ሮጣ ባሸነፈችበት ፉክክር የቡሩንዲዋ አትሌት ፍራንሲኔ ኒዮንሳባ ሁለተኛ፤ ኬኒያዊቷ ቤያትሪስ ቼፕኮኤች ሦስተኛ ወጥተዋል። የ4ኛ ደረጃውን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ማኅሌት ሙሉጌታ ይዛለች።
በሌላ የአትሌቲክስ ዜና 40ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ውድድር ትናንት መጠናቀቁ ተገልጧል። ሱሉልታ ከተማ ውስጥ የተከናወነው ውድድር ላይ በድብልቅ ሪሌ፤ በ6 ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶች፤ በ8 እና 10 ኪሜ አዋቂ ሴቶች እና ወንዶች የምድብ ፉክክሮች ተከናውነዋል። በውድድሩ ከ50 ዓመት በላይ አንጋፋ አትሌቶችም ተካፋይ ነበሩ።
እግር ኳስ
የፔሌ ስንብት፦ በሳንቶስ ስታዲየም
የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን ለሦስት ጊዜያት በመውሰድ ብቸኛ ለሆነው የኳስ ንጉሥ ኤድሰን አራንቴስ ናሲሜንቶ፤ በይበልጥ በሚታወቅበት ስሙ ፔሌ ደጋፊዎች የመጨረሻ ስንብት እያደረጉ ነው። ፔሌ በልጅነት ዘመኑ ለረዥም ጊዜ በተጫወተበት የትውልድ ስፍራው ሳንቶስ ውስጥ በሚገኘው የቪላ ቤልሚሮ ስታዲየም መሀል አስክሬኑን የያዘው ሳጥን ተቀምጧል። አድናቂ ደጋፊዎቹም እስከ ነገ ለ24 ሰአታት ወደ ስታዲየሙ እየሄዱ ከአስክሬኑ 5 ሜትር ርቀት በመጠጋት ስንብት እንዲያደርጉ ተፈቅዷል።
በነገው ዕለት እጅግ በርካታ ሰዎች ይታደሙበታል ተብሎ የሚጠበቀው የፔሌ ቀብር ሥርዓት በከተማዪቱ ደቡብ ምሥራቅ ውስጥ ይከናወናል። በቀብር ሥርዓቱ መርኃ ግብር መሰረትም አስክሬኑ አሁንም ድረስ በሕይወት በሚገኙት የ100 ዓመት ባለጸጋዋ የፔሌ እናት ሴሌስቴ ናሲሜንቶ ቤት በኩልም ያልፋል። ከዚያም በቤተሰቡ እና ወዳጆቹ ደግሞ በግል ቀብሩ ይፈጸማል ተብሏል። ከዚያ በፊት ግን በርካቶች ለመጨረሻ ስንብታቸው ወደ ስታዲየሙ እየጎረፉ ነው። የብራዚልሉ ርእሰ ብሔር ሉዊዝ ኢናቺዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ለፔሌ ስንብት ከተጠበቁት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ናቸው። የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፊፋ (FIFA) ፕሬዚደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖም ወደ ብራዚል ሳንቶስ አቅንተዋል። የፔሌን አስደናቂነት የቆሮንቶስ እና ፍላሜንጎ ቡድን የቀድሞ ስፔናዊ ተጨዋች ሆዜ ኡፋርቴ፤ የስፔን የስፖርት ጋዜጠኛ ሆዜ ማሪያ ሬሊያኞ እንዲሁም ቀደም ሲል አብረውት ከተጫወቱ መካከል የ70ዎቹ የስፔን ምርጥ ተጨዋች ዣቪዬር ኢሩሬታ የኳስ ንጉሡን እንዲህ ይዘክሩታል። የ81 ዓመቱ ሆዜ ኡፋርቴ።
«ለቆሮንቶስ እና ፍላሚንጎ ተሰልፌ ከፔሌ ጋር ብዙ ጊዜ ተጋጥሜያለሁ። ያኔም ጥሩ ወዳጅነት ስለነበረን እንገናኝ ነበር።»
ሆዜ ኡፋርቴ ከበርካታ ዐሥርተ ዓመታት በፊት የነበረው የፔሌ ሁኔታ ዛሬም ከዐይነ ኅሊናቸው እንደማይጠፋ ነው የሚናገሩት።
«ፔሌ» የሚለውን ስም የኳስ ንጉሡ እንዴት አገኘ?
«አስደናቂ ነበር፤ በሁለት እግሮቹ ትላለህ በጭንቅላቱ በመጫወት የተሟላ ነበር። በአጠቃላይ አንዳች እንከን አይወጣለትም ነበር። እጅግ አስደናቂ ምርጥ ተጨዋች።»
ፔሌ እንዲያ በእግር ኳስ ብቃቱ ገናና የነበረ ቢሆንም በችሎታው ግን አይታበይም ነበር ይላሉ እኚሁ የጥንት ወዳጁ ሆዜ።
«በምንም ነገር ልኩራራ ሲል ዐይታይም። ሰው ቀናብ ሎ የማያይ አብረውት ለሚጫወቱ መልካም ጓደኛ ነበር።»
እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1958፤ 1962 እና 1970 ዓ.ም የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን ለሦስት ጊዜያት በመውሰድ ብቸኛው የኳስ ንጉሥን የሚያውቁት ሁሉ አወድሰው አይጠግቡም። ሌላኛው የፔሌ አድናቂ የስፖርት ጋዜጠኛው ሆዜ ሬሊያኞ።
«በጭንቅላት ጨዋታ የሚደርስበት አልነበረም፤ እጅግ ጨዋታ ዐዋቂ ነው። በርካታ ርእይ የነበረው፤ ነገሮችን ወዲያው በመፍጠርም የተካነ ነው። ከነዚያ ሁሉ በላይ ደግሞ ፔሌ አስደናቂ ሰውነት ነበረው። መለያውን ካወለቀ ሆዱ ላይ የተሟሉ ስምንት ቅርጾች ተደርድረው ታያለህ። ታላቅ ኃይል ነበረው።»
ስፔናዊው የ70ዎቹ ኮከብ የእግር ኳስ ተጨዋች ዣቪዬር ኢሩሬታም የፔሌ አድናቂ ናቸው፤ በተለይ የተክለ-ሰውነቱ።
«ሰውነቱ ተወው ድንቅ ነበር። ደግሞ ስማ በጣም ጠንካራ።»
ዣቪዬር በትዝታ ወደ ኋላ ለዓመታት ተመልስውም «ንጉሡን» እንዲህ ይዘክሩታል። ዓለም ላይ ምርጥ ተጨዋቾች ቢከሰቱም ፔሌ ላይ ግን የሚደርስ የለምም ይላሉ።
«እንደ ማራዶና ያሉ ሌሎች በርካታ ጥሩ ተጨዋቾች አሉ። እሱ ግን እነሱ እንደሚጠሩት ንጉሡ ነበር። አስደማሚ ተጨዋች ንጉሥ ነበር።»
አስደማሚው ንጉሥ፤ ኤድሰን አራንቴስ ናሲሜንቶ፤ ፔሌ ዘመን አይሽሬ ስሙን ተክሎ አልፏል። ፔሌ ሳኦፖሎ ውስጥ በሚገኘው አልበርት አንሽታይን ሐኪም ቤት ከካንሰር ኅመም ለመዳን ሲታገል ቆይቶ በ82 ዓመቱ ያረፈው ሐሙስ፤ ታኅሣሥ 20 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ነበር።
አጠር ያሉ ስፖርታዊ መረጃዎች
ከዓለማችን ምርጥ የእግር ኳስ ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ፖርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለሳዑዲ ዓረቢያው አል ናስር የእግር ኳስ ቡድን የመፈረሙ ዜና ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል። ሮናልዶ በአል ናስር ቡድን ቢያንስ የሁለት ዓመት ቆይታው በዓመት 200 ሚሊዮን ዶላር ይከፈለዋል ተብሏል። ከአል ናስር ቡድን ፕሬዚደንት ጋር ሆኖ ክርስቲያኖ ሮናልዶ መለያውን በማሳየት የተነሳው ፎቶም ቡድኑን እጅግ ዝነኛ አድርጎታል። ይህ ፎቶግራፍ የሚገኝበት የአል ናስር ቡድን የኢንስታግራም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገጽ ሮናልዶ ለቡድኑ መፈረሙ ከተሰማ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የተከታዮቹ ቁጥር ከ 860 000 በአንድ ጊዜ ወደ 6,2 ሚሊዮን ከፍ ብሏል። ይህ ቁጥር ሰዛሬ ጠዋት የነበረ ነው። ፎቶግራፉን በአል ናስር ቡድን የኢንስታግራም ገጽ ላይ ከ31 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መውደዳቸውን ዐሳይተዋል። ክርስቲያኖ ሮናልዶ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ ጥቂት ሰዎች መካከል ይመደባል። የ37 ዓመቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በኢንስታግራም ገጹ ብቻ 527 ሚሊዮን ተከታዮች አሉት። ለንጽጽር ሊዮኔል ሜሲ በኢንስታግራም የተከታዮቹ ብዛት 413 ሚሊዮን ነው።
በነገራችን ላይ ከምንም ተነስቶ በአንድ ሌሊት የመላው ዓለም መነጋገሪያ የሆነው የሳዑዲ ዓረቢያው አል ናስር ቡድን የምን ክርስቲያኖ ሮናልዶ ብቻ እያለ ነው። እንደ ስፔኑ የድረ ገጽ ጋዜጣ «ማርካ» ዘገባ ከሆነ አል ናስር ቡድን የሪያል ማድሪድ ተጨዋቾች ሉካ ሞድሪች እና ሠርጂዮ ራሞስንም ለማስፈረ ላይ ታች እያለ ነው። ሁለቱ በቅርቡ አል ናስርን ይቀላቀላሉም ብሏል ቡድኑ። ማየት ነው።
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ ከሜዳው ውጪ ማሸነፍ አልቻለም። ወራጅ ቀጣና 18ኛ ደረጃ ላይ ወደሚገኘው ኖቲንግሀም ፎረስት ሜዳ ትናንት አቅንቶ አንድ እኩል ተለያይቷል። ቸልሲ 25 ነጥብ ይዞ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በ28 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል 5ኛ ደረጃውን ከቶትንሀም ሆትስፐርስ ለመረከብ 10ኛ ደረጃ ላይ ያለው ብሬንትፎርድን ዛሬ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ማንቸስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት ከኤቨርተን ጋር አንድ እኩል ተለያይቶ ነጥብ ሲጥል፤ የመሪው አርሰናል ግስጋሴን የሚገታ አልተገኘም። አርሰናል ቅዳሜ ዕለት ብራይተንን በሜዳው 4 ለ2 ነው ያደባየው። በዚህም መሰረት አርሰናል ነጥቡን 43 አድርሶ ከበላይ ተኮፍሷል። ማንቸስተር ሲቲ በ36 ነጥብ ይከተላል። ኒውካስትል ዩናይትድ እና ማንቸስተር ዩናይትድ 34 እና 32 ነጥብ ይዘው 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ማንቸስተር ዩናይትድ ቅዳሜ ዕለት ዎልቨርሀምፕተንን በሜዳው አሸንፏል። 76ኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ማርኩስ ራሽፎርድ ነው።
የሜዳ ቴኒስ
የዓለማችን ቁጥር 5 ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ኖቫክ ጄኮቪች ከዚህ ቀደም ወደታገደበት አውስትራሊያ ሲገባ መልካም አቀባበል ተደረገለት። የ35 ዓመቱ ሠርቢያዊ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች በአውስትራሊያ 2022 የፍጻሜ ውድድር ወቅት ከአውስትራሊያ ተጠርዞ እንዲወጣ የተደረገው የኮቪድ-19 ደንብን ለማክበር ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነበር። አውስትራሊያ ኖቫክ ጄኮቪች ላይ የጣለችውን የ3 ዓመት ሀገር ያለመግባት የቪዛ ገደብ ያነሳችው ኅዳር ወር ላይ ነበር። ለ21 ጊዜያት የዓለም የሜዳ ቴኒስ ዋንጫን ማሸነፍ የቻለው ኖቫክ በዛሬው የአውስትራሊያ የጥምር ውድድር ከካናዳዊው የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ጋር ሽንፈት ገጥሟቸዋል። ኖቫክ ውድድሩን ያካሄደውም ከካናዳዊው ባሴክ ፖስፒስሊ ጋር በመጣመር ሲሆን፤ በኤኳዶሩ ጎንዛሎ ኤስኮባር እና የቦስኒያ ሔርዜጎቪኒያው ቶሚስላቭ ብርኪች ተሸንፈዋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ