1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታኅሣሥ 5 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 5 2013

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ትናንት የመሪነት እድሉን አጨናግፏል። የተጋጣሚው ፉልሃም ተጨዋቾች ጠንክረው ታይተው ነበር። የዓለም ከባድ ሚዛን የቡጢ ተፋላሚዎች አንቶኒ ጆሹዋ እና ታይሰን ፉሪ ያደርጉታል የተባለው ግጥሚያ በቡጢ ፍልሚያ ታሪክ ለአራቱም አይነት የከባድ ሚዛን ቀበቶዎች የሚደረግ የመጀመሪያው ውድድር ይኾናል።

Schweiz Nyon | Champions League | Auslosung Achtelfinale
ምስል UEFA/dpa/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ አንደኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ተጀምረዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ትናንት የመሪነት እድሉን አጨናግፏል። የተጋጣሚው ፉልሃም ተጨዋቾች በተክለ ሰውነትም በመከላከልም ጠንክረው ታይተው ነበር። በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከባድ ሽንፈት ገጥሞታል። አሰልጣኝ ሉቺያን ፋቭሬ ከእነ ምክትላቸው በሽቱትጋር ጉድ ከኾነው ቡድናቸው መሰናበታቸው ተሰምቷል። የዓለም ከባድ ሚዛን የቡጢ ተፋላሚዎችን በጎርጎሪዮሱ መጪው ለማጋጠም ድርድሩ ቀጥሏል። ምናልባትም በቅርቡ አንቶኒ ጆሹዋ እና ታይሰን ፉሪ ያደርጉታል የተባለው ግጥሚያ በቡጢ ፍልሚያ ታሪክ ለአራቱም አይነት የከባድ ሚዛን ቀበቶዎች የሚደረግ የመጀመሪያው ውድድር ይኾናል።

የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ

አድማጮ ዛሬ ከሰአት ኒዮን ስዊዘርላንድ ውስጥ በእጣ ስለተደለደሉት የሻምፒዮንስ ሊግ እና የአውሮጳ ሊግ ተጋጣሚዎች ዝርዝር ከማለፋችን አስቀድሞ ስለ ኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ አጠር አድርገን እናሰማችሁ። የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ 2013 ዓ.ም የእግር ኳስ ውድድር በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ጀምሯል። በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎችም፦ ትናንት አዳማ ከተማ ጅማ አባጅፋርን 4 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ኢትዮጵያ ቡና ከወልቂጤ ከተማ ጋር 2 እኩል ተለያይቶ ነጥብ ተጋርቷል።  በቅዳሜ ዕለት ግጥሚያዎች ደግሞ፦ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን በፋሲል ከነማ 1 ለ0 ተሸንፏል።

ምስል Omna Taddele/DW

የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ባለፈው ሳምንት ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ከካፍ ኮንፌዴሬሽን ግጥሚያ ቢሰናበቱም ዋነኛ ትኩረታቸው የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት እንደኾነ ተናግረው ነበር። በመጀመሪያ ጨዋታቸው ተሳክቶላቸው 3 ነጥብ መያዝ ችለዋል።  ዛሬ በተከናወኑ ግጥሚያዎች ደግሞ፦ ሀዲያ ሆሳዕና ወላይታ ድቻን 2 ለ1 ማሸነፍ ችሏል። ባህር ዳር እና ሲዳማ ቡና ዛሬ ከሰአት በኋላ ባደረጉት ግጥሚያ  በባህር ዳር የ3 ለ1 አሸናፊነት ጨዋታው ተጠናቋል።

ሻምፒዮንስ ሊግ

የሻምፒዮንስ ሊግ 16 ቡድኖች ድልድል እጣ ዛሬ ወጥቷል። ዘንድሮም እጣው የወጣው እንደባለፈው ዓመት ሁሉ በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከቀኑ ስምንት ሰአት ላይ ስዊዘርላንድ ኒዮን ከተማ የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA) ማእከል ውስጥ ነው።  በዘንድሮው የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ አራቱም የጀርመን ቡድኖች ከምድብ ውድድር አልፈው 16 ቡድኖች የደርሶ መልስ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያ ወደ ሚያደርጉበት ስብስብ መቀላቀል ችለዋል። 

ምስል UEFA/dpa/picture alliance

በዛሬው የእጣ ድልድል መሠረት ደግሞ፦ ባየር ሙይንሽን ከጣሊያኑ ላትሲዮ፤ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ከእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ እንዲሁም ላይፕትሲሽ የባለፈውን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ካሸነፈው ሌላኛው የእንግሊዝ ቡድን ሊቨርፑል ጋር ይጋጠማል። ከእያንዳንዱ ምድብ አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡ ቡድኖች ናቸው ወደ 16ቱ ስብስብ መግባት የቻሉት። ባየርሙይንሽን እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከእየ ምድባቸው አንደኛ ኾነው ማለፍ ችለዋል።  

የቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ አሰልጣኝ ማርኮ ሮስ የጀርመናዊው አሰልጣኝ የዬርገን ክሎፕ ሊቨርፑል እንዲደርሳቸው ተመኝተው ነበር። የዬርገን ክሎፕ አድናቂ የኾኑት ወጣቱ የላይፕትሲሽ አሰልጣኝ ዩሊያን ናገልስማን ባይመኙም ሊቨርፑል ደርሷቸዋል።  ቦሩስያ ዶርትሙንድ የስፔኑ ሴቪያን ይገጥማል። ቀሪዎቹ የስፔን ቡድኖች፦ ሪያል ማድሪድ ከጣሊያኑ አታላንታ ቤርጋሞ፤ ባርሴሎና ከፈረንሳዩ ፓሪ ሳን ጃርማ እንዲሁም አትሌቲኮ ማድሪድ ከእንግሊዙ ቸልሲ ጋር ይፋለማሉ። የፖርቹጋሉ ፖርቶ የጣሊያኑ ጁቬንቱስ ይጠብቀዋል።

የአውሮጳ ሊግ

በአውሮጳ ሊግ 32 ቡድኖች የእጣ ድልድል መሠረት ከሦስቱ የጀርመን ቡድኖች ቮልፍስቡርግ ጠንካራ ተጋጣሚ ደርሶታል። ቮልስፍቡርግ ከእንግሊዙ ቶትንሀም ሆትስፐር ጋር ነው የሚጋጠውመው። ሌሎቹ ሁለት የጀርመን ቡድኖች፦ ባየር ሌቨርኩሰን ከያንግ ቦይስ ቤርን እንዲሁም ሆፈንሃይም ከኖርዌዩ ሞልደ ጋር በደርሶ መልስ ይጫወታሉ። ቪላሪያል ከዛልስቡርግ፣ ብራጋ ከሮማ፤ ክራሶናድር ከዲናሞ ዛግሬብ፤ ዲናሞ ኪዬቭ ከብሩዥ፤ ግራናዳ ከናፖሊ፤ የእስራኤሉ ማካቢ ቴልአቪቭ ከሻክታር ዶኒዬትስክ፤ ሊል ከአያክስ አምስተርዳም፤ ኦሎምፒያኮስ ከአይንድሆቨን፤ ሪያል ሲሲዬዳድ ከማንቸስተር ዩናይትድ፤ አርሰናል ከቤኔፊካ ሊዛቦን፤ ሚላን ከሮተር ሽቴርን ቤልግራድ፤ አንትቬርፐን ከግላስኮው ሬንጀርስ  እንዲሁም ስላቪያ ፕራህ ከላይሰተር ሲቲ ጋር ይጋጠማሉ።

ምስል picture-alliance/Keystone/S. Di Nolfi

ዘረኝነት

ከሻምፒዮንስ ሊግ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ባሳለፍነው ሳምንት የታየው የዘረኝነት ጉዳይ ነው። ፓሪ ሳንጃርማ ከቱርኩ ባሳክሴሂር ኢስታንቡል ጋር ሲጋጠም ሩማኒያዊው አራተኛ ዳኛ የዘረኝነት ቃል መጠቀማቸው ጨዋታው እንዲቋረጥ አስገድዶታል። የቀድሞው የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች የባሳክሴሂር ኢስታንቡል ተባባሪ አሰልጣኝ ፒዬር ዌቦ በመጀመሪያው አጋማሽ ቀይ ካርድ ሲያይ አራተኛ ዳኛ ሠባስቲያን ኮልቴቹ ፒዬርን ጥቊር የቆዳ ቀለሙን የሚመለከት ዘረኛ ስድብ ሲሰድቡት በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ላይ ተላልፏል። የሩማንኛ ቃሉ (Negru) ትርጉሙ «ጥቊር» እንደ ማለት ነው። የባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጨዋታ ቡድኖቹ ዜሮ ለዜሮ እያሉ ተቋርጦ ለረቡዕ ተላልፎ ነበር። ፓሪ ሳን ጃርማ በስተመጨረሻ ባሳክሴሂር ኢስታንቡልን 5 ለ1 ድል አድርጎታል። አኹን በ16ቱ የጥሎ ማለፍ የደርሶ መልስ ግጥሚያ ባርሴሎና ይጠብቀዋል።

ቡንደስሊጋ

ቅዳሜ ዕለት በቡንደስሊጋው ግጥሚያ ቦሩስያ ዶርትሙንድ አስደንጋጭ ሽንፈት ገጥሞታል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በቡንደስሊጋው በሜዳው በሽቱትጋርት 5 ለ1 መሸነፉም አሰልጣኙ ሉቺያን ፋቭሬ ትናንት እንዲባረሩ ምክንያት ሆኗል። ምክትል አሰልጣኙም ማንፍሬድ ሽቴፈስ ተባረዋል።  ሌላኛው ምክትል አሰልጣኝ ኤዲን ቴርዚች ቡድኑን እስከ ዘንድሮ የጨዋታ ዘመን ያሰለጥናሉ ተብለዋል። ነገ በቡንደስሊጋው ከቬርደር ብሬመን ጋር የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን ያደርጋሉ።

ምስል Bernd Thissen/dpa/picture alliance

ቦሩስያ ዶርትሙንድ በትናንቱ ሽንፈት ከአራተኛ ደረጃው ወደ አምስተኛ ተንሸራቷል።  መሪው ባየር ሌቨርኩሰን ባየር ሙይንሽንን በአንድ ነጥብ በልጦ 25 ነጥብ ሰብስቧል። ትናንት ሆፈንሃይምን 4 ለ1 ነበር ድል ያደረገው። ቅዳሜ ዕለት ቬርደር ብሬመንን 2 ለ o ያሸነፈው ላይፕትሲሽ ከባየር ሙይንሽን በተመሳሳይ ነጥብ ግን በግብ ክፍያ ልዩነት ተበልጦ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል። ቮልስፍስቡርግ የዐርብ ዕለት የአይንትራኅት ፍራንክፉርት የ2 ለ1 ድሉ ተደምሮ በሰበሰበው 21 ነጥብ  አራተኛ ደረጃው። ቦሩስያ ዶርትሙንድን በ2 ነጥብ ይበልጠዋል። አርሜኒያ ቢሌፌልድ ከትናንት በስትያ በፍራይቡርግ 2 ለ0 ተሸንፏል፤ ደረጃውም 16ኛ ነው። ወራጅ ቃጣናው ውስጥ የሚገኙት ማይንትስ እና ሻልከ 5 እና 4 ነጥብ አላቸው። ማይንትስ ዐርብ ዕለት በኮሎኝ 1 ለ0 ተሸንፏል። ሻልከ ትናንት ከአውግስቡርግ ጋር ባደረገው ግጥሚያ 2 እኩል ነው የተለያየው።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ፒዬር ኤመሪክ ኦባሜያንግን በ73ኛው ደቂቃ ላይ በገዛ ቡድኑ ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ  በበርንሌይ 1 ለ0 ተሸንፏል። ግራኒ ሻቃን በ56ኛው ደቂቃ ላይ ቀይ ካርድ ያጣው አርሰናል በኤሚሬትስ ስታዲየሙ በበርንሌይ ሲሸነፍ የመጀመሪያው ነው። አርሰናል ከግማሽ ምእተ ዓመት ወዲህ በአንድ የጨዋታ ዘመን በተከታታይ ለአራት ጊዜያት በሜዳው ሲሸነፍም የትናንቱ የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህም ውጤት መሠረት የሚኬል አርቴታ ቡድን አርሰናል 15ኛ ደረጃ ላይ  ይገኛል። ከወራጅ ቃጣናውም በአምስት ነጥብ ርቀት ላይ ብቻ እንዲወሰን አስገድዶታል። የወራጅ ቃጣናው 18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፉልሃም 8 ነጥብ አለው። ከስሩ ዌስት ብሮሚች እና ሼፊልድ ዩናይትድ በ6 እና 1 ነጥብ 19ኛ እና 20ኛ ደረጃ ላይ ተዘርግተዋል።

ምስል Mike Hewitt/Getty Images/AFP

ፉልሃም ትናንት በከፍተኛ ኹናቴ በመከላከል ሊቨርፑልን የመሪነቱን ዕድል አሳጥቶታል። በትናንቱ ግጥሚያ ፉልሃሞች አንዳንድ ጊዜ ያገኟቸው የነበሩ እድሎችን በመጠቀም በመልሶ ማጥቃት ሊቨርፑል ላይ ብርቱ ፈተና ደቅነው ቆይተዋል። በ25ኛው ደቂቃ ላይም  በቦቢ ራይድ ግብ መሪነቱን ይዘው ቆይተዋል። በ79ኛው ደቂቃ ላይ ሞሐመድ ሳላኅ ሊቨርፑልን አቻ የምታደርገውን ግብ በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል። በእለቱ የፉልሃም ግብ ጠባቂ ድንቅ ነበር። የሞሐመድ ሳላኅ ፍጹም ቅጣትንም ለጥቂት ሊያጨናግፍ ነበር። ግቧን ማጨናገፍ ባይችልም ሊቨርፑል የመሪነቱን ስፍራ እንዳይዝ ግን አድርጓል። 25 ነጥብ ያለው ሊቨርፑል በደረጃ ሰንጠረዡ ከቶትንሀም ሆትስፐር ጋር የሚለያየው በግብ  ክፍያ ብቻ ነው። ቶትንሀም ሆትስፐር ትናንት ከክሪስታል ፓላስ ጋር እንደሊቨርፑል ሁሉ አንድ እኩል ነው የተለያየው።

24 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ላይ የሚገኘው ላይስተር ሲቲ ሳውዝሀምተንን በአንድ ነጥብ ይበልጣል፣ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲን ደግሞ በ2 ነጥብ። ላይስተር ሲቲ ብራይተንን ትናንት 3 ለ0 ነው ያሸነፈው። ሳውዝሀምተን ሼፊልድ ዩናይትድን 3 ለ0 ድል አድርጓል። ቸልሲ ቅዳሜ ዕለት በኤቨርተን የ1 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። ኤቨርተን  እንደ ዌስትሀም ዩናይትድ 20 ነጥብ ይዞ  ግን በግብ ክፍያ ተበልጦ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በተመሳሳይ 20 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ከስሩ የከሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ጋር ከትናንት በስትያ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል።  

ቡጢ

ምስል Andrew Couldridge/Pool/picture alliance

በከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ የታላቋ ብሪታኒያ ተፋላሚዎች አንቶኒ ጆሹዋ እና ታይሰን ፉሪ ግጥሚያ በሚቀጥለው የጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት በበርካታ የቡጢ ስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ ይጠበቃል። አንቶኒ ጆሹዋ፦ የዓለም አቀፍ ቡጢ ፌዴሬሽን (IBF)፣ የዓለም ቡጢ ማኅበር (WBA) እንዲሁም የዓለም ቡጢ ድርጅት (WBO) የቀበቶዎችን ሰብስቧል። ታይሰን ፉሪ በበኩሉ የዓለም ቡጢ ምክር ቤት (WBC) ቀበቶ ባለቤት ነው። በእነዚህ ኹለት የከባድ ሚዛን ቡጢ ተወዳዳሪዎች መካከል የሚደረገው ግጥሚያ በከባድ ሚዛን የአራቱም ዋና ዋና ቀበቶዎችን ለመሰብሰብ የሚደረግ በመሆኑ በበርካቶች ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። በከባድ ሚዛን ቀበቶ ፍልሚያ አራቱ ወሳኝ ቀበቶዎችን ለማግኘት የሚደረግ ፍልሚያ መኾኑም በታሪክ የመጀመሪያው ያደርገዋል። በኹለቱ የከባድ ሚዛን ተፋላሚዎች መካከል ግጥሚያው እውን መሆኑ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ይፋ እንደሚደረግ ተገልጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW