የታንዛኒያው ድርድር ተስፋ እና ተግዳሮቱ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 26 2015በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት እና ኦሮሚያ ውስጥ በስፋት ታጥቆ በሚንቀሳቀሰው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሲል በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል ታንዛኒያ ዛንዚባር ደሴት ላይ ለዘጠኝ ቀናት ገደማ ሲካሄድ የነበረው ውይይት የመጀመሪያው ምዕራፍ ትናንት ተመናቋል። ይህ ውይይት በግጭት መካከል ከቤት ንብረቱ ለተፈናቀለውና ሰላምን ለሚናፍቅ ለክልሉ ኅብረተሰብ ሲጠበቅ ቆይቷል። የአምቦ ከተማው ነዋሪ አቶ ሴኔሳ ደምሴ ይህን ውይይት በጉጉት ሲጠብቁ ከነበሩ የማኅበረሰቡ አካላት አንዱ ናቸው። «ኦሮሚያ ክልል በጦርነት ውስጥ የከረመ ክልል ነው። በሰላም ወጥቶ መግባት የናፈቀው የማኅበረሰቡ ክፍል በርካታ ነው። ይህ ውይይት ቢያንስ መፈናቀል እና ሞትን ብሎም የተኩስ ድምጽ ነዋሪዎችን የማያውክበትን ሁኔታ ፈጥራል በሚል ትልቅ ጉጉት ውስጥ ቆይተናል።»
ሁለቱ ተደራዳሪ ቡድኖች ትናንት ባወጡት አጭርና ዝርዝር መረጃዎች በሌሉት የተናጠል መግለጫ፤ ተስፋ ሰጪ ያሉት እና ወደፊት ለመቀጠል በተስማሙበት ውይይት በወሳኝ ፖለቲካዊ ነጥቦች ላይ ከስምምነት ሳይደረስ መቅረቱን አንስተዋል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ዑርጌሣ በዚህ ሂደት ውስጥ ሁለቱ ወገኖች ከጦርነት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት መምጣታቸው በራሱ ትልቅ እምርታ ነው ባይ ናቸው። «የፖለቲካ ችግሮችን በንግግር ለመፍታት መቀመጥ በራሱ ትልቅ ተስፋ ነው። ሁለቱም ወገኖች በተናጥል ባወጡት መግለጫም በቀጣይ ምዕራፎችም ውይይት እንደሚቀጥል ከመስማማት መድረሳቸው ተስፋ አስቆራጭ አይደለም። ለጊዜው በውይይታቸው ላይ ሁሉንም መረጃ አለመስጠታቸውም የውይይቱ ቀጣይነት ስለሚያሳይ ያንንም በትዕግስት መጠበቁ ነው የሚበጀው።» ብለዋል። ሌላው አስተያየት ሰጪ ፖለቲከኛ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ቃል አቀባይ አቶ ሱልጣን ቃሲም ናቸው።
እንደ እሳቸው አተያየትም ሁለቱ ወገኖች ከጦርነት ጉሰማ ወደ ሰላማዊ ውይይት መሸጋገራቸው ሰላሙን ላጣው ለክልሉ ህዝብ ትልቅ እፎታ ነው። ሁለቱ ወገኖች በተናጠል ባወጡትም መግለጫ የውይይቱን ቀጣይነትና ተስፋ ማሳየታቸው አመርቂ ነው ብለዋል። ቢያንስ በዚህ የውይይት ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ይጠበቅ ነበር ያሉት አቶ ሱልጣን፤ እጅግ ውስብስብ ያሉት የፖለቲካ ሁናቴ በዘጠኝ ቀን እንዲፈታ ቀድሞውኑም እንደማይጠበቅ አስረድተዋል። ፖለቲከኞቹ ሰላማዊ ውይይቱ በቀጣይሊገጥመው የሚችሉ ተግዳሮቶች ሊኖሩ ይላሉ የሚል ስጋትም አላቸው። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ባለሥልጣኑ አቶ በቴ ዑርጌሳ መንግሥት የፖለቲካ ምዕዳሩን አለማስፋቱ እና ከትጥቅ ትግል ውጪ ያሉትን የፖለቲካ ሰዎችን ከእስር በመልቀቅ ምዕዳሩን ቢያሰፋ ባይ ናቸው። የኦፌኮ ቃል አቀባይ አቶ ሱልጣን ቃሲም በበኩላቸው፤ ውይይቱን የሚያደናቅፉ በመላምት ላይ የተመሰረቱ ኃላፊነት የጎደላቸውን መረጃዎች ማሰራጨት አግባብነት እንደሌላቸው አንስተዋል።
ሁለቱ ተደራዳሪ ቡድኖች ትናንት ባወጡት መግለጫ ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት ከሳምንት የዘለለውን ውይይት ቀጣይ ምዕራፎች እንደሚኖሩት አመልክተዋል። ይሁንና በውይይቱ ወሳኝ ነጥቦች ላይ ከስምምነት መድረስ አለመቻሉም ተነስቷል። ተደራዳሪ ቡድኖቹ ከስምምነት ላይ የደረሱባቸው እና ያልደረሱባቸው ነጥቦቹ ላይ የሰጡት ዝርዝር መረጃ ግን የለም። ዶቼ ቬለ በነዚህ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በስልክ እና በጽሑፍ መልእክት የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሠ ቱሉ፣ የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ቃል አቀባይ ቢለኔ ስዩም እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከፍተኛ አማካሪ እና የተደራዳሪ ቡድኑ አባል ጅሬኛ ጉደታን በተደጋጋሚ ጠይቆ ለዛሬ አልሰመረም።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር