1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታደሰው የግብጽና ሱዳን ጫና

ቅዳሜ፣ ሰኔ 5 2013

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የአባይ ግድብ ሙሌት በሐምሌ እና ነሐሴ ልታካሂድ እንደምትችል አመላክታለች። በአንጻሩ የግድቡ ጉዳይ ስጋት እንደፈጠረባት የምትናገረው ግብጽ ሱዳንን ከጎኗ በማድረግ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ ያለውን ቀውስ ለማረጋጋት ጣልቃ ይግባልን የሚል ጥሪያቸውን አጠናክረዋል።

Äthiopien Addis Abeba | Report | Grand Ethiopian Renaissance Dam
ምስል DW/N. Desalegen

ትኩረት በአፍሪቃ 05.10.2013

This browser does not support the audio element.

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ ከአንድ ወር በፊት ነበር ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የታላቁ የህዳሴ ግድብን ሙሌት ብታካሂድ ሀገራቸው ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ የለም ሲሉ ለዜጎቻቸው ያረጋገጡት። ሚኒስትሩ ግብጻውያን የውኃ እጥረት ያጋጥመናል የሚል ስጋት እንዳይኖራቸውም በአስዋን ግድብ አስተማማኝና በቂ የውኃ ክምችት እንዳለም ነበር የተናገሩት። ሆኖም ከዚያ ወዲህ ከግብጽ የሚወጡ ዘገቦች ከሙሌቱ ጋር በተገናኘ አሁንም ግብጽ ከፍተኛ ስጋት እንዳላት ያመላክታሉ። ሱዳንን ከጎኗ ማሰለፉ የቀናት ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ የምታሳርፈውን ጫና አጠናቅራለች። ባሳለፍነው ሳምንትም ሁሉቱ ሃገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ግድቡን አስመልክቶ በያዘችው ፖሊሲ መጽናቷ የሚያስከትለውን አደጋ ተመልክቶ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቀውሱን ለማርገብ ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ አቅርበዋል። የግብጽ ባለሥልጣናት ግድቡን አስመልክተው የሚሰጡት የተጣረሰ አስተያየት እንዳለ ሆኖ በአሁኑ ወቅት ግብጽ በድጋሚ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ጣልቃ ገብነት ለመጋበዝ ምን አነሳሳት? በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንዲሁም የአባይ ውኃ ጉዳይ ተመራማሪ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ እንደአዲስ በዚህ ሳምንት ለሚታየው ግፊት ይኽን ይጠረጥራሉ።

«እንደምጠረጥረው አሁን አሜሪካ እና ምዕራብ አውሮጳ አገሮች በዚህ በትግራይ ጉዳይ ኢትዮጵያ ላይ ግፊት በመጨመራቸው ይኼንኑ ተዳብለው ምናልባት አንዳንድ አዳዲስ ጥቅም እናገኛለን ብለው አስበው ይሆናል። እንጂ ከአሁን በፊት የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች የተመለሱ ወይም በውይይት ላይ ያሉ ናቸው እንጂ አዲስ ነገር መሬት ላይ ወርዶ የለም።»

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ለኃይል ማመንጫነት ይውላል በሚል የምትገነባው ግድብ ከሦስቱ ሃገራት በተውጣጡ ባለሙያዎች ተጠንቶ አሉታዊ ተጽዕኖው እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ መገለጹ ይታወሳል። በጎርጎሪዮሳውዊ 2015 ዓ,ም መጋቢት 23 በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የተፈረመው ባለ 10 ነጥብ የመግባቢያ ሰነድም ትብብሩ በሦስቱም ሃገራት የጋራ መረዳት፣ ፍላጎት፣ መልካም ሃሳብ፣ ጥቅም እና ዓለም አቀፍ ሕጎችን መመሪያ አድርጎ የተደረሰበት መሆኑ ተገልጿል።

ምስል DW/Negassa Desalegen

የአባይ ውኃ ጉዳይ ተመራማሪው ዶክተር ያቆብ አርሳኖ እንደሚሉትም ኢትዮጵያ አምና ያደረገችውም ዘንድሮም ሆነ ለወደፊት የምታካሂደው የግድቡ ሙሌት በጎርጎሪዮሳዊው 2018 ዓ,ም የሦስቱም ሃገራት ብሔራዊ ገለልተኛ ሳይንሳዊ ተመራማሪ ቡድን በአንድ ላይ ተቀምጠው ሙሌቱን እንዲሁም በሙሌቱ ሂደት ምናልባት ሊያጋጥሙ ይችላሉ የሚባሉ ነገሮችን ታሳቢ በማድረግ ባቀረበው ሃሳብና ባደረገው ስምምነት መሠረት ነው።  

 ግብጽ የአባይ ግድብን ሙሌት ለማስቆም የምታደርገው ጥረት የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ጫና በመጋበዝ ብቻ አላበቃም። በኢትዮጵያ አጎራባች ሃገራት እንደ ጅቡቲ እና ኬንያ እንዲሁም ዩጋንዳ በመዝለቅም ወታደራዊ ትብብር ጨምሮ የተለያዩ ውሎችን ስትፈራረም ይታያል። ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ ባለፉት ሳምንት ከሱዳን፤ ከደቡብ ሱዳን፤ ከጅቡቲ እንዲሁም ዩጋንዳ ጋር ውጤታማ የተባሉ ውይይቶችን እና ስምምነቶችን ማድረጓን የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ዶክተር ስለሺ በቀለ በትዊተር ገጻቸው አመላክተዋል። እሳቸው እንደገለጹት የዩጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የአባይ ተፋሰስ ሃገራት የሚገኙበት ጉባኤ ተጠርቶ የየሃገራቱ መሪዎች ማከራከራቸው በቀጠለው ጉዳዮች ላይ መመሪያ መስጠት እንዲችሉ ሃሳብ አቅርበዋል። ቀደም ሲልም የተፋሰሱ ሃገራት በተገኙበት ውይይት ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሌለው መመላከቱ ግብጽን አላስደሰተም ነበር። አሁን ግብጽ ትብብራቸውን የምትፈልገው የኢትዮጵያ የቅርብ ጎረቤት ሃገራት እስከምን ድረስ ተጽዕኖ ማሳረፍ ይችላሉ ብሎ መገመት ይቻል ይሆን?

የአባይ ውኃ ተመራማሪው ዶክተር ያቆብ አርሳኖ እንደሚሉት የአባይ ግድብ እንኳን ኢትዮጵያን ግብጽና ሱዳንንም በሚገባ የሚጠቅም መሆኑን በመረጃ የተደገፈ እውነታ ነው። እንደእሳቸው እምነትም ይኽን ከብዙ ግድቦች የተሻለ አገልግሎትና ጥራት ያለው የህዳሴ ግድብን በዚህ ሰዓት መቃወም ማለት በሀገሪቱ ላይ ደባ መፈጸም ነው። ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ዘገባው ያድምጡ!

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW