1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታገቱት ተማሪዎች ጉዳይ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሱዳን ጉብኝት፤ የአዉሮጳ እግርኳስ ግጥምያ

ዓርብ፣ ሐምሌ 5 2016

ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በታጣቂዎች ከታገቱት 167 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች 160ዎቹ መለቀቃቸውን የመንግሥት ባለሥልጣናት ቢናገሩም ቤተሰቦች ግን እስካሁን ልጆቹ እንዳልተለቀቁ አስታዉቀዋል። ኧረ እንደታገቱ ነው። ከታገቱት ተማሪዎች ውስጥ የኔ ባች የሆኑ በርካታ ጓደኞቼ አሁንም በአፋኞች እጅ ዉስጥ ናቸዉ ሲሉ ተማሪዎችተናግረዋል።

የታገቱት የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጉዳይ
የታገቱት የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጉዳይምስል Seyoum Getu/DW

የታገቱት ተማሪዎች ጉዳይ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሱዳን ጉብኝት፤ የአዉሮጳ እግርኳስ ግጥምያ

This browser does not support the audio element.

የታገቱት 167 ተማሪዎች ጉዳይ

በኦሮምያ ክልል የታገቱት  167 ተማሪዎች ጉዳይ፤ ፖርት ሱዳን የተገኙት የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም፤ የአዉሮጳ እግርኳስ ሻንፒዮና የዋንጫ ተፋላሚዎች በሚል ርዕስ ስር የተሰጡ አስተያየቶችን ይዘናል።

ባለፈው ሳምንት ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ አካባቢ በታጣቂዎች ከታገቱት 167 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች160ዎቹ መለቀቃቸውን የመንግሥት ባለሥልጣናት ቢናገሩም ቤተሰቦች ግን እስካሁን ልጆቹ እንዳልተለቀቁ አስታዉቀዋል። ዶቼ ቬለ ካነጋገራቸው መካከል እህታቸውን እስከአለፈዉ ረቡዕ ድረስ በስልክ አግኝተው ማነጋገራቸውና አሁን እዚያው በአጋቾቹ ቁጥጥር ስር መሆኗን የገለጹልን ቤተሰብ የተለየ ነገር አለመኖሩን አረጋግጠዋል። ከትናንት በስትያ ጠዋትም እህታቸውን እንዲያነጋግሩ ከሚያገናኟቸው አጋቾች አንዱን በስልክ አግኝተው እንደነበር የገለጹት እኒሁ እማኝ፤ እህታቸውን ወዲያው ማነጋገር ያልቻሉት ግለሰቡ ታጋቾቹ የሚገኙበት፤ አካባቢ ባለመሆኑ ከ30 ደቂቃ በኋላ እንዲደውሉ እንደነገራቸው አክለው ገልጸዋል። ረቡዕ እለት ማምሻውን የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ በበኩላቸዉ «በተደረገ ጥብቅ ኦፕሬሽን ከ167 ታጋች ተማሪዎች መካከል 160ዎቹ ተለቀዋል» ማለታቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።    

ፊቨን ዋክጅራ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ ኧረ እንደታገቱ ነው። ከታገቱት ተማሪዎች ውስጥ የኔ ባች የሆኑ በርካታ ጓደኞቼ አሁንም በአፋኞች እጅ ዉስጥ ናቸዉ። ከተማሪ እስከ መምህር ሁሉም ያቅሙን እያዋጣ ባለበት ሁኔታ እንደዚህ አይነት የውሸት ዜና መነገሩ በጣም ያሳዝናል፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን በፌስቡክ ላይ አስቀምጠዋል።

ጋሻዉ ሙሉጌታ የተባሉ በበኩላቸዉ ፤ ሰሜን ሸዋ ዞኑ በአጠቃላይ ችግር ውስጥ ነው ያለው።  አማራ እየታገተ፤ እየተገደለ፤ ገንዘቡን እየተዘረፈ ፤ ገንዘብ ከፍሎም እየሞተ ነው። በተለይ የደራ ህዝብ ትልቅ አደጋ ውስጥ ነው ያለው።  ሁሌ መሞት መታገት ነው እጣፈታው።  ሺ ሰው ቢሞት አይነገርለትም። ይሄ ደሞ በደንብ እዲሰፋ እና እዲደራጁ አድርጓቸዋል። ገና ሁሉንም ያዳርሳል፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ደጀኔ ገመቹ የተባሉ አስተያየት ሰጭ፤ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የአማራ ተማሪዎች ከታገቱ በኋላ ተለቀዋል ብለው የተሳለቁትን ስላቅ ዛሬም ደግመዉታል፤ ያሳዝናል ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

ፎቶ ማህደር ፤ ቢሾፍቱ ምስል Seyoum Getu/DW

ኮስዬ ሞቱማ የተባሉ የፌስ ቡክ ስም ያላቸዉ በአስተያየታቸዉ፤ የታገቱ ተማሪዎች በረሀብ እየሞቱ ነው። ዜናውን ለዓለም አሰሙልን። ይኸ ሰው በላ አጋች ጩኸታችንን እየሰማ አይደለም። ፍትህ ለታገቱ ልጆቻችን ሲሉ አስተያይት አስቀምጠዋል።

በየነ አይሬ የተባሉ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ፖለቲካ፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ፖለቲካ፤ ተማሪዎችን ማገት ሆንዋል። ተማሪ በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ መጫወጫ ሆኖዋል። ተማሪን ማገት ይቁም፡ ፍትህ ለታገቱት ተማሪዎች ሲሉ በቃል አጋኖ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ፍቅሩ በየነ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የአሜሪካን ኤምባሲን ጨምሮ የጉዳዩን አሳሳቢነት ስለዘገቡ መንግስት በድንጋጤ የሰጠው ተለቀዋል የሚል ማስተባበያ መሰል መግለጫ የትም አያደርስም:: ከጅምሩ እንዲህ አይነት ነገር እልባት ትሰጥቶት መንግስትም በሙሉ ቁርጠኝነት ቢሰራ ኖሮ በተከታታይ ታገቱ፣ታፈኑ፣ለማስለቀቅ ይህን ያህል ብር ተጠየቀ የሚሉ ዘገባዎችን አንሰማም ነበር: ሲሉ አስተያየት ጽፈዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖርት ሱዳን ጉብኝት

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሱዳን ከጀነራል አብደል ፋታሕ አልቡርሃን ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጀነራል አልቡርሃን የተገናኙት በቀይባሕር ዳርቻ በምትገኘው የፖርት ሱዳን ከተማ ነው።

ፎቶ ፖርት ሱዳን ምስል ASHRAF SHAZLY/AFP/Getty Images

የሱዳን ሉአላዊ ምክርቤት ባወጣው መግለጫ በዝግ በተካሄደው ስብሰባ ጀነራል አልቡርሃን፤  በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሐይሎች እየተፈጸመ ነው ስላሉት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጻ ማድረጋቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸዉ በማሕበራዊ መገናኛ ብዙኃን ገጻቸው ባስተላለፉት መልክት "የወንድም ሱዳን ሕዝብ ችግር የኛም ችግር፤ ሰላማቸውም ሰላማችን በመሆኑ ለሱዳን ሕዝብ እፎይታና የብልጽግና ጉዞ ዛሬም እንደትላንቱ ከልብ እንሰራለን" ብለዋል።

ዎርንቶ ሞርቆ ቁጨና የተባሉ የፌስቡል ተከታታይ፤ ጀነራል አብደልፋታሕ አልቡርሃን ቅድምያ የኢትዮጵያ ሰላም ሰላማቸው መሆኑን ካወቁ፤ ሱዳን ሰላም ትሆናለች ይህንን ማመን አለባቸዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

አብዱ ሀበሻ የተባሉ አስተያየት ሰጭ፤ አይ የአፍሪቃ መሪዎች ይገርሙኛል ሲሉ አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ። አይ የአፍሪቃ መሪዎች ይገርሙኛል፤ ሀገራቸውን በጦርነት እያፈረሱ ትልቅ ሥራ እንደስሩ ሲተቃቀፉ ሳይ፤ ይገርመኛል ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

ጀግናዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን የጀመሩት አሳየ አለባ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸዉ። ጀግናው፤ ሁሌም እረፍት የለለው መርያችን፤  ሁሉም አመራሮች እንዳንተ ቢሰሩ ኖሮ እትዮጵያ የት በደረሰች ነበር።  ሽህ ዓመት ኑር፤ የተከበርክ ዶ/ር አብይ ፤ ጀግናችን ነህ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። 

የአዉሮጳ እግርኳስ ሻንፒዮና 2024   

የአዉሮጳ እግር ኳስ ሻምፒዮና የዓለም የእግር ኳስ አፍቃሪዎችን ወደ አዘጋጅዋ ሃገር ጀርመን ትኩረታቸዉን እንዲያደርጉ  ማድረጉን እንደቀጠለ ነዉ። ባለፈዉ ረቡዕ ከኔዘርላንድ ጋር የገጠመችዉ እንግሊዝ ለፍጻሜ የዋንጫ ሽሚያ የበርሊን ቲኬቷን ቆርጣለች። ባለፈዉ ማክሰኞ በስፔን እና ፈረንሳይ መካከል ለፍጻሜ ለማፍ በተደረገው ፍልሚያ በስፔን የ2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቆ እንደ እንጊሊዝ ሁሉ ስፔን ለአውሮጳ ዋንጫ ፍልምያወደ በርሊን አቅንታለች።  በ 16 ዓመቱ ታዳጊ ላሚኔ ያማል ፊት አውራሪነት ስፔን ዋንጫዉን ታሸንፋለች የሚለዉ የደጋፊዎች አስተያየት በርከት ብሎ እየታየ ነው።  በግማሽ ፍጻሜው ጨዋታ በተሻለ አቋም የቀረቡት ሦስቱ አናብስትም፤ ቀላል ግምት የማይሰጣቸው እንደሆኑ አሳይተዋል። የሆነ ሆኖ አሁን ጥያቄው የ 17ኛውን የአውሮጳ ዋንጫ ማን ያነሳ ይሆን ነዉ።  ስፔን ወይስ እንግሊዝ? የፊታችን እሁድ ምሽት 4 ሰዓት በርሊን  በኦሎምፒያ ስታዲየም ቀጠሮ ተይዟል። እርሶስ ምን ይላሉ? ማን ያሸፋል ?

የአዉሮጳ እግር ኳስ ሻምፒዮና 2024 ምስል Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

ተስፋዬ እያሱ ሰሙ የተባሉ የዶቼ ቬለ ማኅበራዊ መገናኛ ተከታታይ ስፔን ዋንጫዉን ትበላለች ብለዋል።

ቱት ቶት ላትጆር የተባሉ ሌላዉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ ለእንግሊዝ  እግር ኳስ ቡድን፣ ለሼክስፒር ምድር፣ ለእግር ኳስ አፍቃሪዉ፣ እና የቀይ ድርብ አዉቶቡሶች ባለምልክት፤  ምስጋና ይድረሰው። እንጊሊዝ በታሪክ፣ በባህልና በተለያዩ መልክዓ ምድሮች የተሞላች አገር ናት። እንጊሊዞች በደጋግሜ እንኳን ደስ አላችሁ ዋንጫዉን ታነሳላችሁ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ወንድሙ ደግፌ ችግር የለዉም ሲሉ አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ። ችግር የለዉም እንጊሊዝ በስፔን ትቀጠቀጣለች፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

ደጀኔ ገመቹ  የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ ኣመናችሁም አላመናችሁም ዋንጫው የስፔን ወይም የእንግሊዝ ነው ሲሉ ፈግግ የሚያሰኝ የማያጣላ አስተያየት ሰጥተዋል። አድማጮች የፊታችን እሁድ የአዉሮጳ የኳስ ሻንፕዮና የዋንጫ ግጥምያን ለማየት ተሰናድታችኃል? ዋንጫዉን ማን ይወስድ ይሆን? ስፔን ወይስ እንጊሊዝ ? አስተናጋጅ ሃገር ጀርመንንስ እንዴት አገኛችኋት ጻፉልን!

አዜብ ታደሰ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW