1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ታግተዉ የተወሰዱት የቺቦክ ሴት ተማሪዎች ከ10 ዓመት በኋላ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 5 2016

ከ 10 ዓመት በፊት በናይጀርያ 276 ሴት ተማሪዎች ቦኮሃራም ታፍነዉ ከተወሰዱ በኃላ ቺቦክ የሚገኘዉ ትምህርት ቤቱ ተዘግቶ ቆይቷል። በ16 እና 18 ዓመት ዕድሜ ክልል የሚገኙት ከእነዚህ 276 የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል ወደ መቶ ገደማ የሚሆኑት አምልጠዉ ቢመለሱም፤ በመቶዎች ከሚቆጠሩት ታፋኝ ሴቶች አሁንም የደረሱበት አይታወቅም፤

ከእገታ የተለቀቁ የቺቦክ ልጃገረዶች በአቡጃ
ከእገታ የተለቀቁ የቺቦክ ልጃገረዶች በአቡጃ ምስል፦ Sunday Aghaeze/AFP

ከ10 ዓመት በፊት ታፍነዉ የተወሰዱት የቺቦክ ሴት ተማሪዎች

This browser does not support the audio element.

የዛሬ አስር ዓመት በናይጀርያዋ ቦርኖ ግዛት ከቺቦክ  ትምህርት ቤት 276 ወጣት ሴት ተማሪዎች በጽንፈኛዉ ቦኮሃራም ታግተዉ ከተወሰዱ በኃላ ትምህርት ቤቱ ተዘግቶ ቆይቷል። በ16 እና 18 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ከእነዚህ  276 ወጣት ሴት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል ወደ መቶ ገደማ የሚሆኑት አምልጠዉ ቢመለሱም፤ በመቶዎች ከሚቆጠሩት ታፋኝ ሴቶች አሁንም የደረሱበት አይታወቅም፤ አልያም ከታፋኞች መካከል አንዳንዶች የጽንፈኛዉን ቡድን አባላት አግብተዉ ተቀምጠዋል የሚል ግምት አለ።

በአማፂዉ ቡድን የታፈኑት የቺቦክ ልጃገረዶች   

በናይጀርያ ቺቦክ ግዛት በአማፅያን የተደመሰሰዉ የልጃገረዶች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ የናይጄሪያ ወታደሮች ከቦርኖ ግዛት እና ከናይጄሪያ ፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር በአሁኑ ወቅት በጋራ የትምህርት አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል። ወላጆች ዛሬ ከአስር ዓመታት በኋላ መልሶ ወደተገነባዉ ትምህርት ቤት ልጆቻቸዉም መላክ በመቻላቸዉ እና ተማሪዎችም ጥብቅ የደህንነት ጥበቃ ወደ ሚደረግበት ትምህርት ቤት መሄድ በመጀመራቸዉ ደስተኛ መሆናቸዉን ተናግረዋል። 

ታግተዉ ደብዛቸዉ የጠፋዉ የቺቦክ ታዳጊ ሴቶች መታሰብያ ምስል፦ Audu Ali Marte/AFP

በናይጀርያ የሚንቀሳቀሰዉ ቦኮ ሃራም አማጺ ቡድንበጎርጎርጎረሳዉያኑ ሚያዝያ 14 ቀን 2014 ዓ.ም ቺቦክ የሚገኘዉን የልጃገረዶች ትምህርት ቤትን በመዉረር የሁለተኛ ደረጃየመጨረሻ ዓመት ፈተናቸውን ለመፈተን እየተዘጋጁ የነበሩ 276 ተማሪዎችን አፍኖ ወሰደ። ከእነዚህ መካከል 164 ቱ ከአማፂዉ ቡድን አምልጠዉ ወደቤታቸዉ ሲመለሱ ፤ ቀሪዎቹ 112  የደረሱበት አይታወቅም፤ ከነዚህ መካከል አንዳንዶቹ አማፅያኑን አግብተዉ ሳይቀመጡ አይቀርም የሚል መረጃ አለ።

በአማፂዉ የወደመዉ የቺቦክ ልጃገረዶች ት/ቤት ዛሬ

በቦኮ ሃራም አሸባሪ ቡድን የዛሬ 10 ዓመት በቃጠሎ የወደመዉ ትምህርት ቤት ዛሬ በአዲስ መልክ ታድሶ ‹‹የመንግሥት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶችት ወንዶች እና ሴት ታዳጊ ተማሪዎች መማርያ ሆንዋል።

ትምህርት ቤቱ አዳዲስ መማሪያ ክፍሎች፤ ቤተ መጻሕፍት እና ላብራቶች፤  ኮምፒውተር መማርያ ማዕከል፤ የስፖርት መድረክ፤ ክሊኒክ እና የሰራተኞች መኖሪያ ተገንብቶበታል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ጥብቅ በሆነ የደኅንነት ስሜት ውስጥ በተለያዩ ክፍሎች ለመማር ተመዝግበዋል፤ የቺቦክ ማኅበረሰብ የእለት ኑሮም ወደ ሰላማዊነት እየተመለሰ መሆኑን የቺቦክ የመንግሥት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ማላም ሙሐመድ ቡካር ተናግረዋል።   

ናይጀርያ ቦርኖ ግዛት ቺቦክ የልጃገዶች ትምህርት ቤት ምስል፦ Kola Sulaimon/AFP

".... ትምህርት ቤቱ ወደ 2021 ወደ ነበረዉ ክፍለ ጊዜው ተመልሷል። እንደድል ሆኖ አብዛኞቹ ወላጆች ከአደጋዉ በኃላ ልጆቻቸዉን  ጎረቤት ግዛት አዳማዋ ወደ ሚገኙ ትምህርት ቤቶች አዛዉረዋል። ይሁን እንጂ አሁን ከበየሳምንቱ ማለት ይቻላል አዳዲስ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እየተመዘገቡ ነዉ። ወላጆችም ትምህርት ቤቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በማየታቸዉ ተደስተናል...... " 

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በትምህርት ቤቱ ስላለዉ የተማሪዎች እና አስተማሪዎች ጥብቅ የፀጥታ ጥበቃም ተናግረዋል።

ምስል፦ Olalekan Richard/AP Photo/picture alliance

".... በእርግጥም ጥብቅ የፀጥታ ጥበቃ አለን ። በሁሉም ነገር ጥሩ ጥበቃ አለ ማለት ይቻላል። ፍርሃት የለንም፣ መምህራኑ፣ ተማሪዎቹ እና መላው ማኅበረሰብም ፍርሃት የለዉም። በትምህርት ቤቱ ግቢ እና ዙሪያ ጥብቅ ቁጥጥር አለን። ምንም እንኳ ትምህርት ቤቱ በጣም ትልቅና አንድ ኪሎ ሜትር ካሬ ቢሆንም ጊቢዉ 24 ሰዓት በወታደሮች ይጠበቃል። ስለዚህ የደህንነት ጉዳይን በተመለከተ ምንም የሚያሳስበን ነገር የለም። ....."  

የቺቦክ ት/ቤት የፀጥታ ጉዳይ

የትምህርት ቤቱ ግንባታና እድሳት ለቺቦክ ነዋሪዎችና ለከተማዋ ልጆች እንደገና ተስፋ እንዲፈነጥቅ አድርጓል ። አንዳንድ ወላጆች ያለፍርሃት ልጆቻቸዉን ወደ ትምህርት ቤቱ እንደሚልኩም ተናግረዋል። ታግተዉ የተወሰዱት የቺቦክ ሴት ተማሪዎች ጉዳይ ቃል አቀባይ የሆኑት አዩባ አልማሶን በትምህርት ቤቱ ምንም አይነት ስጋት የለም ባይ ናቸዉ።

"..... እንደ አንድ አባት ከትምህርት ቤቱ ሊያግደን የሚችል ምንም ዓይነት ስጋት የለም እላለሁ ። ብቸናዉ ነገር መንግስትን የምንሟገተዉ እና እንዲሰራ የምንለዉ፣ በተለይም ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የተጀመረው እና ግን ፍፁም ተግባራዊ ያላደረገዉን በትምህርት ቤት አስተማማኝ የፀጥታ ደህንንነትን እውን እንዲያደርግ ነው። ስለዚህ ቢያንስ ሌላ ስትራቴጂ ይከተል፣ ተጨማሪ ግኝቶችን ያድርግ፣ ሌሎች አገሮችን ተሞክሮ ይጠይቅ..." 

የታደሰዉ የቺቦክ የልጃገረዶች ትምህርት ቤት ምስል፦ Kola Sulaimon/AFP/Getty Images

ሃፒ አዳሙ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤቱ ከሚማሩት ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት። ትምህርት ቤቱ ጥሩ እና ለመማር ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸዉን ትመሰክራለች።

"..... በትምህርት ቤቱ በቂ የመማርያ ክፍሎች፤ በቂ መምህራን ይገኛሉ። ምንም ዓይነት የደህንነት ፈተና የለም። በቂ የደህንነት ጥበቃ ስላለን በጣም ተደንቀናል። በትምህርት ቤታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን ችግሮች፣ በቂ የመማርያ መጻሕፍት፣ በቂ የላብራቶሪ መሳሪያ፣ እንዲሁም ኮምፒውተርና ማተሚያ ቤት ያለመኖራቸዉ ነዉ..."

ሞሐመድ ነስሩ / አዜብ ታደሰ  

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW