1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስኢትዮጵያ

የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የተጠቃሚዎችን የግል መረጃ ለምን ይሰበስባሉ?

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ግንቦት 6 2017

በምንኖርበት የበይነመረብ ዓለም ጎግል ላይ በየቀኑ 8.5 ቢሊዮን የመረጃ ፍለጋዎች ይካሄዳሉ።በአሁኑ ወቅት ለብዙዎች የህይወት አንድ አካል በሆኑት የተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን እና በላፕቶፕዎቻችን ላይ በየቀኑ የምንጠቀማቸው ብዙዎቹ አገልግሎቶች ነፃ ናቸው።ነገር ግን በሌላ መንገድ የግል መረጃዎቻችንን በመስጠት ለኩባንያዎቹ ዋጋ እንከፍላለን።

ውስጥ ጎግል ላይ በየቀኑ 8.5 ቢሊዮን የመረጃ ፍለጋዎች ይካሄዳሉ
ውስጥ ጎግል ላይ በየቀኑ 8.5 ቢሊዮን የመረጃ ፍለጋዎች ይካሄዳሉምስል፦ La Nacion/ZUMA Press/picture alliance

የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የተጠቃሚዎችን የግል መረጃ ለምን ይሰበስባሉ?

This browser does not support the audio element.

በስልኮቻችን እና በላፕቶፕዎቻችን በየቀኑ የምንጠቀማቸው ብዙዎቹ አገልግሎቶች ነፃ ናቸው።ነገር ግን ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የተጠቃሚዎችን የግል መረጃዎች ትርፍ ለማግኘት ይጠቀሙበታል። ለመሆኑ ኩባንያዎቹ መረጃውን እንዴት ይሰበስባሉ? እንዴትስ ጥቅም ላይ ያውሉታል?  የመረጃ ግላዊነትንስ እንዴት መጠበቅ ይቻላል? በየቀኑ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኢንተርኔት/ በይነመረብ/ ይጠቀማሉ። ነገር ግን በይነመረብን፣ በበላይነት የሚመሩት ኩባንያዎች የበለጠ እየተጠቀሙባቸው ነው። በምንኖርበት የበይነመረብ ዓለም ውስጥ ጎግል ላይ በየቀኑ 8.5 ቢሊዮን የመረጃ ፍለጋዎች ይካሄዳሉ።በአሁኑ ወቅት ለብዙዎች  የህይወት አንድ አካል በሆኑት  የተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን እና በላፕቶፕዎቻችን ላይ በየቀኑ የምንጠቀማቸው ብዙዎቹ አገልግሎቶች ነፃ ናቸው።ነገር ግን በሌላ መንገድ የግል መረጃዎቻችንን በመስጠት ለኩባንያዎቹ  ዋጋ እንከፍላለን።
ሾሻና ዙቦት የተባሉ አሜሪካዊት «የስለላ ካፒታሊዝም ዘመን» /the age of surveillance capitalism / መጽሐፍ ደራሲ እንደሚሉት ኩባንያዎቹ የግለሰቦችን መረጃ የግል ንብረት ያደርጋሉ።
«ትልቁ እርምጃ የግል መረጃን በመንጠቅ ወደ ውሂብ መቀየር ብቻ ሳይሆን ፤እነዚያን መረጃዎች የኮርፖሬሽኑ የግል ንብረት አድርገው  ይጠቀሙባቸዋል ዋው! » በማለት ገልፀዋል።

ኩባንያዎቹ የግል ውሂብ እንዴት ይሰበስባሉ?

እንደጉግል፣ ሜታ፣ አማዞን እና ማይክሮሶፍትን የመሳሰሉ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች የተጠቃሚዎችን ውሂብ ለማግኘት የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ። ከነዚህም መካከል፤በቀጥታ ውሂብን በመጠየቅ፣በግዥ ወቅት የኤሜል አድራሻን በመቀበል፣አንድ እቃ ከተገዛ በኋላ ስለ ዕቃው ጥራት ስለ ኩባንያው አገልግሎት አሰጣጥ ወዘተ ግብረመልስ በመጠየቅ እና አገልግሎትን ለማሻሻል በሚል በዳሰሳ  ጥናት መልክ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን እንድንመልስ ማድረግ ይገኙበታል።.ሌላው የበይነመረብ እንቅስቃሴን በመከታተል ማለትም ተጠቃሚዎች የሚጎበኙትን ድረገፅ፣የሚከፍቷቸውን ሊንኮች ፣የሚጠቀሙትን ኢሜል በተደጋጋሚ የተመለከቷቸውን ይዘቶች ላይ ክትትል ማድረግን  ያጠቃልላል።በሌላ በኩል የተጠቃሚዎችን መረጃ  በቀጥታ ከመሰብሰብ ይልቅ መረጃ ለመሰብሰብ ጊዜውን እና ሀብቱን ከሰጠ ከሌላ ሶስተኛ ወገን  መረጃን ይገዛሉ።

የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ምን አይነት መረጃዎችን ይሰበስባሉ?

በዚህ ሁኔታ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ስማችንን፣ የኢሜል አድራሻን፣ ስልክ ቁጥርን፣ ዓለም አቀፍ መለያ/አይፒ/ አድራሻ፣ የምንጠቀምበትን የኤለክትሮኒክስ መሳሪያ፣ የተጠቀምንበትን ጊዜ፣ ምን እንደምንሰራ እና ሌሎችንም መረጃዎቻችን ከእኛ ይሰበስባሉ። ክትትትልም ያደርጋሉ። ይህ የሚሆነው ደግሞ  በበይነመረብ ግዥ ስንፈፅም፣የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ስንጠቀም፣በጎግል መረጃ ስንፈልግ  ወይም የተለያዩ ድረገጾችን ስንጎበኝ ሊሆን ይችላል። በዚህም እንደ ጉግል ያሉ ኩባንያዎች ከጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያነት እስከ ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር  የገቢ ኢምፓየር መፍጠር ችለዋል። 
ሾሻና ዙቦት ይህን መሰሉን ድርጊት ከዲሞክራሲ የሚፃረር የክትትል ካፒታሊዝም ይሉታል።
«ክትትል፣ ካፒታሊዝም ወይም ዲሞክራሲ። አንዱን ሊኖረን ወይም ሌላውን ልንይዘው እንችላለን። ሁለቱም ግን ሊኖረን አንችልም። በእነዚህ ሁለት ዓለማቀፋዊ መሪ ተቋማት መካከል ያለ መስማት የተሳናቸው ፍልሚያ ብየ እጠራዋለሁ።»ብለዋል።

የሰበሰቡትን መረጃ ለምን ዓላማ ያውሉታል ?

እነዚህ ኩባንያዎች የተጠቃሚዎችን ውሂብ  ከያዙ በኋላ የደንበኛ ፕሮፋይል በመገንባት እና ተጠቃሚው ማን እንደሆነ እና ምን እንደሚፈልግ የተሻለ ግንዛቤ ይኖራቸዋል። በዚህ መልኩ ከተጠቃሚዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ግላዊ በማድረግ ፤በተጠቃሚዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ማስታወቂያዎችን ይለቃሉ።የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መተግበሪያዎችም ተጠቃሚው ማየት የሚፈልገውን ይዘት ደጋግመው ያቀርባሉ።እንደ ቲክ ቶክ ያሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሱስ የሚያስይዙትም ለዚህ ነው። ምክንያቱም የሚነድፉት ስልተ ቀመር ከዚህ ቀደም በተመለከቱት  መሰረት አዲስ ይዘት  ማቅረብን ቅድሚያ ስለሰጡ ነው።.ለምሳሌ ለሆነ ጉዳይ የልደት ቀን በአንድ ገፅ ላይ ሲሞሉ ያንን መሰረት አድርገው ኢሜል ሊደርሰዎት ይችላል። በዚያ ኢሜይል የእርስዎን ስም ተጠቅመው መልካም ልደት ይመኙለዎታል። ይህንን የግል ኢሜል ሊልኩልዎ የሚችሉት ያንን ለማድረግ መረጃ ስላላቸው ነው።

ከተጠቃሚዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ግላዊ በማድረግ ፤በተጠቃሚዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ማስታወቂያዎችን ይለቃሉ ፤በተጠቃሚዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ማስታወቂያዎችን ይለቃሉምስል፦ Marcus Brandt/dpa/picture alliance

«የስለላ ካፒታሊዝም ዘመን» /the age of surveillance capitalism / መጽሐፍ ደራሲ ሾሻና ዙቦት ይህ የስለላ ካፒታሊዝም አዲስ የኢኮኖሚ ስልትን እንደሚወክል ያምናሉ።የዚህ አይነቱ የኢኮኖሚ አዝማሚያ  ጎግል ላይ በ1990ዎቹ መጨረሻ እና በ2000 መጀመሪያ ላይ እንደተጀመረ የሚናገሩት ፀሀፊዋ፤ ይህም የሰውን የዕለት ተዕለት የበይነመረብ እንቅስቃሴ እና የግል መረጃን እንደ ጥሬ እቃ ለንግድ አገልግሎት የሚያውል ነው ይላሉ።
ፀሀፊዋ እንደሚሉት ጉግል ስለሰዎች የወደፊት የበይነመረብ ባህሪ ለመተንበይ እና ከተጠቃሚዎች የይነመረብ ፍለጋ ያገኘውን መረጃ ለመጠቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ የተራቀቁ መንገዶችን አዳብሯል።
«የሰውን ባህሪ ለመተንበይ መረጃውን ለመተንተን ይጠቀሙበታል፣ እና ያን ነው የሚሸጡት። የእነሱ ታላቅ  የትንበያ ግኝት በበይነመረብ ላይ ያነጣጠረ ማስታወቂያ ለመጀመር  መነሻ ነበር።» ሲሉ ገልፀዋል።

የጎግል ወደ 80 በመቶ ገቢው ከማስታወቂያ የሚገኝ ነው

ጎግልን ከመረጃ ፍለጋ ባሻገር  እንደ ጎግል ማፕ፣ ጂሜይል እና ዩቲዩብን በመሳሰሉ እና  ሌሎች አገልግሎቶች ይታወቃል።ነገር የጎግል ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው ከፍተኛ ገቢ የሚገኘው በማስታወቂያ ነው።
ልክ እንደ ጎግል ፌስቡክም ከፍተኛውን ገቢ የሚያገኘው የተጠቃሚዎችን መረጃ በመጠቀም እነሱን ታሳቢ ያደረጉ ማስታወቂያዎችን በመስራት ነው። ሌሎች ብዙ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ መድረኮችም ይህንኑ ያደርጋሉ።ሜታ የዋትስአፕ እና ኢንስታግራም ባለቤት በመሆኑ ኩባንያው ከእነዚህ መተግበሪያዎች  መረጃ ወስዶ በፌስቡክ ላይ ለታለሙ ማስታወቂያዎች ሊጠቀምባቸው እንደሚችልም ባለሙያዎቹ ግምት አላቸው።
ያም ሆኖ የኩባንያዎቹ  የግላዊነት ፖሊሲ ፤የተጠቃሚውን መረጃ የሚሰበስቡት የተጠቃሚውን አጠቃላይ አገልግሎት ለማሻሻል መሆኑን ይገልፃል።ሾሻና ዙቦት ይህንን በብርቱ ይተቻሉ። «ስለዚህ ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም የሚገርመው ነገር፤ ግላዊነት ተብሎ መጠራቱ ነው። ይህ በጣም ጨካኝ አነጋገር ነው። ይህን የሚያደርጉት እኛን መለየት ስለሚፈልጉ እንጅ እኛን ለመርዳት ስለፈለጉ አይደለም። እነሱ የእኛን መረጃ ከእኛ ሊወስዱ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ህይወታችንን በማንኛውም ተጨባጭ መንገድ ለማሻሻል ሊጠቀሙበት አይደለም። በቀላሉ የሚፈልጉት  መለየት መቻል ነው፣ መረጃውን ለማውጣት ግምቶችን ለመፍጠር ፣ለመሸጥ ገቢን ለማመንጨት፣ ትርፍ ለማግኘት ነው። ይህ ነው የምንኖርበት አለም።»በማለት ገልፀዋል።

የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች የተጠቃሚውን መረጃ የሚሰበስቡት የተጠቃሚውን አጠቃላይ አገልግሎት ለማሻሻል መሆኑን ይገልፃሉ።ምስል፦ Dado Ruvic/REUTERS/Illustration

ጥቅማቸውን መካድ አይቻልም 

ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ እድገት ላስመዘገቡት ግዙፍ ለውጦች የምንከፍለው ዋጋ መረጃን ለኢኮኖሚ ጥቅም የማዋል ዘዴ አከራካሪ ነው።የቴክኖሎጅ ተንታኙ ቤኔዲክት ኢቫንስ ስለላ በሚለው ባይስማሙም የቴክኖሎጅ ኩባንያዎቹ የተጠቃሚን መረጃ እንደሚሰበስቡ ግን ያምናሉ። በአንፃሩ ደግሞ ጥቅማቸውን መካድ አይቻልም ይላሉ።  «የመገናኛ ዘዴዎች ችግር ይፈጥራሉ።እናውቃለን። ነገር ግን ቆም ብለህ ወደ ኋላ ማሰብ አለብህ፣ ከኒውዮርክ ወደ ጀርመን የአንድ ሰዓት የቪዲዮ ጥሪ ማድረግ መቻላችን በእውነት  መጥፎ ነገር ነውን? በእርግጥ ያ እንዲቀር እንፈልጋለን? ታውቃለህ፣ ይህ ጥሪ በ1980ዎቹ  200 ዶላር ያህል ዋጋ ያስከፍል ነበር። ያ የተሻለ ነበር ብለህ ታስባለህ?» ብለዋል።
 የአየርላንድ  የሲቪል ነፃነቶች ካውንስል በግላዊነት ጥሰት ላይ የሚያተኩር ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ውስብስብ እና አሳሳቢ በሆነው እና በይነመረብ ላይ ባነጣጠረ የማስታወቂያ ኢንዱስትሪ  ላይ ይፋ የሆነ ሪፖርት አውጥቷል።የድርጅቱ ባልደረባ ጆኒ ሪያን  እንደገለፁት ፤ተጠቃሚዎች እያንዳንዱን የንግድ ድረ-ገጽ በጎበኙ ቁጥር  ስለሚያነቡት  ነገር እና በገሃዱ አለም የት ቦታ  እንዳሉ ለብዙ  ኩባንያዎች መረጃ የሚልክ ስልት አላቸው። ይህንን የሚሰሩት ያለ ተጠቃሚው እውቅና ነው።

የውሂብ ግላዊነት ጥበቃ ህጎች

በግላዊነት መብት ጥሰት በፌስቡክ ላይ ለዓመታት በርካታ የህግ ዘመቻዎችን ሲያካሂድ ለቆየው ለኦስትሪያዊው ጠበቃ እና የግላዊነት ተሟጋች ማክስ ሽራምዝ ሁኔታው አስገራሚ ነው። «ምርት ከገዛህ እና ምርቱን  ለማድረስ አድራሻው ያስፈልግሃል። ያ ማለት ግን መረጃ ለሌላ ሰው መሸጥ ይችላሉ ማለት አይደለም። እና እኔን መከታተል እና ለእኔ ፕሮፋይል ለመስራት መሞከር እና ወዘተ እኔ እንደማስበው በእውነት አስገራሚ ነገር ነው።» በማለት ገልጿል። ባለሙያው እንደሚለው በማስታወቂያዎች ፣ወደ ተጠቃሚው ቀጥተኛ የጉግል ፍለጋዎች በሚወስዱ አገናኞች እና የተጠቃሚውን የግል መረጃ በአንድ ላይ በማጣመር መለያ /ፕሮፋይል/ በሚገነቡ ኩባንያዎች መካከል ልዩነት መፍጠር አስፈላጊ ነው ። 

የሜታ መድረኮች ፌስቡክን፣ ኢንስታግራምን እና ዋትስአፕን ይቆጣጠራሉ። በዓለም ላይ ካሉት ትልልቅ ማህበራዊ አውታረ መረቦች እና የመልእክት መላላኪያ መድረኮች መካከል ፌስቡክ  በበርካታ የውሂብ ግላዊነት ውዝግቦች ውስጥ ገብቷል። ባለፉት አመታት፣ ካምብሪጅ አናሊቲካ የተባለ የፖለቲካ አማካሪ ድርጅት ከ80 ሚሊየን በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን የግል መረጃ  እንዳገኘ እና ያንን መረጃ በ2016 የ«ብሪኢግዚት» ለሚባለው የብሪታንያ ህዝበ ውሳኔ እና በዚያው ዓመት ከተካሄደው ከአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት ለፖለቲካዊ ማስታወቂያዎች መጠቀም እንደቻለ ተረጋግጧል።
ኦስትሪያዊው የህግ ባለሙያ ማክስ  ሽራምዝ ፤ ካሊፎርኒያ ውስጥ ህግ ያጠና በነበረበት ወቅት፤ መረጃውን እንዲያሳየው ፌስቡክን በጠየቀ ጊዜ የገጠመውን ያስታውሳል። «ለምሳሌ፣ ከፌስቡክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ውሂቤን ሳገኝ፣ የተሰረዘ ውሂቤ አሁንም እንዳለ ለማየት ችያለሁ። ለምሳሌ እኔ ምንም አይነት የአካባቢ መረጃ ሳላጋራ የእኔን ጂኦግራፊያዊ አካባቢ ለማወቅ ሞክረው ነበር። እና ይህ በተለይ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪው ነገር ነው። ለምሳሌ ተጠቃሚዎች የመረጃቸውን ቅጂ የመጠየቅ መብት አላቸው። አሁን ግን፣ አብዛኛዎቹ እነዚህ ትልልቅ ኩባንያዎች ያንን አያከብሩም።  ተቆጣጣሪዎቹም እንዲሁ ወደ አገልግሎቶቻቸው አይገቡም በእውነቱ ከበስተጀርባ ያለውን ነገርም አይፈትሹም።» ብለዋል።
እንደ አፕል፣ አማዞን ፣ ማይክሮሶፍት ፣ጎግል እና ሜታ ያሉ ኩባንያዎች በየጊዜው የተነሱባቸውን ውዝግቦች  እና የፖለቲካ ጫናዎች ተከትሎ.የውሂብ ግላዊነት ተግባራቸውን ለዓመታት ቀይረዋል። እንደ አውሮፓ ህብረት ያሉ ተቋማት የተጠቃሚን  መረጃ ለመጠበቅ  ህጎችን አውጥተዋል።በጎርጎሪያኑ 2018 ዓ/ም ህብረቱ ያወጣው ጠቅላላ የውሂብ ጥበቃ ህግ /GDPR/ አንዱ ነው።

በኩኪስ  መረጃን ለመውሰድ ግልፅ ፈቃድ መጠየቅ 

ይህንን ተከትሎ፤ ኩባንያዎች  ይህ ሂደቱ የሚፈልገውን  ውሂብ ከመውሰዳቸው በፊት በኩኪስ አማካኝነት ግልፅ ፈቃድ ይጠይቃሉ።የውሂብ የግላዊነት ጠበቃ ጉሊያሞ ካውንሰን ግን ኩባንያዎቹ ይህንን ዘዴ እንደ ስልት ይጠቀማሉ ባይ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ድረ ገጾችን መጎብኘት ከቀጠልክ ፈቃድ እንደሰጠህ መቆጠሩም ወይም ለመጠቀም አስገዳጅ ሆኖ መቅረቡ ግላዊነትን የሚጋፋ ነው። በዚህ መንገድ ተራ ዜጎች መረጃቸው ጥቅም ላይ የሚውልባቸውን እጅግ ውስብስብ መንገዶች እንዲገነዘቡ መጠበቁ  ስህተት መሆኑን ገልፀዋል።የውሂብ የግላዊነት ጠበቃው ጉሊያሞ ካውንሰን።
አሜሪካዊቷ ፀሀፊ በበኩላቸው የዲጂታሉ ዓለም ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ይመኛሉ። ለዚህም ህግ አውጭዎች ሊተባበሩ ይገባል ይላሉ።
«የሕግ አውጭዎች በአንድ ላይ ተባብረው  ህግ እንዲቀርፁ መንገድ እንዲያሳዩ እንሻለን ። ስለዚህ ይህንን የምናደርገው ለእያንዳንዱ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ እና ዲሞክራሲያዊ ለመሆን እየታገለ ላለው ማህበረሰብ ሁሉ ነው።ምክንያቱም ያካልሆነ የሞት ዘርን ከእነዚህ የክትትል እና የቁጥጥር ኃይሎች ጋር እንዘራለን።» ብለዋል።

የግላዊነት ጥበቃ ባለሙያው ማክስ ሽራምዝ በበኩላቸው የሕግ ጫና እየጨመረ ሲሄድ በእነዚህ ኩባንያዎች  ላይ ለውጥ ሊመጣ ይችላል የሚል እምነት አላቸው። «እናም ቀስ በቀስ እነዚህን ኩባንያዎች እንደ ጀግና ወደማናይበት ሥርዓትየምንሸጋገር ይመስለኛል። ታውቃለህ፣ ሱከርበርግ፣ ወይም አንዳንድ የጉግል ስራ አስፈፃሚውች ልክ እንደ አዲስ መሲህ ይታያሉ። ነገር ግን እነሱም ስህተት የሚሰሩ ኩባንያዎች መሆናቸውን እንገነዘባለን። ትክክለኛ ቁጥጥር ያስፈልጋቸዋል፣ እኛም ያንን ማድረግ አለብን።» ብለዋል።

ልክ እንደ ጎግል ፌስቡክም ከፍተኛውን ገቢ የሚያገኘው የተጠቃሚዎችን መረጃ በመጠቀም እነሱን ታሳቢ ያደረጉ ማስታወቂያዎችን በመስራት ነው። ምስል፦ picture alliance / empics

የተጠቃሚዎች የግል መረጃ ጥበቃ 

ያም ሆኖ፤የቴክኖሎጅ ተንታኙ ቤኔዲክት ኢቫንስ በእያንዳንዱ የዕለት ተዕለት ህይወታችን ጣልቃ እየገባ ያለውን ውስብስብ  የቴክኖሎጅ አገልግሎት ልክ እንደ ሌሎቹ ዘርፎች ፖሊሲ እና ህግ በማውጣት ብቻ ውጤታማ ማድረግ እንደማይቻል ገልፀዋል።በመሆኑም በተጠቃሚዎች ዘንድ ግላዊ  መረጃን ለመጠበቅ ጠንካራ የይለፍ ቃል መጠቀም፣ባለብዙ ደረጃ ምስጠራን ማረጋገጥ፣አስፈላጊ መረጃዎችን መጠበቅ፣የበይነመረብ እንቅስቃሴዎችን በተጠና እና በጥንቃቄ ማድረግ፣ጠቃሚ የግል መረጃዎችን በዘፈቀደ በበይነመረብ ከማጋራት መቆጠብ፣የህዝብ  ዋይፋይ ከመጠቀም መቆጠብ ፣ የግላዊነት መመሪያዎችን በጥንቃቄ ማስተካከል በተለይ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መተግበሪያዎችን ስንጠቀም እንዲሁም የድጅታል እውቀትን ማሳደግ ግላዊ መረጃን ለመጠበቅ ከሚወሰዱ ርምጃዎች ጥቂቶቹ ናቸው።ከበይነመረብ የምንሰበስበውን እና የምናከማቸውን የውሂብ መገደብ።


ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ 

 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW