1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትኢትዮጵያ

የትምህርት ጥራት መፍትሄው እንዴት ይምጣ?

ሰኞ፣ መስከረም 6 2017

“የትምህርት ሚኒስቴርም መርዶ ነጋሪ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ብዙ ያልተፈተኑ ተማሪዎች አሉ፡፡ ደግሞም ከተፈተኑትም ከጸጥታ ስጋት ውጪ ሆነው የተፈተኑትና የተማሩት ብዙ አይደሉም፡፡ እናም ትምህርት ሚኒስቴር ከመርዶ ነጋሪነት ወጥቶ ወደ ተግባር መግባት አለበት፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋምስል Shewangizaw Wegayoh/DW

ተማሪዎች ምን አሉ?

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ተከታታይ ሶስት ዓመታት በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ላይ እየተመዘገበ ያለው ውጤት በርካቶችን አሳስቧል፡፡ አስደንጋጩ ውጤት የትምህርት ጥራት እና ተግዳሮቶቹ ላይ ብዙ ጥያቄ እንዲነሳም እያደረገ ነው፡፡  ተማሪዎች፣ መምህራን እና የስርኣተ ትምህርት ባለሙያዎችም ችግሩ መንስኤና እልባት ያሉት ላይ አስተያየታቸውን እስቀመጡ ነው፡፡
 

“ፈተናው ጥሩ ነው፡፡ እንደውም እየቀለለ የመጣ ነው የሚመስለኝ፡፡ ግን ችግሩ አሁን ተማሪዎች ሊያነቡት የሚጠበቅባቸው ከ9-12ኛ ክፍል ትምህርት ሰፋ ማለቱ ተስፋ የሚስቆርጣቸውና ስነልቦናዊ ችግሮች ያሉ ነው የሚመስለኝ”፤ በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከ600 ውስጥ 575 ነጥብ በማስመዝገብ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበችው ሲፌኔ ተክሉ ለዶይቼ ቬለ የሰጠችው አስተያየት ነው፡፡
ሌላው ለበርካታ ተማሪዎች ከተፈተኑት ውስጥ ግማሽ እንኳ ማሳካት አለመቻል ምክንያቱ ብዙ ሊሆን እንደሚችልም ሲፌኔ በአስተያየቷ ስትገልጽ “የትምህርት ጥራቱ ሁሉም ቦታ እኩል አለመሆን፤ አዲስ አበባ ላይ የተሻለ ትምህርት ቢሰጥም እሱም ከትምህርት ቤት ት/ቤት ይለያያል” ትላለች፡፡ ተማሪዎች በየትምህርት ቤቶቻቸው የሚያገኙት የትምህርት ቁሳቁስ ልዩነትም ሌላው ልዩነቱን የሚፈጥር ክፍተት ሊሆን እንደሚችል አንስታለች፡፡

የመምህራን ጭንቀት

በመምህርነት ሙያ የተሰማሩና አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የትምህርቱ ዘርፍ አንዱ ባለድረሻ በአስተያየታቸው እንደሚሉት ደግሞ ለትምህርት ዘርፍ የተሰጠው አነስተኛ ትኩረት በተለይም በታችኛው እርከን ባሉት መምህራን ብቃት ላይ የተሰራው ስራ ዝቅተኛ መሆን ለትምህርት ጥራቱ ውድቀት አይነተኛ ሚና ያለው ነው ይላሉ፡፡ “ለኔ እንደሚገባኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት መምህራን የትምህርት ጥራት አስኳል ናቸው” የሚሉት መምህሩ የትምህርት መሰረት ይዞ ሳይመጣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚገባን ተማሪ ፕሮፌሰሮች ሊረዱት አይችሉም ባይ ናቸው፡፡ ለመምህርነት የሚሰጥ ግምትና ትኩረትም ሊያሳስበን የሚገባው ቁልፉ ጉዳይ ሊሆን የሚገባበት ምክንያትም ይሄው ነው ብለዋል፡፡

ከ600 ውስጥ 575 ነጥብ በማስመዝገብ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበችው ሲፌኔ ተክሉ ምስል Seyoum Getu/DW

መፍትሄው እንዴት ይምጣ?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስርዓተ ትምህርት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሀምቢሳ ቀነዓ አሁን እየተመዘገበ ያለው ውጤት ከድሮው ምን ያህል ይለያል ብሎ ከመጠየቅ መጀመር ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት 10ኛ ክፍል ላይ የብሔራዊ ፈተና በመስጠት የተሻሉ ያሏቸውን ተማሪዎች ወደ መሰናዶ የማሳለፉ አማራጭ አሁን ላይ መቅረቱ ግን ለውጤቱ ማሽቆልቆል አንዱ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረም ያነሳሉ፡፡ “ውጤቱ አሳዛኝ ነው፡፡ ተማሪዎቻችን እየተማሩ እንዳልሆነ አስረጂ ነው፡፡ ግጭትና የግጭቱ ስጋት ደግሞ በተለይም ከአዲስ አበባ ውጪ ለትምህርቱ ጥራት መውደቅ ዋነኛ መንስኤ ሊሆን የሚችልበት እድል ሰፊ ነው” ያሉት ባለሙያው “የመምህራንም ህይወት ቆም ብሎ በማየት” እልባት መፈለግ ይሻል ባይ ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር ሀምቢሳ ቀነዓ የበርካታ ውስብስብ ጉዳዮች መንስኤ የፈተኑት የትምህርት ጥራቱ ከወዲሁ እልባት ወደ ሚሆኑ መፍትሄዎች መሻገር ካልተቻለ ሊብስ እንጂ ሊሻሻል የሚችልበት እድል አይኖረውምም ብለዋል፡፡ “የትምህርት ሚኒስቴርም መርዶ ነጋሪ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ብዙ ያልተፈተኑ ተማሪዎች አሉ፡፡ ደግሞም ከተፈተኑትም ከጸጥታ ስጋት ውጪ ሆነው የተፈተኑትና የተማሩት ብዙ አይደሉም፡፡ እናም ትምህርት ሚኒስቴር ከመርዶ ነጋሪነት ወጥቶ  ወደ ተግባር መግባት አለበት፡፡ የመምህራንን ህይወት ማሻሻል፣ ትምህርቱን ከየትኛውም ፖለቲካ ነጻ ማድረግ ከብዙ በጥቂቱ የሚታይ ነው” በማለትም ከሁሉ በላይ ግን በትምህርት መሰረተ ልማት የሚለያዩት የከተማ እና የገጠር አከባቢ ተማሪዎች መካከል እየተፈጠረ ያለው ልዩነት በብዙ እንዳሳሰባቸው አስረድተዋልም፡፡

ዘንድሮ ለተከታታይ ሶስት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን 50 በመቶ ውጤት ማምጣት ያቃታቸው ከ95 በመቶ ግድም በላይ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡    

ስዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ፀሐይ ጫኔ
  
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW