1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትራምፕ «ቅሌት»

ሰኞ፣ መጋቢት 25 2015

በአንድ የጎልፍ ዉድድር ወቅት ተወዳዳሪዎችን ለማስተዋወቅ ከጓደኞችዋ ጋር ወደ መጫዎቻዉ ሜዳ ገባች።እኛ ረጅም፣ደልዳላ፣ ፊተ ሰፊ ሰዉዬ አዩዋት።አላመነቱም።ከአጃቢዎቻቸዉ አንዱን ጠሩና «ይሕችን ልጅ ለዕራት ይጋብዝሻል በላት» አዘዙ።ያኔ የ60 ዓመት ሽማግሌ፣ቱጃር፣ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ነበሩ።ሁለተኛዋ ባለቤታቸዉ ደግሞ ድርስ እርጉዝ ነበሩ

USA | frühere US-Präsident Donald Trump veranstaltet eine Wahlkampfveranstaltung in Waco, Texas
ምስል Nathan Howard/AP Photo/picture alliance

የትራምፕ መከሰስ፣ የዳንየልስ ፅናት

This browser does not support the audio element.


በሕጻንነቷ ወላጆችዋ ተለያዩ።ከናቷ ጋር ቀረች።እናቷ ድሕነትም፣ራስ ወዳድነትም ስለሚጫጫናቸዉ «ብዙም አትንከባከበኝም ነበር።» ትላለች-ስቴፋኒ ኤ ግሪጎሮይ።«በዘጠኝ አመቴ በዕድሜ በጣም የሚበልጠኝ ሰዉዬ ደፈረኝ።» አለች። የሕይወቷ የጉዞ አቅጣጫም በዚሕ አጋጣሚ  ሳይቀየስ አልቀረም። ድሕነት፣ብቀላ፣እልሕም ተደማምረዉ በ17 ዓመቷ የመሸታ ቤት ራቁት ደናሽ ሆነች።ቀጠለችም። ወሲብ ቸርቻሪ ሆነች። ስሟንም ከሙያዋ ጋር እንዲጣጣም ለወጠች።ስቶርሚ ዳንዬልስ ብላ።ዕዉቅ የወሲብ ፊልም ተዋኝ፣ አዘጋጅ፣አከፋፋይም ወጣት። ኮኮብ። በ2006 ከኛ ቱጃር፣የቴሌቪዥን አዘጋጅ፣የኋላ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር እሷ እንደምትለዉ «አልጋ ላይ» ተወነች። ዘንድሮ ደግሞ የአሜሪካ ፍትሕ፣ የሐብትና የፖለቲካ ጡንቻ ግብ ግብ ኮኮብ ሆነች። የሦስቱ ትግል መነሻ፣ የሁለቱ ኮኮቦች ግንኙነት ማጣቃሻ፣ አስተምሕሮቱ መድረሻችን ነዉ።
                         
የጀርመን ስደተኛ የልጅ ልጅ ግን የናጠጠ ሐብታም ልጅ፣ የናጠጠ ሐብታም ናቸዉ።ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ፣ ፖለቲከኛ፣ ፕሬዝደንትም።
ክስ፣ ዉንጀላ፣የፍርድ ቤት ዉጣ ዉረድ ተለይቷቸዉ አያዉቅም።ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ አስተማሪ ዘልፈዉ፣ትንሽ ከፍ ሲሉ በጥፊ ተማትተዉ ተከሰዉ ነበር።በወጣትነታቸዉ ብሔራዊ ዉትድርና ለማምለጥ በተለይ ቬትናም ላለመዝመት ምክንያት ፈጥረሐል ተብለዉ ተከሰዉ ነበር።
በዕድሜም እየበሰሉ፣በሐብቱ አባታቸዉን እየተኩ እየበለጡም ሲሄዱ አንድ ጊዜ ግብር በማጭበርበር፣ ሌላ ጊዜ ያለ ፈቃድ በመነገድ፣ ሌላ ጊዜ ባንኮችን በማታለል ብዙ ጊዜ---ተከሰዉ ብዙ ጊዜ አሸንፈዉ ብዙ ጊዜ ተቀጥተዋል።
የፍርድ ቤቱ አሰልቺ ሙግት፣ የተፎካካሪ ነጋዴዎች፣ የተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ወቀሳ ሴራ፣የመገናኛ ዘዴዉ አጋጭ ዘገባና ትችት ግን ማድረግ የሚፈልጉትን ከማድረግ አላገዳቸዉም።
ለአሜሪካ -በጣሙን ለነጭ ዜጎችዋ የሚያደሉ፣ በወንድ የበላይነት የሚያምኑ፣የሰዎችን እኩልነት የሚንቁ አክራሪ ቀኝ ፅንፈኛ መሆናቸዉን ቃል-እርምጃ ድርጊታቸዉ ከሚሊዮን ጊዜ በላይ ገልፆታል።የአሜሪካ ሕዝብ ግን 45ኛዉ ፕሬዝደንቱ አድርጎ መረጣቸዉ።
 ጥር 2017 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) 4 ዓመት በቆየዉ የፕሬዝደንትነት ዘመነ-ስልጣናቸዉ ወቅት እንኳን በሐገሪቱ ምክር ቤት ሁለቴ ተከስሰዋል።የመጀመሪያዉን ነፃ ወጡ።ሁለተኛዉ ሒደቱ ሳይጋመስ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ አበቃ።በአሜሪካ ታሪክ አንድ ፕሬዝደንት ሁለቴ ሲከሰስ ትራምፕ የመጀመሪያዉ ናቸዉ።
ስልጣን ከለቀቁ በኋላም በ2020ዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለማሸነፍ የክፍለ-ግዛት መሪዎችንና አስመራጮችን አስፈራርተዋል-አንድ፣የአሜሪካ ምክር ቤት መቀመጫ ሕንፃን አስወርረዋል-ሁለት፣ሚስጥራዊ ሰነድ ደብቀዋል በሚል ወንጀል በብዙ አንቀፆች ተከስሰዋል።ግን በ2020ዉ ምርጫ «ተቀማሁ»  የሚሉትን ሥልጣን ዳግም ለመያዝ የምርጫ ዘመቻ ላይ ናቸዉ።«እኔን ለማጥቃት የሚረባረቡ» አሉ ከሰሞኑ የምረጡኝ ቅስቀሳቸዉ ባንዱ ለናንተ ስለምታገል ነዉ ግን አይችሉኝም» ቀጠሉ።  
                                     
«እንግዲሕ አሁን በይፋ የሶስተኛዉ ዓለም ሐገር ነን።እንዲሕ ዓይነት የጥቃት ዑደት ሲፈፀም ዝም ብሎ የሚመለከት ፕሬዝደንት በሐገራችን ታሪክ አጋጥሞን አያዉቅም።እነሱ የሚያዉቁት እኔን ማጥቃት ብቻ ነዉ።ምክንያቱም ለናንተ ስለምታገል ነዉ።በጣም ቀላል ነዉ።ሊገዙኝ አይችሉም።ሊቆጣጠሩኝ አይችሉም።ይሕ ከሚታመነዉ በላይ ያስፈራቸዋል።»
ዶናልድ ትራም በጣሙን ፍሎሪዳ ላይ ባነጣጠረዉ የምርጫ ዘመቻ፣ የገንዘብ መዋጮ፣ የደጋፊዎቻቸዉ ሰልፍ መሐል ከወደ ኒዮርክ የሚናፈሰዉን ዜና ሲሰሙ «ሊያስሩኝ ነዉ» ብለዉ ነበር።
በርግጥም ባለፈዉ ሳምንት ከወደ ኒዮርክ የተሰራጨዉ ዘገባ ለ76 ዓመቱ አዛዉንት «መጥፎ ዜና» ነዉ።ኒዮርክ ያስቻለዉ ታላቅ ሸንጎ ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሰረት የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ካንዲት ሴተኛ አዳሪ ጋር በመማገጥ፣ መማገጣቸዉ እንዲደበቅ ለሴትዮዋ ምናልባት ለምርጫ ዘመቻ ከሰበሰቡት ገንዘብ 130 ሺህ ዶላር በመክፈልና ሌሎችን በማታለል ወንጀል ተከስሰዋል።መጥፎ ግን ያደጉ-የኖሩበት የፍርድ ቤት እሰጥ አገባ።
ዶናልድ ትራም ነገ ኒዮርክ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበዉ የዕምነት ክሕደት ቃላቸዉን ይሰጣሉ።የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ፈፅሞታል በተባለ ወንጀል ተከስሶ ፍርድ ቤት ሲቀርብ፣ የፍርድ ቤት ጉዳይ ዘጋቢ ጋዜጠኛ ኤሪክ ታከር እንደሚለዉ በአሜሪካ ታሪክ ትራምፕ የመጀመሪያዉ ይሆናሉ።
«ይሕ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ልዩና ታሪካዊ ሳምንት ነዉ የሚሆነዉ።ምክንያቱም የቀድሞ ፕሬዝደንት ራሱ ሰራዉ ተብሎ በሚጠረጠር ወንጀል ተከስሶ ቃሉን ለመስጠት ከዳኛ ፊት ሲቀርብ የመጀመሪያዉ ይሆናልና።»
አሜሪካኖች ብዙ ታሪክ የላቸዉም፤ ግን «በታሪክ የመጀመሪያዉ፣ታሪካዊ፣ በአሜሪካ ታሪክ---» ማለት ይወዳሉ።ትራምፕ ደግሞ ሁሉንም ሳይወዱ አይቀሩም።ገንዘብ፣ ክብር፣ዝና፣ሥልጣን----ከሁሉም በላይ ግን ሁሉም የሚያደርገዉን ሁሉም የሚደብቀዉን በጣም ሳይወዱ አይቀርም።--ቅብጠት።
እንዲያዉ ልባቸዉ በቀላሉ «ፈሰስ ይላል« መሰለኝ እዚሕም እዚያም ካልጋ መዉደቅ «ይቀናቸዋል« ይባላል።እርግጥ ነዉ-ነገ ከተከሳሽ ሰንዱቅ ዉስጥ የሚከታቸዉን ወንጀል አልፈፀምኩም ባይ ናቸዉ።
ከቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝደንታቸዉ ማይክ ፔንስ፣ ማር ኤ ላ ጎ-ፍሎሪዳ አደባባይ እስከወጡት ደጋፊዎቻቸዉ፣ ከሪፐብሊካን የምክር ቤት እንደራሴዎች እስከ ጠበቃቸዉ፣ ቱጃሩ ፖለቲከኛ የተያዘባቸዉን የወንጀል ጭብጥ ፖለቲካዊ እንጂ አልፈፀሙም ባይ ናቸዉ።የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝደንት ማይክ ፔንስ 
                         
«እንደሚመስለኝ ለአብዛኛዉ አሜሪካዊ ይሕ ክስ አንድ አሜሪካዊን ፍርድ ቤት ለመገተር አበክረዉ በሚጥሩ በአንድ የማንሐተን ጠቅላይ አቃቤ ህግ የተቀነባበረ ፖለቲካዊ ክስ መሆኑ ግልፅ ነዉ።»
ከትራምፕ ደጋፊ ሰልፈኞች አንዷ «በተወዳጁ ፕሬዝደንታችን በዶናልድ ጄ ትራምፕ ላይ የሐሳት ክስ መመስረቱን አዉቀናል።እዚሕ የወጣነዉም ፕሬዝደንቱ የኛ ድጋፍ እንዳላቸዉ ልናሳያቸዉ ነዉ።እዉነቱን ለመናገር እንደኔ የሚያስቡ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ።»
ነገ ማንሐተን-ኒዮርክ በሚያስችለዉ ፍርድ ቤት ከትራምፕ ጎን የሚቆሙት ጠበቃቸዉ ጆ ታኮፒናም ክሱን «ፖለቲካዊ ዉንጀላ» ይሉታል።
« (ትራምፕ) ለፍልሚያዉ እየተዘጋጁ ነዉ።ይሕ እኛ እንደምናምነዉ የሆነ ፖለቲካዊ ዉንጀላ ነዉ።እንደሚመስለኝ ከመስሩ ግራ ቀኝ ያሉ ሰዎች በሙሉ ክሱ የተመሰረተዉ ስልጣንን አለአግባብ በመጠቀም እንደሆነ ያምናሉ።»
ትራምፕን በቅርብ የሚያዉቁ ግን ጥቅም ያልተጋሩ የሕግ  አዋቂዎች ፣የዴሞክራቲክ ፓርቲ እንደራሴዎች፣ የሩቅ ታዛቢዎች ከሁሉም በላይ የወሲብ ኮኮቧ  ስቶርሚ ዳንዬልስ ትራምፕ የሚክድቱን አድርገዋል ባዮች ናቸዉ።
ዶናልድ ትራም የፕሬዝደንትነቱን ስልጣን ከያዙ በኋላ ብዙ ሴቶች አንሶላ ተጋፈናል እያሉ በእዉነትም በሐሰትም አጋልጠዋቸዋል።ይህቺኛዋ ግን «አኞ» ነዉ-የሆነችባቸዉ።በምርጫዉ ዘመቻ ወቅት ሚስጥሩን እንዳታወጣ ትራምፕ ያዘዙትን 130 ሺሕ ዶላር  ለሴተኛ አዳሪዋ ያዘዋዋረዉ የቀድሞ ጠበቃቸዉ ማይክል ኮኸን በ2018፣ የ3 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።
ኮሕን ላይ ካስፈረደዉ ወንጀል አንዱ ለዳንዬልስ ገንዘብ ማስተላለፋቸዉ ነዉ።ትራም በገንዘብ የቀበሩት የወሲብና የገንዘብ ማዘዋወር ቅሌትም የጫነዉን ምርጊት እየሸራረፈ መዉጣት የጀመረዉ ኮሕን  በ2018 ከታሰሩ በኋላ ነበር።ዳኒየልስ የዚያን ቀን «ሴት፣ ከሴትም የኔ ብጤ ሴት ዋጋ  እንዳላት ተረጋገጠ» ብላ ነበር።
«ሰላም ሁላችሁም።ለዓመታት ኮሕን ከሕግ በላይ እንደሆነ ሲንቀሳቀስ ነበር።እራሱን የትራምፕ ጉዳይ አስፈፃሚ አድርጎ የሚቆጥር፣ እንደሆነም በግልፅ የሚናገርም ነበር።በተለያዩ የመጫዎቻ ሕግጋት ተጫዉቷል ነዉ---ወይስ ህግም የለም እንበል።አንድ ትንሽ ሰዉ ወይም በተለይ ሴት፣ ከሴትም የኔ ብጤ ሴት ዋጋ አላት ብሎ አያዉቅም ነበር።ዛሬ ግን ይኽ አበቃ።»
ዳንየልስ እንደምትለዉ ነገሩ የሆነዉ በ2006 ነዉ።የ27 ዓመት ወጣት ነበረች።ቀጠን፣ መለል፣ ቀልጠፍ፣ ያለች። በዚያ ላይ  በአለባበስ፣ አካሔድ-አረማመድ-ፈገግታ ሰለቦቻን በቃላሉ መጣል የተካነች ወጣት።
በአንድ የጎልፍ ዉድድር ወቅት ተወዳዳሪዎችን ለማስተዋወቅ ከጓደኞችዋ ጋር ወደ መጫዎቻዉ ሜዳ ገባች።እኛ ረጅም፣ደልዳላ፣ ፊተ ሰፊ ሰዉዬ አዩዋት።አላመነቱም።ከአጃቢዎቻቸዉ አንዱን ጠሩና «ይሕችን ልጅ ለዕራት ይጋብዝሻል በላት» አዘዙ።ያኔ የ60 ዓመት ሽማግሌ፣ ቱጃር፣ ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ነበሩ። ሁለተኛዋ ባለቤታቸዉ ደግሞ ድርስ እርጉዝ ነበሩ።
«ትልቅ ክፍሉ ስገባ የሌሊት ልብስ (ፒጃማ) ለብሶ ጠበቀኝ።» አለች በ2018 ።ከዚያ በኋላ «ልክ ልጄን ትመስያለሽ--- እያለኝ----» እያለች  የዚያች ቀን ከወደፊቱ ፕሬዝደንት ጋር ያደረገችዉን የአልጋ ላይ ጨዋታ «በሕይወቴ ካደረጉት ወሲብ ሁሉ በጣም ቀዝቃዛዉ» እያለች ታወጋለች። እዉነት  ይሆን?

በ2018 የታሰሩት ማይክል ኮሕን፣ የቀድሞዉ የትራምፕ ጠበቃምስል Siegfried Anthony/STAR MAX/picture alliance
የትራምፕ ደጋፊዎች ሰልፍ ምስል Go Nakamura/REUTERS
የትራምፕ ተቃዋሚዎችምስል David Dee Delgado/REUTERS
ምስል Go Nakamura/REUTERS
ስቶርሚ ዳንየልስ፣ ከትራምፕ ጋር ተኝቻለሁ ባይዋ የወሲብ ፊልም ኮኮብምስል SMG/ZUMA Wire/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW