የትራምፕ የስደተኞች ጉዳይ የፍርድ ቤት ክርክር
ማክሰኞ፣ መጋቢት 16 2017
የትራምፕ አስተዳደር በጦርነት ወቅት ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል የጠላት ሀገር ዜጎችን የማሰርና ወደ ሀገራቸው የመመለስን ሕግ ስደተኞችን ከሀገር ማስወጣቱ ከፍተኛ የሕግ እሰጣ ገባ ውስጥ ከቶታል። በዚሁ ጉዳይ የተከሰሰው አስተዳደሩ ጉዳዩን በያዙት ዳኞች ስደተኞቹ ተገቢውን ፍትህ አለማግኘታቸውና አዋጁ ጥቅም ላይ የዋለው በሰላም ወቅት መሆኑን ከጥያቄ ውስጥ አስገብተውታል። የትራምፕ አስተዳደር ጉዳዩ ገና ውሳኔ ሳያገኝ ወደ ይግባኝ ሰሚ ችሎት መውሰዱና ለፍርድ ቤት ውሳኔዎችም ያለመገዛት ሁኔታዎችን ማሳየቱ የተገለጸ ሲሆን የሕገመንግሥት ቀውስ ሊያስከትል የሚችል ፍጥጫን ሊፈጥር እንደሚችልም ተነግሯል። ከዋሽንግተን ዲሲ አበበ ፈለቀ ዝርዝሩን ልኮልናል
ዶናልድ ትራምፕ ሰሞኑን የደቡብ አሜሪካ ዜጎችን ከሀገር ለማስወጣት የተጠቀሙበት የቆየና ብዙም ጥቅም ላይ ያልዋለ ሕግ ከተቃውሞ አልፎ አስተዳደሩን የፍርድ ቤት እሰጣ ገባ ውስጥ ጨምሮታል። (Alien Enemies Act ) በግርድፉ፤ የመጤ ጠላቶች ሕግ በ1798 ዓ.ም. የወጣ ሲሆን አሜሪካ ጦርነት ሲታወጅባት፣ ወይም ስታውጅ የዛ ሀገር ተወላጆች የሆኑና አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን፣ በስለላም ሆነ በሌሎች ሀገር በሚጎዱ ተግባራት እንዳይሰማሩ፣ ለማሰር ወይም ለማባረር እንዲችሉ ሥልጣን የሚሰጥ ሕግ ነው። ይሄው ሕግ ከዚህ ቀደም አሜሪካ ባካሄደቻቸው ጦርነቶች ላይ በተወሰነ ደረጃ ጥቅም ላይ እንደዋለ ያነጋገርኳቸው መቀመጫቸውን ሲአትል ዋሽንግተን ያደረጉት፣ የሕግ ባለሞያና ጠበቃ ቃለአብ ካሣዬ ይናገራሉ።
ከዚህ ባለፈ ግን ሀገር ሰላም በሆነበት ጊዜ፣ እንዲህ ላለ መጠነሰፊ ዘመቻ እንደምክንያት ሆኖ አያውቅም። ዶናልድ ትራምፕ፣ ገና ከምረጡኝ ቅስቀሳቸው ጀምሮ የደቡቡ የአሜሪካ ድንበር ክፍት እንደሆነና ከስደተኞች ጋር በተያያ «ሀገራችን ጦርነት ላይ ናት» የሚል ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነው የከረሙት። ሰሞኑንም ይሄንኑ ሕግ በመጠቀምና በማወጅ «የቬንዝዌላ ወሮበላ ቡድን አባላት ናቸው» ያሏቸውን ሰዎች በጅምላ እያፈሱ ኤልሳልቫዶር ወደሚገኝ እስር ቤት ወስደው አጉረዋቸዋል። ይሄ ሕግ ተፈጻሚ ሲሆን በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ፣ ያውም ሕጉ እንደቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው የታወጀ ጦርነት ሳይኖር መሆኑ ነው። ይሄው ተግባር ከሕግም፣ ከግብረገብም፣ ከሰብዓዊነትም አንጻር ያልተዋጠላቸው ቡድኖች በትራምፕ አስተዳደር ላይ ክስ መስርተው ነው የፍርድ ቤቱ ፍጥጫ የተጀመረው። የሕግ ባለሞያው ቃለአብ ካሣዬ የትራምፕ አስተዳደር ጠንካራ የሚባል የመከራከርያ መሠረት ባይኖረውም የፍርድ ቤቱን ትዕዛዛት ተፈጻሚ ያለማድረግን መንገድ የተከተለበት ሁኔታም እንዳለ ገልጸዋል።
ጉዳዩ አሁንም በመጀመሪያ ደረጃም ሆነ በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች እየታየ ነው። የክስ ጭብጡ ምንም ይሁን ምን ጉዳዩን የሚያዩት ዳኞች የሕግ ፍልስፍናና ፖለቲካዊ ምልከታ የራሱ ተጽዕኖ አለው። ከይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ዳኞች ውስጥ አንዱ በኦባማ የተሾሙ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ በራሳቸው በፕሬዝዳንት ትራምፕ እና በጆርጅ ቡሽ የተሾሙ ናቸው። ውሳኔው ምንም ይሁን ምን ጉዳዩ በዚህ የሚያበቃ አይመስልም። ምርጫም ይሁን የፍርድ ቤት ውሳኔ እሳቸው እንደፈለጉት ካልሆነ ልክ አይደለም ብለው የሚያስቡት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደግሞ፣ እንዲህ በቀላሉ ነገሩን የሚተዉ ዓይነት አይደሉም።
እናም በአሜሪካ ፖለቲከኞችም ሆነ በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ የሚነሳው አንድ ስጋት ፍርድቤት ያዘዘውን አስተዳደሩ አልፈጽም ቢል መላው ምንድነው የሚል ነው። በተለምዶ እንዲህ ያለ ክስተት የሕገመንግሥት ቀውስ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ጉዳዩ እልባት የሚያገኝበት ብቸኛ መንገድም የሀገሪቷ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔና በሁሉም ሀገሪቷ የአስተዳደር ቅርንጫፎች አዎንታዊ ምላሽ እንደሆነ የሕግ ባለሞያና ጠበቃው ቃለአብ ካሣዬ ጠቁመዋል።
ቀጣዮቹ ሕጋዊ እርምጃዎች አሁንም ወዴት እንደሚያመሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። የእስራቱና ተጠርዞ የመመለሱ ዒላማ የሆኑ ግለሰቦች ከተጠቀሰው የወንበዴው ቡድን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ጨምሮ፣ ተጨማሪ እውነታዎች የመጡ እንደሆነ ግን ሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ውጥረቱ እየከረረ መሄዱ አይቀሬ ነው።
የትራምፕ፣ የስደተኞች ጉዳይ እና የፍርድ ቤቱ እሰጣ ገባ፣ በአስፈጻሚውና በፍትህ አካላቱ መሃከል ያለው የሥልጣን ሚዛንና የአሜሪካ የዲሞክራሲ ሥርዓትም እንዲህ ያሉ ያልተለመዱ ፍትጊያወችን ተሸክመው፣ ሳይዛቡና ሳይሰበሩ ማለፍ መቻል አለመቻላቸውን ከሚያሳዩ ፈተናዎች ውስጥ አንዱ መሆኑ ግን እውን ነው።
አበበ ፈለቀ
ሸዋዬ ለገሠ
ፀሐይ ጫኔ