1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ወቅታዊ መግለጫ

ሥዩም ጌቱ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 20 2018

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ለሚያዚያ 30 ቀን፣ 2018 ዓ.ም. በተናጥል በ10 ከተሞች ጠርቶ የነበረውን የአደባባይ ሰልፍ መሰረዙን ዐሳወቀ፡፡ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነትን ከመሰረቱ አራት የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ኢሕአፓ ሰልፉ እንደትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ቅንጅት ወደፊት ቀኑ ተለይቶ እንደሚጠራም ነው ያሳወቀው፡፡

የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት መለያ አርማ
የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት መለያ አርማምስል፦ Coalition for Ethiopian Unity

የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የምርጫ ተሳትፎ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ለሚያዚያ 30 ቀን፣ 2018 ዓ.ም. በተናጥል በ10 ከተሞች ጠርቶ የነበረውን የአደባባይ ሰልፍ መሰረዙን ዐሳወቀ፡፡ ትብብር ለኢትዮጵያ  አንድነትን ከመሰረቱ አራት የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ኢሕአፓ ሰልፉ እንደትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ቅንጅት ወደፊት ቀኑ ተለይቶ እንደሚጠራም ነው ያሳወቀው፡፡ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ እንደሚገኝ ሰኞ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ያሳወቀው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ለፊታችን ቅዳሜ ሚያዚያ 24 ቀን፣ 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ "ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ” ጠርቷልም፡፡ 

የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የምርጫ ተሳትፎ

የአራት የፖለቲካ ድርጅቶች ቅንጅት የሆነው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ትናንት ሰኞ ሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣው ይፋዊ መግለጫ፤ አገርና ሕዝብ ገብተውበታል ያለው የሕልውና አደጋ እንዲቀለበስ፤ መንግሥት ትልቁን ድርሻ ወስዶ፣ የፖለቲካ ልኂቃንም ጎራ ለይቶ ከመሳሳብ ወጥተው የአገር መፍረስ አደጋን ለመታደግ የድርሻቸውን እንዲወጡ ብሏል። "አገር ባለችበት ምስቅልቅል” በምርጫ ውስጥ መሳተፍ ያለው ጉዳትና ጥቅሙን መዝነን ውስጥ ኾኖ መታገል ይሻላል የሚለው ሀሳብ በማመዘኑ "ተሳትፏችን ያለንበት ላይ ደርሷል” ያለው ትብብሩ፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነጻነትን በነጻ ለማግኘት ከመሻት ይልቅ ለወል ነጻነት ባለው ሕጋዊ ማኅቀፍ እንዲታገል ብሏልም።

በመግለጫው ላይ ተጨማሪ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ያጋሩት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ፕሬዝዳንት እና የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ምክትል ፕሬዝዳንት መጋበ-ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት፤ "በአፋር ክልል ላይ ከዚህ በፊት ያስመዘገብናቸው እጩዎች ተለያዩ ችግሮች ስላጋጠማቸው” ሙሉ በሙሉ እራሳቸውን በማግለላቸው አፋር ላይ በምርጫ ፉክክሩ ተሳትፎ እንደሌላቸው፤ በትግራይ ክልል ደግሞ ምን እጩ አለማስመዝገባቸውን በመግለጽ፤ ነገር ግን በአማራ ክልል ከዚህም በፊት እንደተገለጸው አደባባይ የምርጫ ቅስቀሳ በመግታት በሂደቱ ላይ ግን መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ፖለቲከኛው በሌሎች ክልሎች ግን እጩም አስመዝግበው "ከነችግሮቹም ቢሆን” በምርጫው ፉክክር ላይ ተሳትፎ እንደሚኖራቸው አስረድተዋል፡፡

የትብብሩ ጥያቄዎች እና የምርጫ አስቻይነት

ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት እንደ ከዚህ ቀደሙ መግለጫዎቹ ገዢው የብልጽግና ፓርቲ (መንግሥት) ከታጠቁ ኃይሎች እና ከፖለቲካ ልኂቃን ጋር እንዲደራደር አንዲሁም እሥረኞች እንዲፈቱና የሕዝቡ እውነተኛ ሮሮ እንዲሰሙ ውትወታ እያደረግን ነው ብሏል። ይህንኑን መነሻ በማድረግም የሰላማዊና ሕገ መንግሥታዊ  ትግል አማራጭ መንገዶችን አጠናክሮ እንደሚገፋበት ቅንጅቱ አስታውቋልም፡፡ የትብብሩ ምክትል ፕሬዝዳንት እንዳሉትም፤ "የሰላማዊ ትግላችንን አጠናክረን የምንቀጥለው ለዚህ ነው፡፡ ምርጫውም ምርጫ እንዲባልና አስቻይ ሁኔታ እንዲሟላ ስለምንሻ ጥያቄዎቻችን በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ሰላማዊ ትግል አማራጭ ህጋዊ በሆነ መንገድ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” በማለት ምንም እንኳ አስቻይ ሁኔታ ባይኖሩም በምርጫው ሂደት ውስጥ እንገኛለን ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አርማምስል፦ Ethiopian National Election Board

ትብብሩ የጠራው ሕዝባዊ ውይይት

ተከታታይ የሕዝባዊ ውይይት መርሃግብሮችን ማዘጋጀቱን በዚሁ መግለጫው የጠቆመው አራት የፖለቲካ ድርጅቶች ቅንጅቱ፤ "ከህዝብ ጋር እንወያያለን” ሲል የፊታችን ቅዳሜ ሚያዚያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ሕዝባዊ ውይይ በአዲስ አበባ መጥራቱን አስታውቋል። መሰል የህዝባዊ የውይይት መድረኮች አዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ ክፍለከተሞች እና በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎችም እንደሚቀትሉ ነው የተጠቆመው፡፡ ትብብሩ የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ "ታላቅ የአዳራሽ ውስጥ ስብሰባ” ያለውን መድረክ ሲያካህድ ከሕዝቡ ጋር ተቀራርቦ በመምከር በምርጫው አስቻይ ያለው ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ፤ ነጻ የፕሬስ አውድ እንዲኖር እና "እስረኞች እንዲፈቱ” በጋራ እንታገላለን ነው ያለው።

ኢሕአፓ ከዚህ በፊት የጠራው ሰልፍ መሰረዙ

በመጭዎቹ ጊዜያት በዋናነት በአዲስ አበባ እና "የተሻለ ፀጥታ አለባቸው” በሚባሉ አካባቢዎች ታላቅ ሕዝባዊ ሰልፍ እንደሚያካሄድም ትብብሩ አሳውቋል። የትብብሩ አባል ፓርቲ የኾነው ኢሕአፓ ለሚያዝያ 30 ቀን ጠርቶት የነበረው ሰልፍም በአዲስ መልኩ በዚኹ በትብብሩ ማዕቀፍ የሚከናወን እንደሚሆን ተነግሯል። የቅንጅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት መጋበ-ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት በዚህም ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀው፤ "ኢሕአፓ ፍላጎት የኛም ፍላጎት ነው በሚል ትብብር አባል ፓርቲዎች ጋር ከተወያየን በኋላ በስምምነት ኢሕአፓ ለሚያዚያ 30 የጠራው ሰልፍ በተሻለ መልኩ ለማድረግና ከቅንጅቱ ጋር አብሮ ለመጓዝ ወደፊት ይፋ ለሚሆን ጊዜ ሰልፍ ጠርተናል” በማለት የፊታችን ቅዳሜ አዲስ አበባ ቸርችል ጎዳና በሚገኘው የመኢአድ ጽ/ቤት ህዝባዊ ስብሰባ መጠራቱን አስረድተዋል፡፡ ትብብሩ ምርጫን አብሮ ለማሸነፍ እንደሚሰራ እና ትግሉንም በጋራ እንደሚያደርግም እንዲሁ ገልጸዋል፡፡

ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት በህዝባዊ ውይይት መድረኩ ሌሎች ፓርቲዎችና ልኂቃን እንዲሳተፉ በጠየቀበት በመግለጫው፤ የመንግሥት መዋቅር በተለይ የፀጥታ ኃይሎች ሕገ መንግሥታዊ መብት ያለውን ጥረቱ በቀናነት እንዲያግዙ ጠይቋልም።#ምርጫ2018 #EthiopiaElection2026

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW