1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትኒሺቱ ሐገር ትልቅ ተፅዕኖ

ሰኞ፣ ሰኔ 6 2014

የመንን ከሐገርነት ወደ ትንቢያ የቀየረዉ ጦርነት ባይለኩሱት ያጋጋሙት አንድም ሳዑዲ አረቢያ ሁለትም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ናቸዉ።የሱዳን ፖለቲካዊ ቀዉስ ስሩ ካርቱም ሊሆን ይችላል።ሰበብ ምክንያት ቅርንጫፉ ግን ካይሮን፣ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ ሪያድና አቡዳቢ ላይ ደርሷል ። በኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት፣ በጅቡቲና ኤርትራ....

VAE | Besuch türkischer Präsident Recep Tayyip Erdogan
ምስል DHA

የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ሐብትና ተፅዕኖ

This browser does not support the audio element.

 

ሐምሌ 1969 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የያኔዉ የአቡዳቢ ገዢ ብሪታንያን ለመጎብኘት ሲዘጋጁ፣ ለንደኖችን ያሳሰበዉ ብዙ የማትታወቀዉ ትንሽ ሐገር፣ የማይታወቅ መሪ ሥም የሚፃፍበት ፊደል (ስፔሊንግ) ነበር። ጄምስ ሌንግተን እንደፃፈዉ ለንደኖች ዛይድ ወይስ ዛየድ፣ አል ንሕያን ወይስ አል ናያሐን እያሉ ፊዳላት ሲያማርጡ ሰዉዬዉ ለንደን ገቡ።ሼኽ ዛየድ ቢን ሱልጣን አል ናሕያን ለንደንን በጎበኙ በ3ኛዉ ዓመት የመሠረቷት የሰባት ትናንሽ ኤሚሬቶች ስብሰብ ዛሬም በርግጥ ትንሽ ናት።67 ሺሕ 340 ስኩየር ኪሎ ሜትር።10 ሚሊዮን ከሚጠጋዉ ዜጋዋ የሐገሬዉ አንጡራ ተወላጅ 1.5 ሚሊዮን ቢገመት ነዉ።ሐብቷ ግን ከብዙ ሰፋፊ፣ ጥንታዊ ሐገራት አስበልጧት ከመካከለኛዉ ምስራቅና ከአፍሪቃ ዘዋሪዎች አንዷ አድርጓታል።ከኃያላኑ ጎራ ለመሰለፍም እያንጠራራት ነዉ። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች።በዓለም በጣሙን በአፍሪቃ ቀንድ ያላትን ተፅዕኖ ባጭሩ አንቃኛለን።                                      

አጥኚዎች እንደሚሉት የግብፅ ሕዝባዊ አመፅ የፈነጠቀዉን የዴሞክራሲ ብልጫታን የሐገሪቱ የጦር ጄኔራሎች በቀላሉ ያዳፈኑት በምዕራቦች ድጋፍ፣በሪያድና አቡዳቢ ገንዘብ ብርታት ነዉ።የሶሪያ የርስበርስ ጦርነት ሚሊዮኖችን የፈጀዉ ከሪያድ፣ከዶሐና ከአቡዳቢ በሚንዠቀዘዉ ዶላር ነዉ።ራሳቸዉን ሲሻቸዉ ጄኔራል ሲያስፈልጋቸዉ ማርሻል የሚሉት የሊቢያ የጦር አበጋዝ ለሸምጋይ፣አማላጅ አልበገርም ያሉት በአብዛኛዉ አቡዳቢዎች በሚያስታቅፏቸዉ ገንዘብ፣ በሚያስታጥቋቸዉ ጦር መሳሪያ ታብየዉ ነዉ።

ምስል Xinhua/WAM/Photoshot/picture alliance

የመንን ከሐገርነት ወደ ትንቢያ የቀየረዉ ጦርነት ባይለኩሱት ያጋጋሙት አንድም ሳዑዲ አረቢያ ሁለትም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ናቸዉ።የሱዳን ፖለቲካዊ ቀዉስ ስሩ ካርቱም ሊሆን ይችላል።ሰበብ ምክንያት ቅርንጫፉ ግን ካይሮን፣ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ ሪያድና አቡዳቢ ላይ ደርሷል ። በኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት፣ በጅቡቲና ኤርትራ ዉዝግብ፣ በሶማሊያ ፖለቲካዊ ሽኩቻም እጃቸዉ አለበት።

የፖለቲካ ተንታኝ የሱፍ ያሲን እንደሚሉት ሳዑዲ አረቢያ እንደ አዉራ የምትመራቸዉ የባሕረ ሰላጤዉ አካባቢ የአረብ ሐገራት በየስፍራዉ ጣልቃ ሲገቡ እርስበርሳቸዉ እስከ መጋጨትም ይደርሳሉ።                                      

የቀድሞዉ የሶማሊያ ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ (ፎርማጆ-በቅፅሉ) የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን የያዙት «የባሕረ ሰላጤዉ ቀዉስ» የሚባለዉ የቀጠርና ሳዑዲ አረቢያ የምትመራቸዉ ሐገራት ጠብ በናረበት፣ የየመኑ ጦርነት በጋመበት ወቅት ነበር።የካቲት 2017።መሐመድ አብዱላሒ ራሳቸዉም እሳቸዉን የመረጠዉ ምክር ቤትም ጠበኞቹ ድጋፍ ለማሰባሰብ ከሚያደርጉት ሽሚያ አላመለጡም።

ተሻሚዎቹ የካቲት ላይ እስከሳረገዉ ምርጫ ድረስ በነበረዉ ፉክክር ከ12 ሚሊዮን ዶላር በላይ አፍስሰዋል።ዘገቦች እንደጠቆሙት ፕሬዝደንቱ ከቀጠር መወገናቸዉ ሲነገር አብዛኞቹ የምክር ቤት አባላት፣ የክፍለ ግዛት መሪዎችና ለፕሬዝደትነት የተወዳደሩት  ዕጩዎች የሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ደጋፊዎች ወይም ተከፋዮች ነበሩ።

ልዩ የበረራ መስመር የተሰጠዉ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አዉሮፕላን ሞቃዲሾ አዉሮላን ማረፊያ ያረፈዉ ቀጠሮች በመሐመድ አብዱላሒ በኩል ቪላ ሞቃዲሾን በተቆጣጠሩ ባመቱ ነበር።ሚያዚያ 2018።የአዉሮፕላኑ ተሳፋሪዎች ዕቃ ሲፈተሽ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ጥሬ ገዘብ የታጨቀበት ቦርሳ ተገኘ።የአቡዳቢ ደጋፊዎች ገንዘቡ የሶማሊያ የፀጥታ ኃይላትን ለማሰልጠን መላኩን አስታዉቀዉ ነበር።

ምስል Mikhail Metzel/TASS/picture alliance

ይሁንና በስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት ሳያቀዉ የሚሰለጥን ፀጥታ አስከባሪ፣ የሚላክ ገንዘብ ያዉም በጥሬዉ ሞቃዲሾ መግባቱ የአቡዳቢ ደጋፊዎች የሰጡትን ምክንያት ባዶነት ለማረጋገጥ ለሚሹት ወገኖች ሌላ መረጃ መጥቀስ አላስፈለጋቸዉም።ገንዘቡ ተቃዋሚዎቼን ለማደራጀት የተላከ ነዉ ያለዉ የመሐመድ አብዱላሒ መሐመድ መንግስት  ወረሰዉ።

ተደጋጋሚ ግጭት፣ድሕነት፣ ሸፍጥ ተለዋዋጭ ወዳጀት፣ ጠላትነትና ሽኩቻ የዘመኑ ፖለቲካዉ ይትበሐል ያደረገዉ የአፍሪቃ ቀንድ ኢትዮጵያ ላይ በተደረገዉ የመንግስት ለዉጥ፣ በአዲስ አበባና አስመሮች አዲስ ፍቅር፣ በኬንያና በሶማሌ ጠብ፣ በጅቡቲና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዉዝግብ፣በጁቡቲና በኤርትራ ቂም ማመርቀዝ ወዘተ ሲዋከብ የ10 ሚሊዮና ዶላር የጫረችዉ ወሬና አሉባልታ ተዘንግቶ፣ በ4ኛ ዓመቱ ዘንድሮ  መሐመድ አብዲላሒ መሐመድ በምርጫ ተሸንፈዉ ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ የፕሬዝደንትነቱን ስልጣን ያዙ።

ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ ባለፈዉ ሳምንት በዓለ ሲመታቸዉን ሲያከብሩ ከኬንያ፣ ከጁቡቲና ከኢትዮጵያ መሪዎች ቀጥሎ ከተጋበዙት ትላልቅ እንግዶች የሳዑዲ አረቢያ፣የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና የግብፅ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ደኤታዎች ዋናዎቹ ነበሩ።ቀጠር አንድም አልተጋበዘችም አለያም የተወከለችዉ  በዝቅተኛ ባለስልጣን ነዉ።አዲሱ ፕሬዝደንትም እንተባበር አሉ።

«ከተቀረዉ ዓለም ጋር በፀጥታ ጉዳይ መተባበር አለብን።በተለይ አሸባብንና ደአሽን (ISIS)ን የመሳሰሉ አሸባሪ ቡድናት የሚመነጭ የፀጥታ መታወክ ፈተና ከሆነባቸዉ ከአፍሪቃ ቀንድ ሐገራት ጋር ይበልጥ መተባበር አለብን።»

ፕሬዝደንቱ ዓለም ያወገዘዉን፣ የቅርብ ደጋፊዎቻቸዉ የሚወጉትን ኃይል መልሰዉ ከማዉገዝ ባለፍ ከሐገራቸዉ በመቶ ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ስለጠፋቸዉ የመን፣ስለኢትዮጵያዉ ግጭትና ጦርነት፣ስለ ጁቡቲና ኤርትራ ዉዝግብ ያላነሱት የግጭት ጦርነቱን አስከፊነት አጥተዉ አይደለም።ከጎረቤቶቻቸዉ በጣሙን ከሪያድና አቡዳቢ የሚገጥማቸዉን አፀፋና መዘዝ አዉቀዉት እንጂ።

የሐሰን ሼክ ደጋፊዎች እንደሚሉት አዲሱ ፕሬዝደንት ቀዳሚያቸዉ  የወረሱትን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ገንዘብ ለመመለስ፣ መመለሱ ቢቀር በመወረሱ የአቡዳቢ ገዢዎችን ቅሬታ ለማለዘብ ይቅርታ እንዲጠይቁ ከፍተኛ ግፊት እየተደረገባቸዉ ነዉ።

ምስል DHA

የሶማሊያ ጉዳይ  ተንታኞች እንደሚሉት ደግሞ ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ በዘመነ ስልጣናቸዉ ከክፍለ ሐገራት ገዢዎች፣ከጎሳ መሪዎችና ከጠቅላይ ሚንስትራቸዉን ጋር የከረረ አተካራ ዉስጥ የገቡት፣ በስተመጨረሻዉም በተቀናቃኛቸዉ የተሸነፉት በአመራራቸዉ ድክመት ብቻ አይደለም።በአቡዳቢዎች ተዘዋዋሪ ግፊት ጭምር እንጂ።የፖለቲካ ተንታኝ የሱፍ ያሲንም አረብ ኤምሬቶችን የመሳሰሉ ትናንሽ ግን ሐብታም ሐገራት በድሖቹ ሐገራት ላይ የሚያደርጉት ተፅዕኖ ቀላል አይደለም ይላሉ።

                                     

ብሪታንያዊ የሕንድ ገዢ ሎርድ ከርዘን በ1903 ጥቂት የባሕር ኃይል መርከቦቻቸዉን አስከትለዉ ወደ አረቢያ ባሕረ ሰላጤ የቀዘፉት ቱርክና የሌሎች የአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች ባካባቢዉ ስለሚያደርጉት  እንቅስቃሴ ሰላዮቻቸዉ የነገሯቸዉን ለማረጋገጥ ነበር።ሻርጃሕ ወደብ ሲደርሱ የግዛቲቱን ገዢ አስጠሩና «ሌላ ኃይል እንዳያጠቃችሁ የብሪታንያን የበላይ ጠባቂነት ተቀበሉ» አሏቸዉ።

አረቡ ገዢ ምርጫ አልነበራቸዉ። የብሪታንያዉን ሹም ቃል ተቀበሉ።ዛሬ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚባለዉ ስብስብ የሚያስተባራቸዉ ሰባት ግዛቶች ከብሪታንያ ቅኝ ተገዢነት ይልቅ በብሪታንያ የበላይ ጠባቂነት የሚተዳደሩ በሚለዉ ስርዓት ሲገዙ ነበር።

በ1950 አቡዳቢ ላይ የፈለቀዉ ነዳጅ ዘይት የኒዚያን ግዛቶች የዘመናት ምጣኔ ሐብታዊ፤ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስርዓት ቀየረዉ።በ1971 ሙሉ በሙሉ ነፃ ወጡ።በ1972 ዋና ዙፋኑን አቡዳቢ ላይ ያደረገዉን ሕብረት ወይም  ፌደሬሽን መሠረቱ።የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች።ትንሽ ናት።ግን በቀን 3 ሚሊዮን በርሚል ነዳጅ ዘይት ታመርታለች።215 ትሪሊዮን ኪቢክ ሜትር ጫማ ክምችት አላት።በነዳጅና በጋስ ክምችት ከዓለም 7ኛ ደረጃ ትይዛለች።ዱባይን የመሰለ የንግድ ማዕከል ፈጥራለች፣ ቡርዥ ኸሊፋን የመሰለ ሕንፃ ገንብታለች።DP World የተባለዉን ግዙፍ የወደብ አገልግሎት ኩባንያ መስርታለች።

ሐብቷ ጉልበት ሆኗት በዓለም ዕዉቅናን አትርፋለች።የአፍሪቃ ቀንድን፣ የሰሜን አፍሪቃን፣ የመካከለኛዉ ምሥራቅን፣ የአረብ ልሳነ ምድርን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ ወታደራዊ ሒደት ባሻት ለመዘወር ትፍጨረጨራለች።የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት አዳዲሶቹ ገዢዎች ከሪያድ አቻዎቻቸዉ ጋር በመሆን በየስፍራዉ ጣልቃ ለመግባት የደፈሩት በገንዘብ አቅማቸዉ ብቻ ሳይሆን ዩናይትድ ስቴትስን በመሳሰሉ ኃያላን አይዟችሁ ስለሚባሉም ጭምር ነዉ።

ምስል Sasha Pritchard/aal.photo/IMAGO

የሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የአዲስ አበባና የኤርትራ መሪዎችን ወዳጅነት በፊርማ አስፀድቀዋል።ስለተፈረመዉ ስምምነት ይዘት ግን ከፈራሚ-አፈራራሚዎቹ ዉጪ በግልፅ ያወቀ ካለ እሱ በብዙዎች ዘንድ አይታወቅም።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አሰብ ላይ የጦር ሰፈር መስርታ የመንን ስታወድም ነበር። በኢትዮጵያ የርስበርስ ጦርነትም ርዳታ በማቀበሉ ጥረትም ተሳታፊ መሆንዋ በሰፊዉ ይነገራል።አሁን ደግሞ አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ዘይድ አል ናሕያን የአረብ ኤሚሬቶችን የመሪነት ስልጣን ከያዙ ወዲሕ በሕዳሴ ግድብ ሰበብ የሚወዛገቡትን ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳንን ለመሸምገል መጠየቃቸዉ እየተወራ ነዉ።

ምስል Jon Gambrell/AP Photo/picture alliance

የማደራደሩ ወሬ እዉነትም ሆነ ሐሰት ኢትዮጵያን ጨምሮ ድጋፍ የሚደረግላቸዉ ወይም ለተፅዕኖ የተጋለጡት ሐገራት የየራቸዉን ጥቅም፣ከየድጋፍ ሰጪዎቹ ፍላጎት ጋር የሚያጣጥሙበትን መርሕ ካልተከተሉ አቶ የሱፍ እንደሚመክሩት ድጋፉ ጉዳት፣ ወዳጅነቱ ኪሳራ ሊያስከትል ይችላል።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW