የትውልደ ኢትዮጵያ ጀርመናውያን መራጮች አስተያየት
ሰኞ፣ የካቲት 17 2017
ቅድመ ምርጫ
በጀርመን በተለይ ወንድ ወጣቶች ለፅንፈኛ ፓርቲዎች ያላቸው ድጋፍ ትርጉም ባለው መልኩ መጨመሩን መረጃዎች ያመላክታሉ። በጀርመን በጎርጎሮሳዊው 2024 ዓመተ ምኅረት በተካሄዱትና የአጠቃላይ ምርጫው ውጤት መስታወት ናቸው በሚባሉት የአካባቢያዊና የአውሮፓ ሕብረት ምክርቤት ምርጫዎች ቀኝ ፅንፈኛ ፓርቲዎች ከፍተኛ ድምጽ አግኝተው ማሸነፋቸው እንደስጋት እየተወሰደ ነው። በማግድቡርግ ፣ በሙኒክና ሌሎች አካባቢዎች በስደተኞች በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰዎች መሞታቸውና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸው ደግሞ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት መደቀኑን አንዳንድ ነዋሪዎች ለዶይቸቨለ ተናግሯል። እነዚህ ነዋሪዎች የደህንነት ስጋታቸውን ይቀርፉልናል ብለው ላመኑባቸው ለቀኝ ፅንፈኛ ፓርቲዎች ድምጻቸውን መስጠታቸው እንደማይቀር ገልጸዋል።
የትውልደ ኢትዮጵያ ጀርመናውያን መራጮች አስተያየት
አቶ አለም ታደሰ በጀርመን አገር መኖር ከጀመሩ 3 አስርት ዓመታትን አስቆጥሯል። የፅንፈኛ ፓርቲዎችየሕዝብ ድጋፍ ማደግ ብቻ ሳይሆን እንደ ክርስትያን ዴሞክራቲክና ክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች ያሉ አገሪቱን ለረዥም ዓመታት የመሩ ፓርቲዎችም በተለይ በስደተኞች ፖሊሲ «ጽንፈኛ» እየተባለ ከሚጠቀሰው አማራጭ ለጀርመን የተባለ ፓርቲ ጋር ወደ ሚመሳሰል አቋም ማዘንበላቸውን ለመታዘብ መቻላቸውን አጫውተውናል።
«ለረዥም ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ በአመራር ላይ የነበሩት ዴሞክራቶች ናቸው የሚባሉ እንደ ክርስትያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ አመራሮች የሰጡት መግለጫ ከነዛ በጣም ቀኝ «ራዲካል» ከሚባሉት ሰዎች ጋራ የሚመሳሰል ነው። የሸንገን ቪዛን አለመቀበል። በጋብቻ ቤተሰብን የማምምጣትን አለመቀበል ሲቃወሙ ሰምተናል። ግን ተቃውሞ ደርሶበታል፤ በሚገርም አይነት ሁኔታ። እና ይህን ይህን ታዝቤያለሁ።»
የኤኮኖሚ ባለሞያው ዶክተር ፈቃዱ በቀለ ትውልደ ኢትዮጵያ ጀርመናዊ ሲሆኑ የተለያዩ ምርምሮችን በማካሄድ ፤ በዩኒቨርስቲዎች በማስተማርና በራሳቸው ድረ-ገጽ በአፍሪቃና በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ በመጻፍ ይታወቃሉ። የበርሊን ከተማ ነዋሪው ዶክተር ፍቃደ «ፅንፈኛ» ያሏቿው ፓርቲዎች በስደተኞች ላይ እንከተለዋለን ያሉት ፖሊሲ ያላቸውን ምልከታ አጋርተውናል።
«በእርግጥ አንዳንድ ግፊቶች አሉ በተለይም አማራጭ ለጀርመን የሚባለው ቀኝ ፓርቲ አለ። እሱ በተለይም የውጭ አገር ሰዎችን በሚመለከት ግፊት ያደርጋል። በብዛት መምጣት የለባቸውም፤ የመጡትም ተመልሰው ወደ አገራቸው እንዲሄዱ፤ ግን በሌሎች ፓርቲዎች ተቃውሞ አለበት።»
ዶክተር ታምሩ መለሰ በጀርመን ረዥም ዓመታት የኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ጀርመናዊ ናቸው። የሕግ ባለሙያው ዶክተር ታምሩ በፍራንክፈርት ከተማ የሕግ ማማከር አገልግሎት በመስጠትና ጀርመንኛ ቋንቋ በማስተማር ይታወቃሉ። እሳቸውም ስጋታቸውን እንዲህ አጋርተውናል።
«ስጋቱ እነሱ ባያሸንፉም ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት ፓርላማ ውስጥ ቦታ በማግኘት ብዙ ችግር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ነው።»
ከስጋት ባሻገር ያለው ተስፋ
«ፅንፈኛ እና ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎች ከፍተኛ ድምጽ አግኝተው በምክርቤት መግባታቸው በተለይ በስደተኞች ላይ እንከተለዋለን ባሉት ፖሊሲከፍተኛ ስጋት ቢደቅኑም ዴሞክራሲያውያን ፓርቲዎች ይህን በመቃወማቸውና በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ጀርመናውያን ይህን የ«ጽንፈኞች » አቋም መቃወማቸውና ለስደተኞች ያላቸውን አጋርነት በሰላማዊ ሰልፎች መግለጻቸውን ደግሞ ተስፋ ሰጪ ነው ይላሉ ዶክተር ታምሩ።
« ተስፋው ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎች ስልጣን እንዳይዙ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚታገሉ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ጥረት ተስፋ ሰጭ ነው። ሕብረተሰቡ ደግሞ እነዚህ አክራሪ ፓርቲዎች ወደ ስልጣን እንዳይመጡ በሰላማዊ ሰልፍና በመሳሰሉት እየገለጸ ነው።»
«መጤ ጠል» እየተባለ የሚወቀሰው አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ከከዚህ ቀደሞቹ ምርጫዎች የተሻለ ድምጽ ያገኛል ተብሎ ቢጠበቅም መንግስት የመመስረት ዕድል ስለሌለው ግን ለአፍሪካውያን ስደተኞች ብዙም አያሰጋም የሚሉት ደግሞ የበርሊን ከተማ ነዋሪዎ ዶክተር ፈቃደ በቀለ ናቸው።
«ጥሩው ነገር ግን ይህ ፓርቲ ብዙ ድምጽ ቢያገኝም ወደ 20፣ 21 በመቶ። ይሁንና መንግስት የመመስረት ሃላፊነት ሳይሆን ሌሎች ዴሞክራቲክ ፓርቲዎች፤ እንደ ክርስትያን ዴሞክራቲክ ኅብረት ፣ ክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች ሌሎችም ከዚህ የቀኝ ፓርቲ ጋራ ተጣምረው መንግስት ለመመስረት አይፈልጉም። እና በዚህ ምክንያት የውጭ አገር ሰዎች« ኢትዮጵያኖችም በዚህ ጥገኝነት ጠይቀው የሚኖሩ ይህን የሚያህል ስጋት እንዲያድርባቸው የሚያስፈልግ አይመስለኝም።»
«ቀኝ ፅንፈኛ» የተባሉ ፓርቲዎች በስደተኞች ላይ እንከተለዋለን ያሉትን ፖሊሲ በመቃወምና ለስደተኞች ያላቸውን አጋርነት በመግለጽ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ጀርመናውያን አደባባይ ወጥተው መቃወማቸው ይታወሳል።#BTW2025
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ