1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“የትግራይን ጦርነት ለማስቆም በሠራንው ሥራ በጣም እኮራለሁ” - ሞሊ ፊ

Eshete Bekele
ቅዳሜ፣ ጥር 10 2017

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ግጭቶች የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች የሚወስዷቸው እርምጃዎች አሳሳቢ መሆናቸውን በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ተናገሩ። ኃላፊነታቸውን ሰኞ የሚያጠናቅቁት ዲፕሎማት ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ያላትን ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ ልትወስድ የሚገባት እርምጃዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ሞሊ ፊ
ሞሊ ፊ በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሆነው ባገለገሉባቸው ዓመታት ያከናወኗቸውን ሥራዎች መለስ ብለው በፈተሹበት ቃለ-መጠይቅ ደም አፋሳሹ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለማስቆም ሀገራቸው የተጫወተችውን ሚና በበጎ ጠቅሰዋል።ምስል piemags/IMAGO

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እየተካሔዱ በሚገኙ ግጭቶች የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች የሚወስዷቸው እርምጃዎች አሳሳቢ መሆናቸውን በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ተናገሩ።

ግጭቶቹ “እንደ ሁሉም የትጥቅ ትግሎች ሕጋዊ እና አስቸጋሪ” መሆናቸውን የገለጹት ሞሊ ፊ ይሁንና አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከባድ እርምጃዎች እየወሰዱ ነው ብላ እንደምታምን ተናግረዋል። ዲፕሎማቷ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች “ለሲቪል ተጎጂዎች መስጠት የሚገባቸውን ትኩረት እየሰጡ አይደሉም” ሲሉ ተችተዋል።

ኃላፊነታቸውን በመጪው ሰኞ የሚያጠናቅቁት ሞሊ ፊ መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ከፋኖ ታጣቂዎች እና ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሚያደርጉት ውጊያ ላይ አስተያየት የሰጡት ከፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ነው።

ዲፕሎማቷ በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሆነው ባገለገሉባቸው ዓመታት ያከናወኗቸውን ሥራዎች መለስ ብለው በፈተሹበት ቃለ-መጠይቅ ደም አፋሳሹ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለማስቆም ሀገራቸው የተጫወተችውን ሚና በበጎ ጠቅሰዋል።

ከ2013 እስከ 2015 የተካሔደው ጦርነት “በወቅቱ በዓለም ትልቁ ግጭት” እንደነበር ያስታወሱት ሞሊ ፊ “የትግራይን ጦርነት ለማስቆም በሠራንው ሥራ በጣም እኮራለሁ” ብለዋል።

በመጪው ሰኞ ሥልጣናቸውን ለተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የሚያስረክቡት የጆ ባይደን አስተዳደር በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት ኢትዮጵያን ከአጎዋ ከታኅሳስ 23 ቀን 2014 ጀምሮ አስወጥቷል።

የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ያዳረሰው ጦርነት የተገታው የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት ጥቅምት 23 ቀን 2015 በፕሪቶሪያ በተፈራረሙት ግጭት የማቆም ሥምምነት ነበር። ሥምምነቱ እንዲፈረም ከአፍሪካ ኅብረት ጎን አሜሪካ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች።

አሜሪካ “የነበረንን አይነት አጋርነት ለመቀጠል የሚያስችል ሁኔታ ላይ መገኘት ትፈልጋለች” ያሉት ሞሊ ፊ ነገር ግን ኢትዮጵያ ልትወስድ የሚገባት እርምጃዎች መኖራቸውን ከፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ተናግረዋል።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW