1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የትግራይ ጊዚያዊ ፕሬዝደንትን ለመሰየም ሕዝብ እንዲጠቁም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጠየቁ

ረቡዕ፣ መጋቢት 17 2017

የክልሉ ህዝብ የእጩዎች ጥቆማ ከዛሬ ጀምሮ በኢሜይል መላክ እንደሚችልም ጥሪ ያቀርባል። ይህ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር የተሰራጨ መልእክት በትግራይ በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ያለ ሲሆን ከግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት የመሾም ስልጣን ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት በህወሓት ይሰጡ ከነበሩ መግለጫዎች እና አቋሞች ጋርም የሚፃረር ነው።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ። የጠቅላይ ሚንስትሩ ጥያቄ ከዚሕ ቀደም ሥለጊዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ሹመት ከሚነገረዉ ጋር የሚፃረር ነዉ።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ።የትግራይ ሕዝብ ለክልሉ ጊዚያዊ ፕሬዝደንት የሚሆን ሰዉ እንዲጠቁም ጠየቁምስል፦ Fana Broadcasting Corporate S.C.

የትግራይ ሕዝብ ለክልሉ ጊዚያዊ ፕሬዝደንት የሚሆን ዕጩ እንዲጠቁም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጠየቁ

This browser does not support the audio element.

ለትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት፥ ህዝብ ጥቆማ ይስጥ ሲሉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ጥሪ አቀረቡ። ህወሓት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ከፌደራል መንግስት ጋር በሚደረግ መግባባት የሚሾም ነው ሲል ከዚህ ቀደም ማስታወቁ ይታወሳል። በዚህ ጉዳይ የሕግ ምሁር አነጋግረናል።

 

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ዛሬ በትግርኛ ባስተላለፉት መልእክት እንዳነሱት በኢትዮጵያ ሕገመንግስት፣ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እና በሚኒስትሮች ምክርቤት አዋጅ መሰረት የተቋቋመው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፥ ለሁለት ዓመት ስራ ላይ መቆየቱ የሚገልፅ ሲሆን በዚህ ግዜ የተሰጡት ቁልፍ ተግባራት አከናውኖ በህዝብ ወደ ተመረጠ መንግስት ለመሸጋገር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳልተቻለ ያነሳል። በዚህም መሰረት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር  የስልጣን ግዜ በአንድ ዓመት ለማራዘም የግድ ሆኖ እንዳለም ያክላል። የፌደራል መንግስቱ መሬት ላይ ያለ ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የግዚያዊ አስተዳደሩ የስልጣን ግዜ ለማራዘም ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና የሕግ ስራዎች እየተከወነ ነው የሚለው ይህ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ የፅሑፍ መልእክት፥ ከዚህ ጋር ተያይዞ አዲስ የግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት መሾም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱም ያመለክታል።

 

የግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት የመሾም ስልጣን በሚኒስትሮች ምክርቤት አዋጅ ደንብ ቁጥር 533/ 2015 የጠቅላይ ሚኒስቴሩ እንኳን ቢሆንም የህዝብ ተሳትፎ እንዲኖር የክልሉ ህዝብ የእጩዎች ጥቆማ ከዛሬ ጀምሮ በኢሜይል መላክ እንደሚችልም ጥሪ ያቀርባል። ይህ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር የተሰራጨ መልእክት በትግራይ በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ያለ ሲሆን ከግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት የመሾም ስልጣን ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት በህወሓት ይሰጡ ከነበሩ መግለጫዎች እና አቋሞች ጋርም የሚፃረር ነው። በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን ስልጣን ላይ የቆዩት የክልሉ ፕሬዝደንት ለመቀየር ከፌደራል መንግስቱ ጋር ንግግር ላይ መሆኑ ሲገልፅ የነበረ ሲሆን፥ በሁለቱ የፕሪቶርያ ውል ፈራሚዎችመግባባት የግዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ስልጣን እንደሚፀድቅ አስታውቆ ነበረ።

የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ሹመት አሁንም እያወዛገበ ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የትግራይ ሕዝብ ዕጩ እንዲጠቁም ጠይቀዋል።ምስል፦ Million Hailesilassie/DW

ከቀናት በፊት ለመገናኛ ብዙሐን ማብራሪያ ሰጥተው የነበሩ የህወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ አማኑኤል አሰፋ "በተለይም የፕሬዝደንት ቦታ የሚመለከት ደግሞ ሁለታችን የተስማማንበት ነው የሚሆነው። ሁለታችን ያልተስማማንበት እንደማይሆን ከዚህ በፊትም ተረጋግጦ የቆየ ነው" ሲሉ ተናግረው ነበር።

በዚህ የህወሓት እና የፌደራሉ መንግስት የተራራቀ አቋም ዙርያ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጣሉ። የሕግ ምሁሩ አቶ ዓወት ልጃለም የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የተቋቋመው በፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት ነው፥ ስምምነቱም ሁለቱ የውሉ ፈራሚዎች በሚያደርጉት ፖለቲካዊ ድርድር ግዚያዊ አስተዳደሩ ይቋቋማል እንጂ ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ ብቻ የሰጠው የተለየ ሐላፊነት የለም ሲሉ ያስረዳሉ።

ከዚህ በተጨማሪ የሕግ ምሁሩ አቶ ዓወት ልጃለም በጠቅላይ ሚኒስቴሩ የፅሑፍ መልእክት የተጠቀሰው የሚኒስትሮች ምክርቤት አዋጅም ግዚያዊ አስተዳደሩ ስራ ከጀመረ ወራት በኃላ የወጣ መሆኑንም ያነሳሉ።

በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከህወሓት ወገን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW