የትግራይ መምህራን በፌደራሉ መንግስትና በክልሉ አስተዳደር ላይ ክስ መሰረቱ መባሉ
ሰኞ፣ ጥቅምት 25 2017የ17 ወራት ደሞዝ አልተከፈለንም ያሉ በትግራይ የሚገኙ መምህራን በፌደራሉ መንግስት እና በክልሉ አስተዳደር ላይ ክስ መሰረቱ። የትግራይ መምህራን ማሕበር ያልተከፈለው የአስተማሪዎች ደሞዝ እንዲለቀቅ እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ድረስ በመቅረብ መፍትሔ እንዲሰጠው ተደጋጋሚ ጥረት ማቅረቡ የሚገልፅ ሲሆን፥ ይህ ምላሽ ባለማግኘቱ ጉዳዩ ለሕግ ማቅረቡ አስታውቋል።
በትግራይ የሚገኙ አጠቃላይ የክልሉ መንግስት ሰራተኞች በተለይም ደግሞ በክልሉ መንግስት የተቀጠሩ አስተማሪዎች፥ የፌደራል መንግስቱ እና የትግራይ ሐይሎች ጦርነት ላይ በነበሩበት ወቅት የሰሩበት ደሞዝ እንዲከፈላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የስራ ማቆም አድማ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የ2014 ዓመተምህረት ሙሉ ዓመት፣ የ2015 ዓመተምህረት ደግሞ አምስት ወራት፥ በአጠቃላይየ17 ወራት ደሞዝ አልተከፈለንም የሚሉ እነዚህ በትግራይ የሚገኙ መምህራን፥ ቅሬታቸው ለክልሉ አስተዳደር እና የፌደራል መንግስት በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም በቅርቡ ይከፈላል ተብሎ ከተገባ ቃል ውጭ እስካሁን ይገባናል ያሉት ክፍያው አለመፈፀሙ ይናገራሉ። በተደጋጋሚ በሚያወጣቸው መግለጫዎች የመምህራኑ ጥያቄ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥሪ ሲያቀርብ የቆየው የትግራይ መምህራን ማሕበር እንዳስታወቀው፥ የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር እና የፌደራሉ መንግስት እስካሁን ምላሽ ባለመስጠታቸው ጉዳዩ ለሕግ ማቅረቡ አስታውቋል። የትግራይ መምህራን ማሕበር ምክትል ፕሬዝደንት መምህርት ንግስቲ ጋረድ ለዶቼቬለ እንዳሉት፥ ያልተከፈለው የትግራይ መምህራን ጥያቄ ጉዳይ ይዘን እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ድረስ ቅሬታ ማቅረባቸው ይሁንና እስካሁን መፍትሔ ስላልተሰጣቸው በፌደራሉ መንግስት እና በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ላይ ማሕበራቸው ክስ መመስረቱ ገልፀውልናል።
የትግራይ መምህራን ማሕበርበትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እና የፌደራሉ መንግስት የመሰረተው ክስ በትግራይ ከፍተኛ ፍርድቤት እየታየ መሆኑ የገለፁልን የመምህራን ማሕበሩ ጠበቃ ዳዊት ገብረሚካኤል በበኩላቸው፥ የትግራይ ክልል እና የፌደራሉ መንግስት የፋይናንስ መስርያቤቶች ጨምሮ ሌሎች ተቋማት መክሰሳቸው ገልፀውልናል። ጠበቃ ዳዊት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፣ የትግራይ ትምህርት ቢሮ፣ የትግራይ ፋይናንስ ቢሮ እና የፌደራሉ መንግስት ፋይናንስ ሚኒስቴር በዚሁ የመምህራን ጉዳይ ተከሳሽ የመንግስት ተቋማት መሆናቸው ለዶቼቬለ ገልፀዋል።
የትግራይ መምህራን ማሕበር እንደሚለው የ2014 ዓመተምህረት የ12 ወራት ደሞዝ ከፌደራል መንግስቱ፣ የ2015 ዓመተምህረት የ5 ወራት ደሞዝ ደግሞ ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እንዲከፈላቸው እንደሚጠብቁ ይገልፃል። መምህርት ንግስቲ ጋረድ "ሕግ ካለ የአስተማሪው ደሞዝ ይከፈላል ብለን እናምናለን" ሲሉ ጨምረው ገልፀዋል። በዚሁ የትግራይ መምህራን ጥያቄ እና ያቀረቡት ክስ ዙርያ ከክልሉ አስተዳደር እና የፌደራል መንግስቱ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የትግራይ መምህራን ማሕበር በፌደራሉ መንግስት እና የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ላይ የመሰረተው ክስ በዚህ ሳምንት በትግራይ ከፍተኛ ፍርድቤት እንደሚታይ ከጠበቆች ሰምተናል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ