«የትግራይ ተወላጆች አዲስ አበባ ዉስጥ እየታሰሩ ነዉ» ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ደርጅት
ማክሰኞ፣ ሰኔ 24 2017
«የትግራይ ተወላጀች አዲስ አበባ ዉስጥ በዘፈቀድ እየታሰሩ ነዉ» ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ደርጅት
በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ተወላጀች ላይ ያነጣጠረ የዘፈቀደ እስር እየተፈፀመ ነው ሲል ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች የተባለ አገር በቀል የመብቶች ድርጅት አመለከተ፡፡ ሰብዓዊ ድርጅቱ ትናንት ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም. በይፋ ባወጣው ሪፖርት የጅምላ እስር ያሉት ተግባሩ በበራካታ የመዲናዋ ፖሊስ ጣቢዎች ላይ መታየቱን አስረድቷል፡፡
ባለፉት ሳምንታት በአዲስ አበባ ከተማ በትግራይ ተወላጆች በተለይ ደግሞ ወጣቶች ላይ ከተለያዩ ቦታዎች እስር እየተፈፀመ እንደሆነ በማሕበራዊ ሚድያ ሲነገር መቆየቱን ተከትሎ ከሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የደረሰውን ተደጋጋሚ ጥቆማ ተከትሎ ወደ ምርመራ መግባቱን ለዶይቼ ቬለ የነገሩት የቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ደርጅት ኃላፊ አቶ ተስፋሌም በርሔ፤ ባደረጉትም ምርመራ የወጣቶች መታፈስ ስለማረጋገጣቸው ገልጸዋል፡፡ “በየፖሊስ ጣቢ ባደረግነው ምልከታ ወጣቶች እየታፈሱ መሆኑን ነው ማረጋገጫ ያገኘነው” ያሉት አቶ ተስፋለም ይህንኑን ተግባር በተለያዩ የመዲናዋ ፖሊስ ጣቢዎች ውስጥ ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ እስራቱ በዋናነት የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ መስሏል ያሉት የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ኃላፊ፤ “በተለይም ከሰኔ ወር መጀምሪያ ጀምሮ ጉዳዩ በትኩረት ከትግራይ በሚመጡ ወጣቶች ላይ ያተኮረ ነው” በማለት ህንኑን በምርመራቸው እንዳረጋገጡም አንስተዋል፡፡ መንስኤው ምን እንደሆነ እንደማይታወቅ፤ የፖሊስ ጣቢው የእስራቱን መንስኤ ስጠይቅ ወቅታዊ ሁኔታ ከሚል ሌላ መልስ እንዳላገኙም ጠቁመዋል፡፡ትግራይ ክልል ተጨማሪ የተቃዋሚዎች እስር
የትግራይ ክልል ወጣቶችና ቢሮ በቅርብ ጊዜ ባወጣው ሪፖርት በዚህ ዓመት 2017 ዓ.ም ውስጥ ብቻ ከ56,000 (ሃምሳ ስድስት ሺ) በላይ ወጣቶች ከትግራይ ክልል ወጥተው አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች እና ከአገር ውጪም እንደወጡ ማረጋገጡን ያመለከተው አገር በቀል የሰብዓዊ ምብቶች ድርጅቱ፤ ስራ አጥነት ለስደቱ እንደ ዋና መነሻ ቢሆንም በቅርብ ጊዜያት እየታየ ያለ የቅድመ ግጭት ምልክቶች ወጣቶች ከክልሉ ሸሽተው እንዲወጡ ተጨማሪ ምክንያት እየሆነ ነው ብሏልም፡፡
በስራ አጥነትና የፖለቲካ አለመረጋጋት ወቅት አዲስ አበባ ከተማ የወጣቶቹ ዋነኛ መዳረሻ ከሆኑት ቦታዎች ዋነኛ መሆኑ የሚታወቅም ነው ያለው ድርጅቱ፤ ለሥራ ፍለጋና መረጋጋት መሻት ያወጣቸውን ወጣቶች በእስር መቀበል ኢሰብዓዊ ነው ሲል አመልክቷልም፡፡ በስም፣ በአነጋገር ሁኔታ እና በቋንቋ እየተለየ ይፈጸማል ያለውን እስር በምርመራ ወቅት ከተቀበለው ምስክርነቶች መስማቱን የገለጸው ሰብዓዊ ድርጅቱ ከታሰሩት ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ የነዋሪነት መታወቂያ ያላቸውም ጭምር መካተታቸውን አስረድቷልም፡፡በድሬዳዋ የትግራይ ተወላጆች አቤቱታና የድሬዳዋ መስተዳድር መልስ
አንዳንዶቹን በማጣራትም የመልቀቅ ሁኔታዎች ይስተዋላል ያለው ሪፖርቱ ከእስሩ ከወጡት እማኞች ላይ በአንድ ፖሊስ ጣቢያ እስከ መቶ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ እስከ 50 ወጣቶች መታሰራቸውንም በዚህ ዘገባው አካቷል፡፡ ወጣቶቹ ታስረውበታል ያላቸውን ቦታዎችም በዝርዝር የጠቃቀሳቸው ድርጅቱ በዚህ እስር የተጣሱ የሕገ መንግስትና ሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 17፣ አንቀጽ 19(1)(3) እና አንቀፅ 25 እንዲሁም የዓለም አቀፉ ሰብአዊ መብት መግለጫ (UDHR) አንቀፅ 9 እና ዓለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶች ስምምነት (ICCPR) አንቀፅ 6 ናቸው ብሏል፡፡
ጉዳዩ በላይኛው የመንግስት መዋቅር ስለመታወቁም በጥርጣሬ እንደሚነሱትም ለዶይቼ ቬለ ያስረዱት የሰብዓዊ ድርጅቱ ሃላፊ አቶ ተስፋለም፤ በመንግስት ሊወሰዱ ስለሚገቡ የመፍትሄ እርምጃዎችም ሲያነሱ፤ የመንግስት አካላት በተለይም የአዲስ አበባ ፖሊስ በወንጀል የሚያስጠረጥራቸው ጉዳይ ካለም በሕጉ መሠረት ለፍ/ቤት እንዲያቀርብ በአጠቃላይ ለሕገ መንግስቱ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ተገዢ እንዲሆን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
የዘፈቀደ እስር ያሉት ተግባሩ እንዲከናወን የወሰኑ፣ ትዕዛዝ የሰጡ እና እየፈፀሙ የሚገኙ አካላት ውሳኔያቸውንና ተግባራቸውን በመመርመር በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑም ተጠይቋል። ዶይቼ ቬለ የሰብዐዊ ድርጅቱ ሪፖርት እና የሃላፊው አስተያየት ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባዮች ስልክ ላይ በመደወል ሀሳባቸውን እንዲሰጡበት ያደረገው ጥረት ግን ለዛሬ አልሰመረም፡፡ ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም በትግራይ እና ኤርትራ ተወላጆች ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተካሄደ የዘፈቀደ እስር ሪፖርት በማውጣት ድርጊቱ እንዲቆም ሲል መጠየቁም ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ