1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ተፈናቃዮች የዕርዳታ ጥሪ

ቅዳሜ፣ ጥር 27 2015

የክልሉ አስተዳደር እና የተለያዪ ግብረሰናይ ድርጅቶች ካለፈው ነሐሴ ወር ወዲህ በነበረው ሁኔታ በትግራይ ከ1.3ሚልዮን በላይ የሚገመት ህዝብ ዳግም መፈናቀሉ የሚገልፁ ሲሆን፣ ይህ አስቀድሞ ከነበረው ተፈናቃይ እንዲሁም ሌሎች ማሕበራዊ ችግሮች ጋር ተዳምሮ ሰብአዊ ቀውሱ የከፋ አድርጎታል ይላሉ።

Äthiopien Binnenvertriebene aus Tigray | Gebreegziabher Aregawi
ምስል Million Hailessilasse/DW

የትግራይ ተፈናቃዮች የዕርዳታ ጥሪ

This browser does not support the audio element.

በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮች እና ሌሎች እርዳታ ፈላጊዎች ሰብአዊ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ ተናገሩ። የእርዳታ አቅርቦት ሰራተኞች በበኩላቸው ወደ ትግራይ የሚገባ ሰብአዊ እርዳታ በመጠን ከግዜ ወደ ግዜ እያደገ ቢሆንም ካለው ፍላጎት አንፃር ሲታይ አሁንም ዝቅተኛ እንደሆነ ገልጸዋል። 

አቶ ነጋሲ ማረከ እና ስምንት የቤተሰባቸው አባላት ከቀዬአቸው ምዕራብ ትግራይ ፀገዴ ወረዳ የተፈናቀሉት በጦርነቱ ጅማሮ አካባቢ ሕዳር ወር 2013 ዓመተምህረት ነበር። ባለፉት ሁለት ዓመታ በሄዱበት ጦርነት እየደረሰባቸው በተደጋጋሚ ከቦታ ቦታ መፈናቀላቸው፣ ባለፈው ነሐሴ ወር ደግሞ ጦርነቱ ተባብሶ ሲቀጥል፥ ግማሽ ቤተሰባቸው ሽረ እንዳስላሰ ሌላው ደግሞ ወደ ዓብይዓዲ ተጉዞ መበታተኑ የሚገልፁት አቶ ነጋሲ ተደጋጋሚ መፈናቀል፣ የቤተሰብ መለያየት፣ የመሰረታዊ የእርዳታ እና መጠልያ እጦት ለከፍተኛ ችግር እንደዳረጋቸው ይገልፃሉ። አሁን ላይ ከተወሰኑ የቤተሰቦቻቸው አባላት ጋር በዓብይዓዲ ከተማ በሚገኝ መጠልያ እንዳሉ የገለፁልን ተፈናቃዩ፣ እርሳቸው ጨምሮ ከ50 ሺህ በላይ በከተማዋ የሚገኙ በጦርነቱ ምክንያት ከምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ እና ማእከላዊ የትግራይ ዞኖች የተፈናቀሉ ዜጎች ለረሃብና ሌሎች በርካታ ችግሮች ተዳርገው እንዳለ ያስረዳሉ። እንደ ተፈናቃዩ ገለፃ ለመጨረሻ ግዜ የምግብ እርዳታ የደረሳቸው ከሶስት ወር በፊት ጥቅምት ወር አጋማሽ ነበር። 

ምስል Million Hailessilasie/DW

የክልሉ አስተዳደር እና የተለያዪ ግብረሰናይ ድርጅቶች ካለፈው ነሐሴ ወር ወዲህ በነበረው ሁኔታ በትግራይ ከአንድ ነጥብ ሶስት ሚልዮን በላይ የሚገመት ህዝብ ዳግም መፈናቀሉ የሚገልፁ ሲሆን፣ ይህ አስቀድሞ ከነበረው ተፈናቃይ እንዲሁም ሌሎች ማሕበራዊ ችግሮች ጋር ተዳምሮ ሰብአዊ ቀውሱ የከፋ አድርጎታል ይላሉ።  

ሌላው ያነጋገርናቸው መጀመርያ ከምዕራብ ትግራይ፣ ቀጥሎ ከሽረ ተፈናቅለው አሁን ላይ ዓብይዓዲ ከተማ የሚገኙ የስድስት ቤተሰብ እሚያስተዳድሩት አቶ ብርሃነ ታፈረ፥ ለመፈናቀላቸው ምክንያት የሆነው ጦርነት መቆሙ ቢያስደስታቸውም፣ እስካሁን ሰብአዊ ድጋፍ እንኳን የሚያገኙበት ዕድል አለመፈጠሩ እንዳሳሰባቸው ገልፀውልናል። አቶ ብርሃነ በሚኖሩበት ዓብይዓዲ የሚገኝ መጠልያ "በተለይም ህፃናት እና አረጋውያን ለከፋ ችግር ተጋልጠው ይገኛሉ" ብለውናል። በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችም ተመሳሳይ አስተያየቶች ይሰጣሉ። 

ምስል Million Hailessilasse/DW

በዚሁ ጉዳይ ዙርያ ያነጋገርናቸው በክልሉ አስተዳደር የአደጋ መከላከል ኮምሽን የአስቸኳይ ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብረእግዚአብሔር አረጋዊ ጦርነቱ እና ያስከተለው ማሕበራዊ ቀውስ፣ የዜጎች በተደጋጋሚ መፈናቀል፣ በትግራይ ላይ ተጥሎ የነበረ መዘጋት እና ክልከላ እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች በትግራይ የተረጂ ቁጥር እንዲበረክት፤ ሰብአዊ ቀውሱም የከፋ እንዲሆን እንዳደረገው የገለፁ ሲሆን ይህም እየቀረበ ያለው ሰብአዊ እርዳታ ካለው ፍላጎት ጋር እንዳይመጣጠን እንዳደረገው ጠቁመዋል። ሐላፊው "ሁለት ዓመት የቆየው ጦርነት እና የነበረው መዘጋጋት የፈጠረው ከባድ ችግር ነው ያለው። ይህ የተረጂው ቁጥር እጅግ በጣም ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል። የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱም እንዲሁ ሲደነቃቀፍ ነበር የቆየው። ተደራራቢ ችግሮች ነው ያለው። የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱ አሁን እየተሻሻለ ቢመጣም አሁንም በተጨባጭ ካለው ችግር ጋር የሚቀራረብ አይደለም። ያለው ፍላጎት እና አቅርቦት አልተመጣጠነም" ይላሉ። 

አሁን ላይ እንደመልካም የሚነሳው የፌደራሉ መንግስት ለሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ስራው ተባባሪ መሆኑ ነው የሚሉት የአስቸኳይ ምላሽ ዳይሬክተሩ አቶ ገብረእግዚአብሔር አረጋዊ ሰብአዊ እርዳታ ማቅረብ የሚጠበቅባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት ጨምሮ ሌሎች ግን እስካሁን በቂ እርዳታ ወደ ትግራይ እያቀረቡ እንዳልሆነ አንስተዋል። ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ባለው ግዜ አንድ ነጥብ ሁለት ሚልዮን ኩንታል በአብዛኛው ምግብ የሆነ እርዳታ ወደ ትግራይ መግባቱ ሐላፊው ገልፀው ይሁንና ይህ ከፍላጎት አንፃር ሲለካ ዝቅተኛ መሆኑ ተናግረዋል። 

አስተያየት የሰጡን በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮች መንግስት እና ዓለምአቀፍ ተቋማት በአፋጣኝ ሕይወት አድን የምግብ አቅርቦት በማዳረስ፣ በዘላቂነት ደግሞ ተፈናቃዩ ወደ ቀዬው በመመለስ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። በትግራይ በአጠቃላይ ከስድስት ሚልዮን በላይ የሚገመቱ ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ ፈላጊ መሆናቸው የክልሉ አስተዳደር መረጃ ያመለክታል።
ሚልዮን ሃይለስላሰ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW