1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ኃይሎች ከተቆጣጠሯቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች መውጣት

ሰኞ፣ መስከረም 23 2015

በተለይ ሰሞኑን ለተከታታይ 10 ቀናት በራያ የተለያዩ ቦታዎች ከፍተኛ ጦርነት ሲካሄድ ከቆየ በኋላ ከትናንት ጀምሮ የህወሓት ኃይሎች አካባቢዎቹን ለቅቀው እየወጡ እንደሆኑ የቆቦ ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡

Karte Äthiopien Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre DE

የትግራይ ሃይሎች ከአማራ ክልል ስለመውጣት

This browser does not support the audio element.

የህወሓት ኃይሎች ይዘዋቸው ከነበሩ የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች እየወጡ እንደሆነ የዓይን እማኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ተዋጊዎቻቸው ተቆጣጥረዋቸው ከነበሩ የአማራ ክልል አካባቢዎች መውጣታቸውን ገልጸዋል። አንድ የሰሜን ወሎ ዞን የሥራ ኃላፊ ደግሞ ውጊያ አሁንም እንደቀጠለ ብቻ እንደሚየውቁ ገልጠዋል፡፡
 የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት በቅርቡ የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገው ቢቆዩም አንዱ ሌላውን ተጠያቂ በማድረግ  የተኩስ አቁሙ ከተጣሰ በኋላ ህወሓት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን አንዳንድአካባቢዎችን ተቆጣጥሮ ከአንድ ወር በላይ ቆይቷል፣ ከፍተኛ ጦርነቶችም ሲካሄዱ እንደቆዩ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፣ በተለይ ሰሞኑን  ለተከታታይ 10 ቀናት በራያ የተለያዩ ቦታዎች ከፍተኛ ጦርነት  ሲካሄድ ከቆየ በኋላ ከትናንት ጀምሮ  የህወሓት ኃይሎች አካባቢዎቹን ለቅቀው እየወጡ እንደሆኑ የቆቦ ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
የዓይን እማኙ ፣“ለተከታታይ 10 ቀናት ከፍተኛ ውጊያ ተካሂዷል፤ በግመልም በአሕያም፣ በተሸከርካሪም የያዙትን ይዘው እየወጡ ነበር፣ አልገቡም ከተማ ዳርና ዳር ያለ መስመር አለ ያን ተጠቅመው እየወጡ እንደነበረ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪም 90 ከመቶ የሚሆነው በህወሓት ተይዞ የነበረ የሰሜን ወሎ ዞን መለቀቁንና በአንዳንድ አካባቢዎች ውጊያ መኖሩን አመልክተዋል፡፡ ተዋጊዎቹ ቆቦ ከተማን እንደለቀቁና አርበት ከተባለ ቦታ ላይ ውጊያ እንዳለ፣ ነገር ግን ተቆርጠው የቀሩ ጓደኞቻቸው መውጣታቸውን ያላወቁ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡ አራዶም ጎብዬ የተባሉ አካባቢዎችን የህወሓት ኃይሎች ትናንት ለቅቆ መውጣታቸውንና ቆቦን ግን ከዛሬ ጠዋት ጀምረው እየለቀቁ  እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡
 “የትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ” የተባለውን አካል ጠቅሶ የትግራይ ቴሌቪዥን ትናንት ባወጣው መግለጫ ህወሓት በደቡብ ግንባር ይዟዋቸው ከነበሩ የአማራ ክልል ቦታዎች በራሱ ፈቃድ መውጣቱን አመልክቷል፡፡
 “ …ተገድደን ወደ አማራ አካባቢዎች የገባነው ጠላት ለማጥቃት እንጂ የአማራ ምድርን የውጊያ አውድማ ለማድረግ አልነበረም፣ አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በህልውናችን አንጃብቦ ለውን ጥምር ወረራ በአስተማማኝ መልኩ ለማስተናገድ በደቡብ አቅጣጫ ተቆጣጥረን ከነበረው የአማራ አካባቢዎች ወጥተን የቦታ ማሻሻያ አድርገናል፣ ላለፉት ሶስት ቀናት ሰራዊታችን ይህን ተግባራዊ ሲደርግ ቆይቷል፣ ይህን ከውጊያ ውጪ በራሳችን ተነሳሽነትና ውሳኔ የተፈፀመ ነው…፡፡” ብሏል፡፡
ለሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የሰላምና ፀጥታ ኃላፊ ተጨማሪ አስተያየት እንዲሰጡን ብሞክርም አልተሳካልኝም፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈላጉ ሌላ ኃላፊ ግን ጦርነቱ እንደቀጠለ ነው ብለዋል፣ ህወሓት በየጊዜው ለሚያወጣው መግለጫ መልስ መስጠት እንደማይፈልጉና አጠቃላይ በግንባሩ ያለውን የጦርነት ሁኔታ በተመለከተ ግን በሚመለከተው አካል ተጠናክሮ ወደፊት እንደሚሰጥ ገልጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት ጦርነት ውስጥ ከገቡ  2 ዓመት ሊደፍናቸው አንድ ወር ይቀራቸዋል፣ ታዲያ በነዚህ ጊዜዎች በአማራ፣ በትግራይና በአፋር የተለያዩ አካባቢዎች አካባቢዎች በርካቶች ህይወታቸው አልፏል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ከቀያቸውና ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW