1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ የተካተቱበት የተደራዳሪዎች ቡድን አቋቋመ

እሑድ፣ መስከረም 1 2015

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ለሚደረግ የሰላም ሒደት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ። የክልሉ መንግሥት የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ እና ከህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የተካተቱበት ተደራዳሪ ቡድን አቋቁሟል።

Äthiopien | Treffen Getachew Reda, Olusegun Obasanjo und Debretsion Gebremichael
ምስል፦ Privat

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ለሚደረግ የሰላም ሒደት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ። ከህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ የትግራይ ክልል መንግሥትን ወክለው እንዲደራደሩ መሾማቸውን ገልጿል። የክልሉ መንግሥት ይኸን ያለው ዛሬ መስከረም 1 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ ነው። 

የክልሉ መንግሥት በመግለጫው ከኢትዮጵያ የፌድራል መንግሥት ጋር ለሚደረግ ድርድር "ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በፍጥነት እና በጋራ ስምምነት ግጭቶችን ለማቆም" ዝግጁ እንደሆነ ገልጿል። 

"በአፍሪካ ኅብረት የሚመራ ተዓማኒ የሰላም ሒደት እንጠብቃለን" ያለው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሊሳተፉ ይገባል ያላቸውን አካላት እና የሚኖራቸውን ሚና በመግለጫው ዘርዝሮ አቅርቧል።

"በጋራ ተቀባይነት ያላቸው አደራዳሪዎች እንዲሁም መተማመንን ለመገንባት የሚረዱ፣ ለሰላም ሒደቱ እምነት የሚፈጥሩ እና የስምምነቶችን ተግባራዊነት የሚከታተሉ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች" ሊሳተፉ እንደሚገባ የክልሉ መንግሥት ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪ "ለሰላም ሒደቱ ተዓማኒነት አስፈላጊ እገዛ እና ምክር የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች" ሊሳተፉ እንደሚገባ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በመግለጫው ጠቁሟል።

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ያስታወቀው የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የሥራ ጊዜ መራዘሙ ከተገለጸ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።  ከኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት 22 ወራት የዘለቀ ደም አፋሳሽ ውጊያ የገጠመው የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም በኦባሳንጆ እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት ትላንት ቅዳሜ የልዩ ልዑኩ የሥራ ዘመን መራዘሙን ባሳወቁበት መግለጫ በኦባሳንጆ "ሙሉ እምነት እንዳለኝ በድጋሚ አረጋግጣለሁ" ብለዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ጋር መገናኘታቸውን ጭምር የገለጹት ማኅማት "የኢትዮጵያውን ግጭት ለማብቃት በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በተዋጊዎቹ መካከል ለሚደረግ ድርድር የዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ አስፈላጊነት ላይ ተስማምተናል" ብለዋል።

በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ የሚመራው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በዛሬው መግለጫው ግጭት ከቆመ በኋላ "በድርድር አጠቃላይ የተኩስ አቁም ላይ መድረስ እና ለግጭቱ መነሾ የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት ሁሉን አካታች ፖለቲካዊ ውይይት ማካሔድ" እንደሚገባ አቋሙን አሳውቋል። 

በመግለጫው መሠረት ከህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ የተካተቱበት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ተደራዳሪ ቡድን ተቋቁሟል። ወደፊት በሚካሔዱ ድርድሮች የትግራይ ክልልን የመወከል ሥልጣን የተሰጠው ቡድን "ያለ ምንም መዘግየት ለመሰማራት ዝግጁ" እንደሆነም አስታውቋል። 

ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት በኩል ሊደረግ ይገባል የሚል አቋሙን በተደጋጋሚ ሲገልጽ የቆየው የፌድራል መንግሥት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰብሳቢነት የሚመሩት እና ሰባት አባላት ያሉት ተደራዳሪ ቡድን ባለፈው ሰኔ 2014 አቋቁሟል። 

ይኸ ተደራዳሪ ቡድን የፍትኅ ምኒስትሩ ጌድዮን ጢሞቲዎስ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጥሩነህ እና የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደሕንነት አማካሪ ሬድዋን ሑሴን የተካተቱበት ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የመረጃ ደኅንነት ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ብርሀኑ በቀለ፣ የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት ጌታቸው ጀምበር እና የብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ማዕከል ዘርፍ ከፍተኛ ኃላፊ ሑሴን አብዱልቃድር ከተደራዳሪዎቹ መካከል ይገኙበታል።

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW