የትግራይ ክልል ሊቃነ ጳጳሳት ኤጲስቆጶሳት ሹመት ዕቅድ
ረቡዕ፣ ግንቦት 16 2015
ትግራይ ክልል የሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት በቅርቡ 10 ኤጲስቆጶሳትን ለተለያዩ አህጉረ ስብከቶች እንደሚሾሙ አስታወቁ። በትግራይ ክልል የሚገኙ የሃይማኖቱ መሪዎች ከኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር የጀመሩት ግንኙነት እንዳለ ተጠይቀው አንድ አባት ሲመልሱ፦ «በእኔ በኩል ምንም አዲስ ነገር የለም» ብለዋል። የሃይማኖት አባቶቹ ከሃይማኖታዊ አጀንዳዎች በተጨማሪ የተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችንም ማንሳታቸው ተዘግቧል ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁእ አቡነ ማትያስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ደግሞ፦ «በትግራይ ክልል በሚገኙት አኅጉረ ስብከት ተቋርጦ የነበረው መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ግንኙነትን በተመለከተ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ ተደይሞ በሥራ ላይ የሚገኘው ልዑክ የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲቀጥል ምልዓተ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል» ብለዋል።
«መንበረ ሰላማ» በሚል ስያሜ የትግራይ ቤተክህነት ማቋቋማቸው ሲገልፁ የቆዩት በትግራይ የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ባለፉት ቀናት ካደረጉት ስብሰባ በኃላ አዳዲስ ውሳኔዎች ማስተላለፋቸው ትናንት ምሽት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። በሃይማኖት መሪዎቹ በተገለፀው መሰረት፥ በትግራይ የሚገኙ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት በቅርቡ አስር ኤጲስቆጶሳት ለተለያዩ አህጉረ ስብከቶች እንደሚሾሙ ዐስታውቀዋል። ይህም መንፈሳዊ አገልግሎትን ለማስፋት ያግዛል ብለዋል።
በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ምዕራብ እና ምዕራብ የትግራይ ዞኖች ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እንዳሉት፥ በተለያየ ቦታ ለሚገኝ ምእመን የሃይማኖት አባቶች መሾም ያስፈልጋል ብለን ጥናት ላይ ነበርን፣ አሁን ጥናቱ አልቋል፣ በቅርቡ አስር ኤጲስቆጶሳት በሀገር ውስጥ እና ውጭ የሚገኝ ምእመን እንዲያገለግሉ ይሾማሉ ሲሉ አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ መንበረ ሰላማ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኤጲስቆጶሳቱ ሹመት ለመስጠት የወሰነበት ምክንያት ያብራሩት የትግራይ ምስራቅና ደቡብ ዞኖች ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መርሐክርስቶስ፥ በመከራ ግዜ "ህዝባችን አባት ስለሚያስፈልገው በቅርበት የሚያገለግሉት የሃይማኖት አባቶች እንዲሾሙ" መወሰኑ አስረድተዋል።
አዳዲስ የሚሾሙት ኤጲስቆጶሳት በሀገር ውስጥ ለደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅ፣ ምዕራብ የትግራይ ዞኖችና ሌሎች የሚያገለግሉ ሲሆን ከሀገር ውጭ ደግሞ ሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና መካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የሃይማኖቱ ተከታዮች እንዲያገለግሉ ተልእኮ የሚሰጣቸው መሆኑ ተገልጿል። የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር የታቀደ አልያም የተጀመረ ግንኙነት ስለመኖሩ ከዶቼቨሌ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ "ምንም አዲስ ነገር የለም" ብለዋል።
ከሃይማኖታዊ አጀንዳዎች በተጨማሪ የተለያዩ ማሕበራዊ ጉዳዮች ያነሱት ጳጳሳቱ፥ በጦርነቱ ምክንያት ከመኖርያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች፣ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በጋራ በመስራት ወደ ቀዬአቸው ሊመልሷቸው ተማፅነዋል።
ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውጭ ሌሎች በትግራይ ያሉ ቤተእምነቶ፥ በኢትዮጵያ ካሉ ተመሳሳይ የሃይማኖት ተቋማት ጋር ያላቸው ግንኙነት ማቋረጣቸው አስቀድመው ገልፀው ነበር።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ