1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ትምህርትኢትዮጵያ

የትግራይ ክልል መምህራን ደሞዝ እንዲከፈላቸው የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በየነ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 8 2017

ፍርድ ቤቱ "3ተኛ ተከሳሽ የ50 ሺህ 720 የትግራይ ክልል መምህራን የ17 ወራት ደሞዝ፥ 5 ቢልየን 473 ሚልዮን 534 ሺህ 614 ብር የመክፈል ግዴታ አለበት ተብሎ ውሳኔ ተሰጥቷል፤ 4ተኛ ተከሳሽ የ50 ሺህ 720 መምህራን የ12 ወር ደሞዝ 3 ቢልየን 863 ሚልየን 671 ሺህ 492 ብር የመክፈል ግዴታ አለበት ተብሎ ውሳኔ ተሰጥቷል" ብሏል።

ለትግራይ ክልል መምህራን ደሞዝ እንዲከፈላቸው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በየነ
ለትግራይ ክልል መምህራን ደሞዝ እንዲከፈላቸው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በየነምስል፦ Million Haileselassie/DW

የትግራይ ክልል መምህራን ደሞዝ እንዲከፈላቸው የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በየነ

This browser does not support the audio element.

የትግራይ ክልል መምህራን ማሕበር በፌደራሉ መንግስት እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ላይ የመሰረተው ክስ ሲመለከት የቆየው የትግራይ ከፍተኛ ፍርድቤት፥ የፌደራል መንግስቱ እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የአስተማሪዎች የ17 ወራት ደሞዝ እንዲከፍል ውሳኔ አስተላለፈ። ፍርድ ቤቱ የፌደራሉ መንግስቱ እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አጠቃላይ 5 ነጥብ 4 ቢልዮን ብር የመምህራን ደሞዝ እንዲከፍሉ ውሳኔ ሰጥቷል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ መምህራን የ17 ወራት ደሞዝ እንዲከፈላቸው በመጠየቅ በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር እና የፌደራል መንግስቱ ላይ የመሰረቱት ክስ፥ ላለፉት ስምንት ወራት በትግራይ ከፍተኛ ፍርድቤት ሲታይ ከቆየ በኃላ በትላንትናው ዕለት ውሳኔ ተሰጥቶበታል። የትግራይ መምህራን ማሕበር፥ በትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ፣ የትግራይ ክልል ፋይናንስ ቢሮ፣ የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር እና የኢትዮጵያ ገንዘብና ፋይናንስ ሚኒስቴር ላይ የመሰረተው ይህ ክስ፥ የ50 ሺህ 720 አስተማሪዎች የ2014 እና 2015 ዓመተምህረት የአስራ ሰባት ወራት ደሞዝ እንዲከፈላቸው የሚጠይቅ ነው። ትላንት የትግራይ ከፍተኛ ፍርድቤት በዋለው ችሎት አንደኛ ተከሳሽ የሆነው የትግራይ ትምህርት ቢሮ በዚህ የደሞዝ ጉዳይ ተጠያቂነት የለውም የሚል ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን፥ ሁለተኛ ተከሳሽ የትግራይ ፋይናንስ ቢሮ፣  ሶስተኛ ተከሳሽ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እና የገንዘብ ሚኒስቴር ላይ ግን ፍርድቤቱ ባስተላለፈው ውሳኔ በጋራ እና በተናጠል ተጠያቂ ናቸው ብሏቸዋል።

በትግራይ የመምህራንና መንግሥት ሠራተኞች የ18 ወራት ውዝፍ ደሞዝ አቤቱታ

ፍርድ ቤቱ  "ሶስተኛ ተከሳሽ የ50 ሺህ 720 የትግራይ መምህራን የ17 ወራት ደሞዝ፥ 5 ቢልየን 473 ሚልዮን 534 ሺህ 614 ብር የመክፈል ግዴታ አለበት ተብሎ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ተሰጥቷል። አራተኛ ተከሳሽ የ50 ሺህ 720 መምህራን የ12 ወር ደሞዝ ፥ 3 ቢልየን 863 ሚልየን 671 ሺህ እና 492 ብር የመክፈል ግዴታ አለበት ተብሎ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ተሰጥቷል" ብሏል።

ለትግራይ ክልል መምህራን ደሞዝ እንዲከፈላቸው ብይን የተላለፈበት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ታዳሚዎችምስል፦ Million Haileselassie/DW

የትግራይ መምህራን ማሕበር ጠበቃ ዳዊት ገብረሚካኤል፥ በፍርድቤት ውሳኔ መሰረት በሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ የተቀመጡ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እና የፌደራል መንግስቱ ገንዘብ ሚኒስቴር ለተወሰነው የአስተማሪዎች ደሞዝ ክፍያ በጋራ እና በተናጠል ተጠያቂዎች ሆነዋል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ ጠበቃ ዳዊት የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ክስ እንዳይመሰረትበት የሚከለክል ሕገመንግስት የሚፃረር አዋጅ አውጥቶ መቆየቱን በመግለፅ፥ በክስ ሂደቱ ይህ የጊዚያዊ አስተዳደሩ አዋጅ ጭምር እንዲሻር መደረጉን አንስተዋል።

የትግራይ መምህራን በፌደራሉ መንግስትና በክልሉ አስተዳደር ላይ ክስ መሰረቱ መባሉ

የፍርድቤቱን ውሳኔ በአዎንታ እንደተቀበለው የትግራይ መምህራን ማሕበር ገልጿል። የማሕበሩ ፕሬዝደንት መምህርት ንግስቲ ጋረድ የትግራይ መምህራን ማሕበር የአስተማሪዎችን መብት ለማረጋገጥ ሁሉንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን በማንሳት ይህ የፍርድቤት ውሳኔ ደግሞ 'ታሪካዊ' የሚባል ነው ብለውታል።

የትግራይ መምህራን ማሕበር የፍርድቤቱ ውሳኔ በአፋጣኝ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚጠብቅም አመልክቷል። መምህርት ንግስቲ "የፍርድቤቱ ውሳኔ በአጭር ግዜ ተግባራዊ መሆን አለበት፥ ይህ ካልሆነ ውሳኔው በአስተማሪው እጅ ላይ ነው" ብለዋል።

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ 

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW