የትግራይ ክልል አዲስ ፕሬዝደንት አዲስ ሥራ አስፈጻሚ እየጠበቀ ነው-ግጭት የማቆም ሥምምነቱስ?
ሰኞ፣ ሚያዝያ 26 2018
የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ግጭት የማቆም ሥምምነት ከተፈራረሙ ከሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ገደማ በኋላ የትግራይ ክልል አዲስ ፕሬዝደንት፣ አዲስ መስተዳድር እየጠበቀ ነው። በጳጉሜ 2012 በተካሔደ ምርጫ የተቋቋመው የቀድሞው የትግራይ ክልል ምክር ቤት በመጪዎቹ ቀናት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።
የምክር ቤቱ ወደ ሥራ መመለስም ይሁን የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች የትግራይ ክልል እና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ቀጣይ ግንኙነት ምን እንደሚመስል የሚበይኑ ይሆናል። ይህን ምዕራፍ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ስትራቴጂክ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ሚካኤለ ክህሽን “የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ” ሲሉ ይገልጹታል።
“ከጦርነቱ በፊት የነበረው ሁኔታ አሁን በቀጥታ እየተስተዋለ ነው” የሚሉት ዶክተር ሚካኤለ “ህወሓት ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለማስወገድ፣ ለማፍረስ እና የራሱን መንግሥት ለማቋቋም የሚሞክር ከሆነ” የፌደራል መንግሥት “ሕገ-መንግሥታዊ ጥሰት” ብሎ ሊፈርጅ እንደሚችል ተናግረዋል።
ፌድራል መንግሥት “ህወሓት ማቋቋም የሚችለው ሕጋዊ የሆነ መንግሥት የለም” የሚል ድምዳሜ ላይ ከደረሰ ጣልቃ ሊገባ እንደሚችልም ገልጸዋል። “ስለዚህ የፌደራል መንግሥቱ እና የህወሓት ጦርነት የማይቀር ነው” ሲሉ ሥጋታቸውን አጋርተዋል።
የሚመለሰው ምክር ቤት የቱ ነው?
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት “ሕገ-ወጥ” ብሎ የፈረጀው የትግራይ ክልል ምርጫ የተካሔደው ጳጉሜ 4 ቀን፣ 2012 ነበር። በምርጫው አምስት ፓርቲዎች ቢሳተፉም ህወሓት ከተሰጡ ድምጾች 98 በመቶ በማግኘት አሸንፏል። በውጤቱ መሠረት የተቋቋመው የክልል ምክር ቤት 190 በድምጽ የሚሳተፉ እና 15 በድምጽ የማይሳተፉ አባላት እንደነበሩት በወቅቱ ተገልጿል።
ምክር ቤቱ መስከረም 14 ቀን 2013 ባካሔደው ጉባኤ የህወሓት ሊቀ-መንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልን የትግራይ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አድርጎ መርጦ ነበር። ይሁንና ምክር ቤቱም ሆነ ደብረ ጽዮን የሚመሩት ሥራ አስፈጻሚ በፌደራል መንግሥት ተቀባይነት አላገኙም።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በመስከረም 2013 መጨረሻ ከትግራይ ክልል ምክር ቤት እና ከሥራ አስፈፃሚው ጋር ያለው ግንኙነት እንዲቋረጥ ወሰነ። የበጀት ድጎማም አቆመ።
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከስድስት ዓመታት ገደማ በፊት በተካሔደ ምርጫ የተመሠረተው የትግራይ ክልል ምክር ቤት “ወደ ሥራ እንዲመለስ” መወሰኑን በይፋ ያሳወቀው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ሚያዝያ 7 እና 8 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ካካሔደው ስብሰባ በኋላ ነበር።
ውሳኔውን በቀዳሚነት ያጸደቀው “የትግራይ ብሔራዊ መኸተ ኮሚቴ” እንደሆነ የህወሓት ቃል አቀባይ ሚኪኤለ አስገዶም ከመቐለ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ሒዋነ ከፓርቲያቸው አባላት ጋር በተደረገ ስብሰባ ላይ አስረድተዋል። ኮሚቴው ከትግራይ ሠራዊት አመራሮች፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ እና የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የተውጣጡ ዘጠኝ አባላት ያሉት ነው።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እና በርካታ አባላት ያሉት “የትግራይ መኸተ ምክር ቤት” ለውሳኔው ይሁንታ መስጠታቸውን ቃል-አቀባዩ አስረድተዋል። መቐለ እና ሒዋነን ጨምሮ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ባለፉት ሣምንታት በተለያዩ የትግራይ ከተሞች ባካሔዷቸው ውይይቶች የውሳኔውን አንድምታ እና አስፈላጊነት ለፓርቲው አባላት፣ ለነዋሪዎች እና ለመንግሥት ሠራተኞች ሲያስረዱ ሰንብተዋል።
ግጭት የማቆም ሥምምነቱ ፈርሷል - የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ተኽላይ ገብረ መድኅን
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥር ከሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች ጋር በተደረገ ውይይት የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ተኽላይ ገብረ መድኅን ግጭት የማቆም ሥምምነቱን “ፌደራል መንግሥት አፍርሶታል” ሲሉ ተደምጠዋል። “የፕሪቶሪያ ውል የለም፣ ፈርሷል። ራሳችንን የሚያዳክም አሬንጅመንት ይዞ መሔድ አይጠቅመንም” ያሉት አቶ ተኽላይ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በግጭት የማቆም ሥምምነቱ የተቋቋመ በመሆኑ ዕጣ-ፈንታው “ፈርሷል” ካሉት ውል እንደማይለይ ገልጸዋል።
“የፕሪቶሪያ ውል ፈርሷል፣ የለም። ይኸን ተቀብለን እንቀጥል ከተባለ ያው ጊዜያዊ አስተዳደሩም የዚያ አሬንጅመንት ነው። የሱ አሬንጅመንት ስለሆነ የለም። ሊኖርም ዐይችልም። እንደማይኖር አስበን፣ ተቀብለን መሔድ ይገባናል” በማለት የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ተኽላይ አብራርተዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩን ከማስቀጠል ወይም ከማስተካከል፣ አዲስ የሽግግር መንግሥት ከማቋቋም፣ ወይም ምርጫ ማካሔድ ይልቅ “በፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት የፈረሰውን መንግሥት ወደ ቦታው መመለስ” የተሻለ አማራጭ እንደሆነ አስረድተዋል። ውሳኔው የተሻለ አማራጭ የሚሆነው ምክር ቤቱ “ሕጋዊ” በመሆኑ እና ሕዝባዊ “ተቀባይነት” ስላለው እንደሆነም ሲናገሩ ተደምጧል።
ዶቸ ቨለ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና ከመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት በኢ-ሜይል እና ቀጥታ ስልክ በመደወል በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የትግራይ ክልል አመራሮች ከኤርትራ እና በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሰው ፋኖ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የፌድራል መንግሥት ማረጋገጫ እንዳለው ማስታወቁን ባለፈው ሣምንት የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የፌድራል መንግሥት የመረጃ ምንጭ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ያቀረቡት ማረጋገጫ ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች አንዱ የሆኑት ዶክተር አዲስ ዓለም ባሌማ የተሳተፉበት ውይይት የድምጽ ቅጂ ነው።
በዘገባው መሠረት ዶክተር አዲስ አለም በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሰው የፋኖ ታጣቂ ቡድን ጋር “ለመተባበር” እና ከኤርትራ ጋር የንግድ ልውውጥ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። አዲስ ዓለም የድምጽ ቅጂው ትክክለኛነት ባያስተባብሉም የፌድራል መንግሥት የሰጠው ትርጓሜ የእርሳቸውን አገላለጽ እንደማያንጸባርቅ ምላሽ ሰጥተዋል። ፓርቲያቸው አሁንም “ለሰላም እና እና መረጋጋት ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ” እንደሆነም ተናግረዋል።
አምባሳደር አዲስ ዓለምን ጨምሮ የፓርቲው አመራሮች እና የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦች ባለፉት ሣምንታት የሰጧቸው አስተያየቶች ህወሓት ከፌደራል መንግሥት ጋር ከተፈራረመው ግጭት የማቆም ሥምምነት በይፋ ራሱን ማራቅ እንደመረጠ የሚጠቁሙ ናቸው። ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የትግራይን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉ አንድ የመቐለ ነዋሪ ውይይቶቹ በመጪዎቹ ወራት ምን ሊከሰት እንደሚችል ጥቆማ ሰጥቷቸዋል።
አንድ ከፍተኛ የጦር አመራር “ከክረምት በፊት ትዕግሥታችን አልቋል፤ ሁሉን ነገር እንጨርሳለን” ሲሉ መደመጣቸውን በምሳሌነት የጠቀሱት የመቐለ ነዋሪ “ጽምዶ” የሚል ስያሜ የተሰጠውን ጨምሮ ከክልሉ ውጪ ከሚገኙ ኃይሎች ጋር ሲደረጉ የቆዩ ግንኙነቶች እስካሁን ከነበረው የተለየ አካሔድ ሊኖር እንደሚችል የሚጠቁሙ እንደሆኑ ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተካሔዱ ውይይቶች “ምክር ቤታችንን በመመለስ ሬዚስታንሳችንን እናስቀጥላለን” በሚል መፈክር የተካሔዱ መሆናቸው ይኸንንው ያሳያሉ።
ህወሓት ምክር ቤቱ “ወደ ሥራ እንዲመለስ” መወሰኑን ያሳወቀው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ታደሰ ወረደን የሥልጣን ዘመን ለተጨማሪ አንድ ዓመት ባራዘሙ በሣምንት ልዩነት ነው። ህወሓት የፌደራል መንግሥቱን ውሳኔ አልተቀበለም።
የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካኝነት ለክልል ምክር ቤት እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እስኪካሔድ ድረስ በፈራሚዎቹ ፖለቲካዊ ውይይት አማካኝነት ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋም ይደነግጋል።
የመቐለ ዩኒቨርሲቲው መምህር ዶክተር ሚካኤለ ፌደራል መንግሥት የሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደን የሥልጣን ዘመን ለአንድ ዓመት ማራዘሙም ይሁን ህወሓት የሥራ ዘመኑ በ2017 ያበቃ የነበረውን የክልል ምክር ቤት ወደ ሥራ እንዲመለስ ያሳለፈው ውሳኔ ግጭት የማቆም ሥምምነቱን ይጥሳሉ የሚል አቋም አላቸው።
ዶክተር ሚካኤለ “እነዚህ ሁለት አካላት የፕሪቶሪያ [ግጭት የማቆም ሥምምነትን] አክብረውም አያውቁም። ተፈናቃዮች ሊመለሱ አልቻሉም” ሲሉ ይተቻሉ። “አከራካሪ የተባሉት ቦታዎችን [ጉዳይ] በሕገ-መንግሥቱ መሠረት መፍታት አልቻሉም። ከክልሉ ውጪ ያሉ ኃይሎች እነ ኤርትራ በሙሉ አልወጣም። የአማራ ኃይሎች በምዕራብ ትግራይ አሉ” ሲሉ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት ልዩነቶቻቸውን “በሕገ-መንግሥቱም በፖለቲካ ውይይትም መፍታት አልቻሉም” ሲሉ ተናግረዋል።
ሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ አቶ ጌታቸው ረዳን ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ሆነው ሲተኩ ልክ እንደ አሁኑ ከፍተኛ ውጥረት ተከስቶ ነበር። የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ጭምር የሆኑት ሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ ተተኪያቸውን ለመምረጥ ህወሓት ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ባለፈው ሣምንት አረጋግጠዋል።
ይሁንና በፓርቲው አካሔድ ደስተኛ አይደሉም። ሥልጣን ማስረከብ እንደሚኖርባቸው ህወሓት ካሳወቀ በኋላ “ርዕዮት” ከተባለ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ፌደራል መንግሥት ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል። የሥልጣን ጉዳይን በተመለከተ ግን “የማስረክበው ነገር የለኝም” የሚል አቋማቸውን አሳውቀዋል።
የ67 ዓመቱ የጦር መኮንን ሥልጣኑን ከተቆናጠጡም በኋላ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ግጭት የማቆም ሥምምነቱን ለማስተግበር ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ ኃላፊነቶቹን ለመወጣት ሲቸገር ቆይቷል። በተለይ የበጀት መቋረጥ፣ የጥሬ ገንዘብ እና የነዳጅ እጥረት የክልሉን ነዋሪዎች፣ ኢኮኖሚ እና ጊዜያዊ አስተዳደሩን ክፉኛ እንደተፈታተኑ ታደሰ ወረደ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ ከኃላፊነታቸው ከተሰናበቱ እርሳቸውን የሚተካው የትግራይ ክልል ፕሬዝደንት ከፊቱ የሚጠብቁት ውስብስብ ችግሮች ናቸው። ዶክተር ሚካኤለ “ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔርም መጡ፣ ዶክተር ደብረጽዮንም መጣ፣ አማኑኤል አሰፋም ወደ መሪነት መጣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ግንኙነት እስከሌለ ድረስ ወይ የፕሪቶሪያ ሥምምነት እስካልተከበረ ድረስ የትም ሊኬድ አይችልም” የሚል ዕምነት አላቸው።
የፌደራል መንግሥት አዲስ የሚመረጠውን የትግራይ ክልል ፕሬዝደንት “እንደ መሪ ተቀብሎ የማስተናገድ ዕድሉ በጣም አነስተኛ ነው” የሚሉት የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደን ጊዜያዊ አስተዳደር የተፈታተኑ ችግሮች መፍትሔ ካላገኙ “አዲስ የሚመጣ መንግሥት ወይም ግለሰብ እንደ ፕሬዝደንት ምንም የሚፈይደው ነገር” እንደማይኖር ገልጸዋል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት የመቐለ ነዋሪ ግን “ግለሰባዊ አቅም” ወሳኝ ቢሆንም የአዲሱ ፕሬዝደንት ሚና ህወሓት በሚከተለው ፕሮግራም እንደሚወሰን ያምናሉ። ከዚያ በተጨማሪ ዘጠኝ አባላት ያሉት የመከተ ኮሚቴ፣ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እና በርካታ ወታደራዊ አዛዦች የተካተቱበት የመከተ ምክር ቤት በትግራይ ክልል አመራር ውስጥ ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ አወቃቀር ምክንያት አዲስ የሚመረጠው ፕሬዝደንት “ፕሮግራሙን ያስፈጽመዋል? አያስፈጽመውም፤ ግጭቱን ምን ያህል ይመራዋል? አይመራውም ነው እንጂ ብዙ ለውጥ የሚኖረው አይመስለኝም” ሲሉ የመቐለው ነዋሪ አስረድተዋል።
ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 የተካሔደው ጦርነት በሥምምነት ከተገታም በኋላ ሌላ ጦርነት ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ሥጋት ሲፈጠር የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ጥር ወር በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተፈጠረ ግጭት ወደ ትግራይ የሚደረጉ በረራዎች እንዲሰረዙ እስከ ማስገደድ ደርሶ ነበር።
የመቐለው ነዋሪ በእርግጥ እንደ አዲስ የሚቀሰቀስ ጦርነት ኢኮኖሚያዊ “ድቀት” እንደሚያስከትል አላጡትም። ጦርነት መቀስቀሱ እንደማይቀር ሥጋት ቢጫናቸውም በንግግር ሊፈታ የሚችለው ግን ፌዴራል መንግሥት በግጭት ማቆም ሥምምነቱ አተገባበር ረገድ “የአቋም ለውጥ” ካመጣ ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። “የፌድራል መንግሥቱ በቅንነት ፕሪቶሪያን የማስፈጸም አዝማሚያ ካሳየ” ውጥረቱ በውይይት ሊፈታ እንደሚችል ተናግረዋል።
“ካልሆነ ግን ተፈናቃዮቹን ከዚህ በኋላ ‘ታገሱን’ ማለትም አትችልም” የሚሉት የመቐለው ነዋሪ ከዚህ ቀደም “እየሞከርን ነው” በሚል ከክልሉ መሪዎች የተሰጡ መልሶች “የሰለቹበት ነገር ነው” ሲሉ አስረድተዋል። “ስለዚህ እንደዚህ ዐይነት ትዕግሥት ይኖራል ብዬ አላስብም። ‘ያዋጣል? አያዋጣም?’ ‘ምን ያህል ኪሣራ ይመጣል? በስንት ኪሣራ ያልቃል?’ የሚለውን ነው መወያየት የሚቻለው እንጂ የውይይት አቅጣጫዎች የሚሳኩ አይመስለኝም” በማለት የእርሳቸውን አተያይ አስረድተዋል።
የህወሓትን አካሔድ በጽኑ የደገፉ የመኖራቸውን ያክል የተቃወሙም አልጠፉም። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ ከጦርነቱ በፊት የነበረው የክልል ምክር ቤት እንዲመለስ ህወሓት ያሳለፈው ውሳኔ ግጭት የማቆም ሥምምነቱን የሚጥስ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሁለተኛ ዙር የሚቀሰቀስ ጦርነት ትግራይን ከማበርታት እና መልሶ ከመገንባት ይልቅ “ያወድማታል” ያሉት ጌታቸው “የጥፋቱን ዳፋ እንደቀደመው ጦርነት ሁሉ የሚሸከሙት የትግራይ ወጣቶች” እንደሚሆኑ አስጠንቅቀዋል።
ሁለተኛ ዙር ጦርነት የሚያስከትለው ቀጠናዊ ሥጋት
በትግራይ የሚፈጠር ተጨማሪ ቀውስ ከ2015 ጀምሮ በአማራ ክልል በፌድራል መንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በመካሔድ ላይ ከሚገኘው ጦርነት ተደማምሮ የበለጠ ሊወሳሰብ ይችላል። ለሦስት ዓመታት ገደማ ከአማራ ክልል እና ከፌደራል መንግሥት ጋር ሲዋጉ የቆዩ የፋኖ አደረጃጀቶች ምን ዐይነት ሚና እንደሚኖራቸው ለጊዜው አይታወቅም።
በትግራይ ጦርነት ወቅት ለኢትዮጵያ መንግሥት ወግና የተዋጋችው ኤርትራ ግጭት የማቆም ሥምምነት ከተፈረመ በኋላ የኃይል አሰላለፏን ቀይራለች። የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት በፕሪቶሪያው ሥምምነት ውስጥ ባለመሳተፉ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት ሻክሯል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በአሰብ ወደብ ላይ ያነሳው የይገባኛል ጥያቄ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ወደ ለየለት ፍጥጫ አሸጋግሮታል።
ዶክተር ሚካኤለ ክህሽን “በትግራይ አካባቢ የሚነሳው ጦርነት ትግራይ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም”። ከትግራይ ውጪ በአፍሪካ ቀንድ የራሱ ከፍተኛ የሆነ ዞናዊ ቀውስ ነው የሚያመጣው” ሲሉ ተናግረዋል።
ሦስት ዓመታት በደፈነው የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በተቃራኒ የተሰለፉ ሆነው ይታያሉ። ኤርትራ በሉቴናንት ጄኔራል አብደል ፋታኅ አል-ቡርኻን የሚመራውን የሱዳን ብሔራዊ ጦር በይፋ ትደግፋለች። የኢትዮጵያ መንግሥት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በመሐመድ ሐምዳን ደጋሎ ለሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የምታደርገውን ድጋፍ በማመቻቸት ክስ ቀርቦበታል። የምዕራብ ትግራይ አካባቢ ለኤርትራ እና ለሱዳን ድንበሮች ያለው ቅርበት እንዲሁም ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በአካባቢው ሊቀሰቀስ የሚችልን ጦርነት አስጊ ያደርገዋል።
ማን ይገላግላል?
ከህወሓት ውሳኔ በኋላ ያንዣበበው ሥጋት ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች የበዙበት ቢሆንም የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት አላጣም። የአውሮፓ ኅብረት “በትግራይ ክልል እየተፈጠሩ ያሉ ሁኔታዎች እጅግ አሳሳቢ” እንደሆኑ ባለፈው ሣምንት አስታውቋል። ጦርነት ሲቀሰቀስ ያቋረጠውን የበጀት ድጎማ መልሶ የጀመረው ኅብረቱ በቃል-አቀባዩ በኩል ባወጣው መግለጫ “በአፋጣኝ ውጥረቱ እንዲረግብ” እና “ግጭት የማቆም ሥምምነቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ማንኛውም እርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲወገዱ” ጥሪ አቅርቧል።
ተመሳሳይ ጥሪ ያቀረበው በአዲስ አበባ የሚገኘው የብሪታኒያ ኤምባሲ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት ወደ ግጭት የማቆም ሥምምነቱ ትግበራ ውይይት እንዲመለሱ አሳስቧል። ኤምባሲው በግልጽ የህወሓትን ውሳኔ ባይጠቅስም “ግጭት ከማቆም ሥምምነቱ መንፈስ ወይም ማዕቀፍ የማይጣጣሙ እርምጃዎችን” እንደማይደግፍ አቋሙን ገልጿል።
በአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ግሪጎሪ ሚክስ “በትግራይ ዳግም ግጭት መቀስቀስ ማንንም አይጠቅምም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ዴሞክራቱ ፖለቲከኛ ህወሓት እና የፌደራል መንግሥት በ2015 ወደተፈረመው ግጭት የማቆም ሥምምነት ትግበራ ፊታቸውን እንዲያዞሩ እና ውጥረቱን “የሚያባብሱ ማናቸውም እርምጃዎችን ከመውሰድ እንዲቆጠቡ” አሳስበው ነበር።
ዩናይትድ ስቴትስ የፕሪቶሪያ ሥምምነት ሲፈረም ከፍ ያለ ጫና በማሳደር ላቅ ያለ ሚና ብትጫወትም የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ለአፍሪካ የሚሰጠው ትኩረት ተቀይሯል። ከዚያ ባሻገር የትራምፕ አስተዳደርን ትኩረት የሚሻ አንገብጋቢ ጉዳይ አለ።
“አሜሪካ በኢራን ጦርነት ሥራ በዝቶባታል። የዓለም አቀፉም ማኅበረሰብ ትኩረት በኢራን፣ የአሜሪካ እና የእስራኤል ጦርነት ላይ ነው” የሚሉት ዶክተር ሚካኤለ “ጦርነቱ ቢቀሰቀስ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና፣ ሚና በጣም አነስተኛ” ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛነት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆን በቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዝደንት ጃክያ ኪክዌቴ የተካው የአፍሪካ ኅብረት እንደ ዋና አደራዳሪነቱ እስካሁን ያለው ነገር የለም። ዶክተር ሚካኤለ ግን ኅብረቱ የግጭት ማቆም ሥምምነቱን አተገባበር በቅጡ መከታተል እንደሚኖርበት ያምናሉ።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “በፋይናንሺያል ተጽዕኖ፣ በዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ የራሳቸው የሆነ ከፍተኛ ጫና ፈጥረው እነዚህ ሁለት አካላት ጦርነቱን እንዳይጀምሩ ማድረግ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ነገር ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ይሁንና አይበልና ጦርነት ቢቀሰቀስ “ገፈት ቀማሹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ ገፈት ቀማሹ የትግራይ ሕዝብ ነው። ስለዚህ እነዚህ ሁለት አካላት ናቸው ወደ መፍትሔ መምጣት ያለባቸው” ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል።
አርታዒ ሸዋዬ ለገሠ