የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የፍርድ ቤቱን ዉሳኔ አገደ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 24 2017
የትግራይ ክልል መምህራን ዉዝፍ ደሞዛቸዉ እንዲከፈል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አዲስ ደንብ በማውጣት አገደው። የጊዚያዊ አስተዳደሩ ውሳኔ በርካቶችን ያስቆጣ ሆንዋል። የትግራይ መምህራን ማሕበር ጠበቃ አዲሱን ደንብ በመቃወም ይግባኝ እንደሚሉ አስታዉቀዋል።ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ ከመቀሌ።
የትግራይ መምህራን ማሕበር የጦርነቱ ወቅት የ17 ወራት ደሞዝ ለመምህራን እንዲከፈል በማለት በፌደራሉ መንግስት እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ላይ ክስ መስርቶ ሲከራከር ከቆየ በኃላ ባለፈው ሚያዝያ ወር የትግራይ ጠቅላይ ፍርድቤት የፌደራል መንግስቱ እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የአስተማሪዎቹ የ17 ወራት ደሞዝ እንዲከፍል ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል። ፍርድ ቤቱ የፌደራሉ መንግስቱ እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አጠቃላይ 5 ነጥብ 4 ቢልዮን ብር የመምህራን ደሞዝ እንዲከፍሉ ውሳኔ ከሰጠ በኃላ በውሳኔ አፈፃፀም ሂደት ላይ የነበረው የትግራይ መምህራን ማሕበር ክስ ከትላንት በስትያ በነበረው ችሎትም በትግራይ ፋይናንስ ቢሮ የባንክ አካውንት ታግዶ የነበረው 500 ሚልዮን ብር ለመምህራኑ እንዲከፈል ተጨማሪ ውሳኔ ሰጥቶ ነበረ።
ይሁንና በትላንትናው ዕለት ሐምሌ23 የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ይህ የትግራይ ከፍተኛ ፍርድቤት ውሳኔ የሚሽረ እና በሕግ ባለሙያዎች ተቃውሞ የቀረበበት ደንብ አውጥቷል። የትግራይ መምህራን ማሕበር ጠበቃ አቶ ዳዊት ገብረሚካኤል ለዶቼቨሌ እንዳሉት ግዚያዊ አስተዳደሩ እስከመጨረሻ በፍርድ ቤት ክርክር ላይ ከቆየ በኃላ፥ በሂደቱ ሲሸነፍ ሌላ ደንብ በማውጣት የሕግ ጥሰት መፈፀሙ ገልፀዋል።
የትግራይ ጠቅላይ ፍርድቤት ያስተላለፈው ውሳኔ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ በየፊናቸው የሚጠበቅባቸውን የገንዘብ መጠን ለመምህራን ደሞዝ እንዲከፍሉ ያዝዛል። የትግራይ መምህራን ማሕበር ጠበቃ አቶ ዳዊት ገብረሚካኤል እንደሚሉት፥ ግዚያዊ አስተዳደሩ 'ደንብ' በማውጣት ይህ የፍርድቤት ውሳኔ መቀየር እንደማይችል የሚገልፁ ሲሆን በሀገሪቱ ሕጎች መሰረት ቀጣይ እርምጃዎች እንደሚወሰዱም አስታውቀዋል።በዚሁ ጉዳይ ዙርያ ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ