1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር ወቅታዊ መግለጫ

ሐሙስ፣ መጋቢት 28 2015

የኤርትራ ጦር በትግራይ በራሱ ከሚፈፅማቸው ወንጀሎች በተጨማሪ የተለያዩ የሚያስታጥቃቸው ሀይሎች እያሰማራ ነው ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰሰ። አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር ከአጓራባች የአማራ እና አፋር ክልሎች ጨምሮ ከሁሉም ኃይሎች ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚፈልግ ገልፀዋል።

Äthiopien Mekele | Getachew Reda, Interimspräsident der Tigray-Region
ምስል Million H. Silase/DW

«በመግለጫው በርካታ ጉዳዮች ተነስተዋል»

This browser does not support the audio element.

የኤርትራ ጦር በትግራይ በራሱ ከሚፈፅማቸው ወንጀሎች በተጨማሪ የተለያዩ የሚያስታጥቃቸው ሀይሎች እያሰማራ ነው ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰሰ። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የኤርትራ መንግሥት የሚያስታጥቃቸው «ትንሣኤ» እና «ዴምህት» የተባሉ ኃይሎች ትግራይ ውስጥ በዝርፍያ እንደተሰማሩ እና ይኽንንም የፌደራሉ መንግሥት እንዲያውቀው መደረጉንም ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪ አቶ ጌታቸው የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር ከአጓራባች የአማራ እና አፋር ክልሎች ጨምሮ ከሁሉም ኃይሎች ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚፈልግ ገልፀዋል።  

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርእሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት ወቅታዊ ጉዳዮች አስመልክተው ለሀገር ውስጥ እና የውጭ መገናኛ ብዙሐን በሰጡት መግለጫ የተለያዩ አጀንዳዎች ዳሰዋል። ከጦርነቱ በኋላ በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረት በትግራይ አስተዳደር እና የፌደራሉ መንግሥት መካከል ስላለው ግንኙነት ያነሱት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ ግንኙነቱ እና መተማመኑ በሂደት እየተጠናከረ ስለመሆኑ አመልክተዋል። በፌደራል መንግሥት ይሁንታ የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምን ያክል መሆኑ ባይጠቅሱም ሥራ ሊያስጀምር የሚያስችል በጀት መገኘቱን የተናገሩት አዲሱ ርእሰ መስተዳድር፥ በቀጣይም ያለፉት ሁለት ዓመታት ድጎማ ከፌዴራሉ መንግሥት እንደሚጠየቅ ገልፀዋል። አቶ ጌታቸው በንግግራቸው «የተለቀቀልን በጀት ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል አቅም የሚፈጥርልን ነው የሚል እምነት አለኝ። ተቋርጠው የነበሩ የውኃ፣ ሴፍቲኔት ጨምሮ በርካታ በቢልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ፕሮጀክቶች እንደሚቀጥሉ ተግባብተናል። ቶሎ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችል ሁኔታ እንፈጥራለን» ብለዋል።

ምስል Million Hailesilassie/DW

ከበጀት ጋር ተያይዞ በክልሉ መንግሥት ሠራተኞች ስለሚጠበቀው የደሞዝ ጉዳይ የተናገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ የተከማቸ ደሞዝ ይከፈለናል የሚል በትግራይ የመንግሥት ሠራተኞች ያለው ግምት የተሳሳተ ነው ብለዋል። ከፌዴራሉ መንግሥት በተጨማሪ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሌሎች ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት በተመለከተም፤ ርእሰ መስተዳድሩ «ከአጎራባች የአማራ እና አፋር ክልሎች ጨምሮ ከሁሉም ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ፍላጎትና ዝግጁነት አለን» ነው ያሉት። በተለይ ከአማራ ክልል ጋር ስላለው ግንኙነት ያነሱት አቶ ጌታቸው የክልሉ አስተዳደር ችግሮችን በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ለመፍታት እንደሚፈልግ መግለፁን የሚበረታታ ያሉት ሲሆን፣ ማንኛውም ሀይል ከትግራይ የወሰደው መሬት ይሁን ንብረት ግን መመለስ እንደሚገባው ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር መልካም ግንኙነት መጀመሩን የገለፁ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ለትግራይ በግብርናው እና ትምህርት ዘርፎች ለመደገፍ ቃል መግባቱን፣ በአንዳንዱም ተግባራዊ ሥራ መጀመሩን አንስተዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አዲስ ካቢኔ

ከዚህ በተጨማሪ በህወሐት እና ኦነግ መካከል ስለቆየው ግንኙነት ዘለቄታ ጉዳይ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው ረዳ «ከOLA ጋር ያላችሁ ግንኙነት የሚል፣ የፌደራሉ መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ይሁን ሌሎች ትጥቅ ያላቸው ኃይሎች ጋር ያለውን ልዩነት በሰላም ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑ እንረዳለን። ችግሮችን በኃይል ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ትክክል አለመሆኑ እናምናለን። የፌደራሉ መንግሥት ከኦሮሞ ታጣቂዎች ጋር የሚያደርገውን የሰላም ንግግር በሙሉ ልብ እንደግፋለን» ሲሉ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ምስል Million H. Silase/DW

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሁሉም ጋር ሰላም እንፈልጋለን ስንል ከኤርትራ ጭምር ነው ያሉት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርእሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ የኤርትራ መሪዎች ወደ ሰላማዊ መድረክ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል። ባለው ሁኔታ የኤርትራ ጦር በትግራይ መሬት ውስጥ ሆኖ በራሱ የተለያዩ ወንጀሎች እየፈፀመ፣ የሚያስታጥቃቸው «ትንሣሳ» እና «ዴምህት» የተባሉ ቡድኖች ደግሞ እንዲሁ በዝርፍያ ላይ ተሰማርተው እንዳሉ ጠቁመዋል። «እነሱ ያስታጠቋቸው፥ አንድ ጊዜ ትንሣኤ ሌላጊዜ ዴምህት እያሉ በዝርፍያ እና ሌሎች መጥፎ ተግባራት የተሰማሩ ኃይሎች አሉ። በደንብ እናውቀዋለን። ይህ ቶሎ እንዲስተካከል ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ተነጋግረናል። ኃላፊነቱ የእነርሱ ስለሆነ። እነዚህ ያስወጣል የሚል ከበፊቱ የተሻለ እምነት አሁን አለኝ። እምነቱ ከየት መጣ የሚል ማንም ሊጠይቀኝ አይገባም» ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ አክለውም «እንደተባለው ከእነርሱም (ኤርትራ) ጋር ወደ መሰዳደብ የምንገባበት ምክንያት የለም።  ጤና ያለው የመሪነት አካል ካለ፣ ከእርሱ ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆናችን እንገልፃለን» ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ በጦርነቱ ወቅት ስለተፈፀሙ ወንጀሎች ተጠያቂነትን አስመልክተው አስተያየታቸውን የሰጡት ርእሰ መስተዳድሩ ከሀገራዊ የሽግግር ፍትህ በተጨማሪ ዓለምአቀፋዊ እና ገለልተኛ የዳኝነት ስርዓት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

 ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶ ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW