1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ይመለሱ ጥሪ ለፌዴራል መንግሥቱ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ማክሰኞ፣ ጥር 6 2017

ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ የፌደራል መንግስቱ ሕጋዊ እና ሞራላዊ ኃላፊነቱን ይወጣ ሲል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጥሪ አቀረበ ። ከዚህ በተጨማሪ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባሰራጨው መግለጫ የአፍሪቃ ኅብረት፣ የአሜሪካ መንግስት እና የአውሮፓ ኅብረት የፕሪቶርያው ውል እንዲፈፀም ጫና ይፍጠሩ ብሏል።

Äthiopien Mekelle 2025 | Proteste von Vertriebenen des Tigray-Krieges
ምስል Million Hailesilassie/DW

ትግራይ ክልል ወደ ቀዬአችን መልሱን ጥሪ

This browser does not support the audio element.

ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ የፌደራል መንግስቱ ሕጋዊ እና ሞራላዊ ኃላፊነቱን ይወጣ ሲል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጥሪ አቀረበ ። ከዚህ በተጨማሪ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባሰራጨው መግለጫ የአፍሪቃ ኅብረት፣ የአሜሪካ መንግስት እና የአውሮፓ ኅብረት የፕሪቶርያው ውል እንዲፈፀም ጫና ይፍጠሩ ብሏል። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የውሉ ፈራሚ አካላት ስምምነቱን በሙሉእነት ሊተገብሩ ይገባል ብለዋል። የመቐለ ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለሥላሴ ተጨማሪ ዘገባ ልኮልናል ።

የትግራዩን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት  በሙሉእነት ባለመተግበሩ የተነሳ የትግራይ ክልል ሕዝብ የከፋ ሁኔታ ላይ ይገኛል ሲል የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ትላንት ማምሻውን ባሠራጨው መግለጫ ዐሳወቀ ። የሰላም ውሉ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውጭ የሆኑ ታጣቂዎች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ፣ ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ፣ ሕገመንግስታዊ የትግራይ ክልል ግዛት ወደነበረበት እንዲመለስ፣ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የሚያስገድድ እንኳን ቢሆንም እስካሁን ተፈፃሚ ባለመሆኑ የትግራይ ክልል ሕዝብ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብሏል ። በዚሁ ምክንያት በተለይም ተፈናቃዮች ለሰው ልጅ በማይመጠን የከፋ ሁኔታ ሊኖሩ የተገደዱበት ሁኔታ አሁንም በትግራይ መቀጠሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ገልጿል።

በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሰረት የተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውሉ በሙሉእነት ሊተገበር ጥረቱ እንደሚቀጥል ያስታወቀ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በተለይም የተፈናቃዮች ሰቆቃ ሊያበቃ ሕጋዊ እና ሞራላዊ ኃላፊነቱ ይወጣ ብሏል። ከዚህ በተጨማሪም ለአፍሪቃ ኅብረት፣ የአሜሪካ መንግስት እና ለአውሮፓ ኅብረት ጥሪው ያስተላለፈው የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ሊተገበር ጫና እንዲፈጥሩ ጠይቋል።

በመቐለ ጎዳናዎች የተቃውሞ ድምጾች ስለ ተፈናቃዮች ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Million Hailesilassie/DW

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከትላንት ጀምሮ  በመቐለ ጎዳናዎች የተቃውሞ ድምፃቸውን እያሰሙ ያሉት ተፈናቃዮች  ችግራችን የማይፈቱ የውስጥ ይሁን የውጭ አካላት እንቃወማለን ብለዋል። ከሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል የሆኑት አቶ ዳኒኤል ነጋሽ "ከሆነ አካል ጋር ራሳችን ችለን እንደራደራለን። እንደ ህዝብ ማንነታችን የሚያጠፋ ከአሁን በኋላ እንዲቋቋምም። ኃላቀርነት መሰረቱ የሆነው ኅይልም ይሁን የውስጥ እና የውጭ ኅይሎች ይበቃል እንላለን" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፥ የኢትዮጵያፌደራል መንግስት፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ አፍሪካ ሕብረት፣ አውሮፓ ሕብረት እና አሜሪካ በክልሉ ለተፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ ትኩረት እንዲሰጡና የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ሊያደርጉ ይገባል ብሏል።

በሌላ በኩል በቅርቡ በጋራ ለመስራት የተፈራረሙ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ እንዲሁም ባይቶና ዛሬ ባሰራጩት መግለጫቸው የሕዝባችን ስቃይ የዓለም ማኅበረሰብ ትኩረት ይስጠው ያሉ ሲሆን፥ የሰላም ስምምነቱ በአስቸኳይ እንዲፈፀም ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። የባይቶና ከፍተኛ አመራር አቶ ዮሴፍ በርሃ እንደሚሉት የውሉ ፈራሚዎች ይሁኑ በመካከል የነበሩ አሸማጋዮች ስምምነቱ ወደጎን ገፍተውታል ሲሉ ተችተዋል። በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ምላሽ ለማግኘት የተደረገ ጥረት አልተሳካም ።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW