የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አዲስ አወቃቀር ጉዳይ
ረቡዕ፣ መጋቢት 24 2017
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንደ አዲስ እየተዋቀረ እንደሚገኝ ከፌደራል መንግሥት በኩል ይገለፃል። በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ቡድን ባወጣው መግለጫ በጊዜያዊ አስተዳደሩ አወቃቀር ዙርያ «ምክረ ሀሳቦች» አቅርቧል። ሌሎች በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እስከ ምርጫ ድረስ የሚዘልቀው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አካታች ሆኖ እንዲሻሻል ጥሪ አቅርበዋል።
ከፕሪቶርያው ስምምነት በኋላ መጋቢት 2015 ዓመተ ምህረት የተመሰረተው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሁለት ዓመት የሥራ ጊዜው በመጠናቀቁ የአዋጅ ማሻሻያ እና ሌሎች ለውጦች ተደርገውበት እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ እንደሚዘልቅ በፌደራል መንግሥት ሲገለፅ ቆይቷል። በዶክተር ደብረ-ጽዮን የሚመራው የሕወሓት ቡድን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ ለውጦች ለማድረግ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር እየተነጋገረ እንነበር ዐሳውቋል ። በትናንትናው ዕለት መግለጫ ያሰራጨው በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የሕወሓት ቡድን ደግሞ የሥልጣን ዘመኑ የሚራዘመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አወቃቀሩ እንዴት ይሁን በሚል ጉዳይ ምክረ ሐሳቦች ይፋ አድርጓል።
በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የህወሓት ቡድን መጋቢት 19 እና 20 ቀን፣ 2017 ዓመተምህረት አካሄደው ከተባለ ስብሰባ በኋላ የወጣው መግለጫ፥ በሂደት ላይ ያለው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዳግም የማቋቋም እና ማደራጀት ተግባር በሚመለከት ዝርዝር ነጥቦች አንስቷል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ማደራጃን በሚመለከት ያለን ሐሳብ የምናቀርበው መነሻችን የፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት በማድረግ ነው የሚለው ይህ መግለጫ የአንድ ፓርቲ የበላይነት የሌለው፣ ሁሉም የትግራይ ፓርቲዎችን ያካተተ፣ በእኩልነት ያሳተፈ ተደርጎ እንዲቋቋም፥ በዚህ መሰረት ደግሞ የዞን አስተዳደሮች እንዲሻሻሉ ይጠይቃል። ከዚህ በተጨማሪ በከተሞች፣ ወረዳዎች፣ ቀበሌዎች በሕዝብ የተመረጡ አስተዳደሮች በአስቸኳይ ተቋቁመው የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካላት እንዲሆኑ ሐሳብ አቅርቧል።
ይህ ጊዜያዊ አስተዳደር ወደ ሥራ እንዲገባ ደግሞ የትግራይ ኃይሎች አስቀድሞ ወደ ተዘጋጀላቸው ካምፖች እንዲገቡ እንዲሁም ፖሊስ የፀጥታ ሥራ እንዲሠራ፥ በዚህ የማሻሻያ መግባባት ከተደረሰ በኋላ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እስከ ቀበሌ ደረጃ በአንድ ወር ግዜ ውስጥ ተዋቅሮ ሥራ እንዲጀምር ሐሳብ ያቀርባል። በዚህ ጉዳይ ማብራሪያ የሰጡን የትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሃፍቱ ኪሮስ «ጊዜያዊ አስተዳደሩ የአንድ ፓርቲ የበላይነት የሚታይበት ሳይሆን ሁሉም አካታች መሆን ይገባዋል» ይላሉ።
በዚህ የጊዜያዊ አስተዳደር ዳግም ማዋቀር ጉዳይ በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እንዲሁ የተለያዩ ሐሳቦች የሚቀርቡ ሲሆን ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፥ ሥራ ላይ የቆየው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አካታች አልነበረም ሲሉ ይተቻል። በዚህም የቅቡልነት ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች እንደሚገጠሙት የሚገልፁት የዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዶሪ አስገዶም፥ ይህ የሚቀይር ማሻሻያ እንዲኖር ፌደራል መንግሥቱ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ያድርጉ ይላል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ