1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አዲስ ካቢኔ

ረቡዕ፣ መጋቢት 27 2015

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር 27 አባላት ያሉት አዲስ ካቢኔ አቋቋመ። የተቋቋመው የጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ 51 በመቶ ህወሓት የተቆጣጠረው ሲሆን የተቀረው 49 በመቶ ደግሞ የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች፣ የትግራይ ምሁራን እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተከፋፍለውታል ተብሏል።

Äthiopien Kabinett Tigray
ምስል Million Hailesilassie/DW

«አስተዳደሩ ሁሉን ያካተተ ነው»

This browser does not support the audio element.

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር 27 አባላት ያሉት አዲስ ካቢኔ አቋቋመ። የተቋቋመው የጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ 51 በመቶ ህወሓት የተቆጣጠረው ሲሆን የተቀረው 49 በመቶ ደግሞ የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች፣ የትግራይ ምሁራን እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተከፋፍለውታል ተብሏል። ዛሬ በተካሄደ ስነ ስርዓት ደግሞ አዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ከነባሩ ህወሓት መር የክልሉ አስተዳደር ሥልጣኑን ተረክቧል። ተቃዋሚዎች በትግራይ የተቋቋመው አዲስ አስተዳደር ከነበረው የማይለይ ብለው ይተቹታል። 

ላለፉት አምስት ዓመታት ትግራይን የመሩት የህወሓቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በይፋዊ የርክክብ ስነ-ስርዓት ከሥልጣናቸው ወርደው ኃላፊነታቸውን ለጊዜያዊ አስተዳደሩ መሪ አቶ ጌታቸው ረዳ አስረክበዋል። ዛሬ በትግራይ ርእሰ መስተዳድር ቢሮ በነበረ የርክክብ ስነ ስርዓት የቀድሞ አስተዳደር ካቢኔ አባላት እና የአዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር ተሿሚዎች ተገኝተዋል። በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላለፉት አምስት ዓመታት ክልሉን የመሩት ዶክተር ደብረፅዮን «ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለማጠናከር አብረን እንሠራለን» ብለዋል። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሲቋቋም አቶ ጌታቸው ረዳ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ሲሆኑ ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሣኤ እና ጀነራል ታደሰ ወረደ የርእሰ መስተዳድሩ ምክትሎች ሆነዋል። 

የሥልጣን ርክክብ በትግራይ ክልል ምስል Million Hailesilassie/DW

ከዚህ ውጭ የተቃዋሚው ፖርቲ ባይቶና አባላት አቶ ሞገሥ ገብረ እግዚአብሔር እና አቶ ታደለ መንግሥቱ የትግራይ ክልል የውኃና ኢነርጂ ቢሮ እንዲሁም የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች ተደርገው ተሹመዋል። በፕሪቶሪያው ውል መሰረት በትግራይ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት የሚሆን የጊዜ ቆይታ ይኖረዋል ተብሏል። በተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዙርያ የጠየቅናቸው የክልሉ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው የዓረና ትግራይ ማእከላይ ኮሚቴ አባል አቶ ሃፍታይ ገብረ ሩፋኤል ጊዜዚያዊ አስተዳደሩ አካታች ያልሆነ፣ ህወሓትን በተለየ ስም የሥልጣን ጊዜውን የሚያራዝምበትን ዕድል የፈጠረ መዋቅር ሲሉ ተችተውታል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW