የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጥሪ እና በአፋር ነጻ መሬት የሚገኘው ኃይል ምላሽ
ሐሙስ፣ መስከረም 22 2018
ከትግራይ ሐይሎች በመነጠል በዓፋር ክልል እየተደራጁ ያሉ ታጣቂዎች ትግራይ ላይ ለመፈፀም ያቀዱት ጥቃት በክልሉ ነዋሪዎች ጥረት መክሸፉ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አስታወቀ። በዓፋር ያሉ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች አባላት ወደ ትግራይ እንዲመለሱም ግዚያዊ አስተዳደሩ ጥሪ አቅርቧል። ራሳቸው የትግራይ የሰላም ሐይል ብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች መሪ ጀነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ በበኩላቸው ፖለቲካዊ ችግሮች በድርድር ለመፍታት ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠዋል።
በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙርያ ትላንት መስከረም 21 ቀን 2018 ዓመተምህረት መግለጫ ያወጣው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እንዳለው፥ 'ሓራ መሬት' በሚል ስም በአፋር እየተንቀሳቀሱ ናቸው ያላቸው ከትግራይ ሐይሎች የተነጠሉ ታጣቂዎች በበራሕለ በኩሉ ወደ ኮኖባ በመሻገር በትግራይ ላይ ጥቃት ለመፈፀም መንቀሳቀሳቸው ያመለክታል። ይሁንና የአከባቢ ነዋሪ የታጣቂዎቹ እንቅስቃሴ መቃወሙ ተከትሎ ግጭት መቀስቀሱ ያነሳው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፥ በዚህም ከትግራይ ሐይሎች የተነጠሉት ታጣቂዎች የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸው ገልጿል።
የትላንት ረቡዕ ክስተት ምን ነበር?
ታጣቂዎቹ ፈፀሙት ያለው ተግባር በማውገዝ የአፋር ክልል ህዝበ በተለይም የበራሕሌ እና ኮኖባ ነዋሪዎችን ያመሰገነው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር መግለጫ፥ የትላንቱ ጥቃት እንዲፈፀም ትእዛዝ የሰጡ እና የፈፀሙ እንዲሁም ከዚህ በዘለለ ተጋሩ እርስበርስ እንዲዋጉ እያስተባበሩ ናቸው ያላቸው አካላት ከተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል ብሏል።
በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ትላንት በተሰጠው መግለጫ ዙርያ ዶቼቬሌ የጠየቃቸው የእነዝያ በአፋር ክልል ያሉ ከትግራይ ሐይሎች የተለዩ ታጣቂዎች መሪ ብርጋዴር ጀነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ፥ ትግራይ በጦር አበጋዞች እየተመራች ነው፣ በትላንትናው ዕለት የወጣው መግለጫም የመንግስት ሳይሆን የጦር አበጋዞቹ ነው ብለዋል።
ጀነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ "ትግራይን እየመሩ ያሉት የጦር መሪዎች ናቸው። ኮነሬሎች፣ ጀነራሎች እንዳሻቸው እያደረጉ ነው። በጦር አበጋዞች የምትመራ ትግራይ እንጂ መንግስት ያላት ትግራይ የለችም። በትላንትናው ዕለት የወጣው መግለጫም የመንግስት ሳይሆን የጦር አበጋዞች መግለጫ ነው" ያሉ ሲሆን በጀነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እውቅና እንደማይሰጡት ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ስለትላንቱ ክስተት ጀነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ (ወዲ አንጥሩ) ሲናገሩ "የአፋር ህዝብ ያመነበት ነው ያደረገው። በጦርነቱ ወቅት ተቀያይመናል። በበርካታ አካባቢዎች እርቅ የማውረድ ስራ ተከውኖል። ትላንት ሁነቱ በተከሰተበት ግን እርቅ አልተደረገም ነበር። በአፋር ባህል ደግሞ ጉዳዩ በእርቅ ሳይፈታ ወደአካባቢያችን አትግቡ ነው የተባለው። እነሱን ለማነጋገር የሄዱት የጦራችን መሪዎች፥ ያኮረፈ ቤተሰብ ነው የጠበቃቸው። ከመሰረቱ ግን ይህ ግጭት የፈጠረው ህወሓት ነው" ሲሉ ገልፀዋል።
የተለየ ፖለቲካዊ አቋም በመያዝ እና ከትግራይ ሐይሎች በመለየት በአፋር ክልል እየተደራጁ ያሉት ታጣቂዎች ራሳቸው "የትግራይ ሰላም ሐይል" ብለው የሚጠሩ ሲሆን በተለይም በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ የቀድሞ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር መቀየር ተከትሎ የትጥቅ ትግል መጀመራቸው ያስታወቁ ናቸው። በጀነራል ታደሰ ወረዳ የሚመራው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ትላንት ባወጣው መግለጫ ፖለቲካዊ ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑ የገለፀ ሲሆን እነዚህ በአፋር ያሉ ታጣቂዎችም እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።
ቅድመ ሁኔታ
የታጣቂዎቹ መሪ ብርጋዴር ጀነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ በበኩላቸው ያለው ፖለቲካዊ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ፍላጎታቸው መሆኑ ለዶቼቬለ ገልፀው፥ ቅድመ ሁኔታ ያሉዋቸው ነጥቦችም አስቀምጠዋል።
ጀነራሉ "እኛ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ፍላጎታችን ትልቅ ነው። ያወጣነው ቅድመ ሁኔታ አለ። ትጥቃቹ አውርዳችሁ ኑ የሚባለው በፍፁም አይሆንም። በመጀመርያ ደረጃ ከኮር በላይ የሰራዊት አመራሮች የወሰዱት አቋም የታጠፍ፣ እሱን ተከትሎ ያለ ጭቆና ይቁም፣ በትግራይ በህዝብ ተቀባይነት ያለው መንግስት ይኑር፣ ገለልተኛ ሰራዊት ይኑረን፣ በፓርቲ የሚታዘዝ የፀጥታ ሐይል መኖር የለበትም" ሲሉ ተናግረዋል።
ገለልተኛ አደራዳሪ
ጀነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ እንደሚሉት፥ የትግራይ ሐይሎች ከፍተኛ አመራሮች ባለፈው ዓመት ጥሪ ወር አጋማሽ ያስተላለፊት ለአንድ ፓርቲ ያዳላ ውሳኔ ከመሻር በተጨማሪ እሱን ተከትሎ ለተፈጠረ ጥፋት ይቅርታ ይጠይቁ፣ በተለያዩ የትግራይ አካባቢ የታችኛው የአስተዳደር መዋቅር አካላት በሐይል ለመቀየር በተንቀሳቀሱበት ወቅት የሐይል እርምጃ የወሰዱት ለሕግ ይቅርቡ ብለዋል። ድርድር የሚኖር ከሆነም በገለልተኛ አካል በኩል መሆን አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው ጀነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ ወዲ አንጥሩ ለዶቼቬለ ገልፀዋል።
ከወራት በፊት በዚህ ጉዳይ ዙርያ ተናግረው የነበሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ አፋር ክልል ካሉ ታጣቂዎች ወደ ትግራይ ማንኛውም ትንኮሳ የሚመጣ ከሆነ ተጠያቂው የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ነው ብለው ነበር። አፋር ካሉ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች ታጣቂዎች ጋር ያለው ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ የተናገሩት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ይሁንና የውክልና ግጭት ለመፍጠር ከተሞከረ ግን ጉዳዮ ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ጋር ነው የሚሆነው ሲሉ ማስታወቃቸው አይዘነጋም። ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ትላንት ባሰራጨው መግለጫ ትላንት በአፋር ክልል የተከሰተው ሁነት መነሻ አድርጎ የከፋ የፀጥታ ችግር እንዳይፈጠር የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጥረት ያድርጉ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ