1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፈርሶ እንደ አዲስ ይቋቋም ጥሪ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 30 2017

በትግራይ ክልል ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር ፈርሶ ዳግም እንደ አዲስ እንዲቋቋም ተቃዋሚው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ጥሪ አቀረበ ። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት አልተወጣም፥ ይልቁኑስ የትግራይ ክልል ጥቅሞችን አሳልፎ እየሰጠ ነው ሲል ተቃዋሚው ፓርቲ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ተችቷል።

Äthiopien I Alula Hailu und Yemane Kassa, führende Oppositionspolitiker in Tigray
ምስል Million Haileselassie

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፈርሶ እንዲዋቀር ጥሪ

This browser does not support the audio element.

በትግራይ ክልል ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር ፈርሶ ዳግም እንደ አዲስ እንዲቋቋም ተቃዋሚው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ጥሪ አቀረበ ። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት አልተወጣም፥ ይልቁኑስ የትግራይ ክልል ጥቅሞችን አሳልፎ እየሰጠ ነው ሲል ተቃዋሚው ፓርቲ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ተችቷል። በሌላ በኩል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በቅርቡ አማካሪ ያለውን ምክር ቤት እንደሚያቋቁም ገልጿል። የመቐለ ወኪላችን ዝርዝሩን ልኮልናል ።

«ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚጠበቅበት አልተወጣም» ተቃዋሚዎች

ከሁለት ዓመቱ ጦርነት በኋላ፥ በዋነኝነት በትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር እንዲኖር በ2015 ዓመተ ምህረት መጋቢት ወር የተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ አይደለም ተብሎ በክልሉ በሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተተቸ ይገኛል ። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይጠበቅ እንደነበረው የጦርነቱ ተፈናቃዮች አልመለሰም፣ የትግራይ ክልል ግዛት አላስከበረም፣ ሰላም እና ፀጥታ አላረጋገጠም የሚሉ ተቃዋሚዎች እና ሌሎች ተቺዎች ይህን ሁኔታ ለመቀየር ደግሞ የተለያዩ ሐሳቦች ያቀርባሉ።

በትግራይ ክልል በተቃዋሚነት ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሆነው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፥ የሚጠበቅበት ኃላፊነት መወጣት አልቻለም ያለው አሁን ላይ ያለው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፈርሶ እንደገና ሊቋቋም ይገባል ሲል ገልጿል። የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አሉላ ኃይሉ «ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደገና እንዲቋቋም፥ ይህ ለማቋቋም ደግሞ ብሔራዊ ጉባኤ እንዲጠራ እና የተለያዩ አካላት ያካተተ ግዚያዊ አስተዳደር እንዲመሰረት ነው ጥሪ የምናቀርበው። እሱን ተከትሎ ደግሞ ጠንካራ ምክር ቤት ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲኖረው ነው ጥሪ እያቀረብን ያለነው» ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በተቋቋመበት ወቅት የተነሳ ፎቶ ። ምስል ፦ከክምችት ክፍልምስል Million Hailesilassie/DW

የሕወሓት በሁለት ቡድኖች ተከፍሎ መፋጠጥ አስተዳደሩን አዳክሟል ተብሏል

ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበላይነት የተቆጣጠረው ሕወሓት በሁለት ቡድኖች ተከፍሎ የሚያደርገው ፍጥጫ አስተዳደሩን ከማዳከም በዘለለ፥  የትግራይ ክልል ጥቅሞችንም አሳልፎ የሰጠ ሆኗል ሲል ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አብራርቷል። የፓርቲው የሕግ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የማነ ካሳ «ሥልጣን ላይ ባሉ ሁለት ቡድኖች መካከል ያለው ፖለቲካዊ መሳሳብ፥ የትግራይ ወሳኝ አጀንዳዎች ለማስፈፀም በፌደራል መንግስቱ ላይ ጫና መፍጠር አልቻለም፣ ፍላጎት የለውም። ይህ ለምን ቢባል በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ፍጥጫ አንዱ ላላው ለማሸነፍ የፌደራል መንግስቱ ድጋፍ ስለሚሹ፥ የትግራይ ጥቅሞች መጠየቅ ደግሞ የፌደራል መንግስቱን ማስጨነቅ ስለሆነ፥ ለራሳቸው የቡድን ጥቅም ሲሉ የትግራይ ብሔራዊ ጥቅም ለፖለቲካዊ ፍጆታ እየተጠቀሙበት ነው» ሲሉ ተናግረዋል። 

አብረው ለመሥራት ከዚህ ቀደም ቃል ከገቡት ሦስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ፣ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ እንዲሁም ባይቶና ይገኙበታልምስል Million Haileselasie/DW

ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ በቅርቡ በጋራ ለመሥራት ቃል ኪዳን የገቡት ሦስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም  የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ እና ባይቶና በበኩላቸው በትግራይ ክልል ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር ሁሉን አካታች ምክርቤት እንዲኖረው ጠይቀዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከወራት በፊት አማካሪ ያለውን ምክርቤት እንደሚያቋቁም አሳውቆ ነበር። ይሁንና ይህ ለረዥም ግዜ አልተፈፀመም። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ባለፈው ሳምንት አድርጎት ከነበረ ስብሰባ በኋላ ባወጣው መግለጫ ደግሞ፦ አማካሪ ካውንስል በአስቸኳይ እንዲቋቋም አቅጣጫ ተቀምጧል ብሏል። ይሁንና በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከግዚያዊ አስተዳደር ማብራሪያ ለማግኘት የተደረገ ጥረት አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስሺ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW