የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ህወሓትን ለማጥፋት ይደረጋል ያሉትን ሙከራ አወገዙ
ሰኞ፣ መስከረም 26 2018
በአፍሪካ ቀንድ አንዣቦ ያለው አደገኛ ጦርነት በሩቅ ለማስቀረት በጋራ እንስራ ተብሎ በህወሓት በተጠራ ኮንፈረንስ ጥሪ ቀረበ። የህወሓት አባላት ጨምሮ ሌሎች በርካቶች የተሳተፉበት የትግራይ ህዝብ ኮንፈረንስ የተባለ መድረክ በሳምንቱ መጨረሻ በመቐለ ተካሂዷል። በዚሁ መድረክ በነፃ ፕሬስ ስም ፀረ ትግራይ ተግባራት እየፈፀሙ ናቸው በተባሉ ሚድያዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ተብሏል።
ህወሓት ለሳምንታት ያደርጋቸው የነበሩ 'የብሔራዊ አንድነት ዘመቻ' የተባሉ መድረኮች መዝግያ የተባለ የሁለት ቀናት ኮንፈረንስ በሳምንቱ መጨረሻ ቅዳሜ እና እሁድ በመቐለ ተደርጓል። ሶስት ሺህ ገደማ የሚሆኑ ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የተወከሉ የህወሓትአባላት የሆኑ ተሳታፊዎች፣ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የስራ ሐላፊዎች፣ የትግራይ ሐይሎች ወታደራዊ መሪዎች እና ሌሎች የተሳተፉ ሲሆን፥ 'የትግራይ ህዝብ ብሔራዊ ኮንፈረንስ' የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል።
የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት
በዚሁ መክፈቻ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደየተገኙ ሲሆን ባደረጉት ንግግርም ህወሓት ላይ ያነጣጠሩ ያሏቸው ጥቃቶች አውግዘዋል። ጀነራል ታደሰ ወረደ "ህወሓት ሊድን ወይም ሊጠፋ የሚችለው፥ በውስጡ እና በአባላቱ ሆኖ፥ ህወሓት ገጥሞት ካለ ማነቆ ወጥቶ ትልቅና ነባር እንዲሁም የሁላችን ተሳትፎ ያለው ፓርቲ እንዲሆን፥ በተጨማሪም ድህንነቱ እና ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ የሚቻለን መጣር ነውር ሳይሆን ሐላፊነታችን መሆኑ ግልፅ መሆን ይገባዋል። በአንፃሩ ምቹ ሁኔታ ተፈጠረ ብለህ ህወሓት ለማጥፋት መሞከር ነው ዲቂላ ፖለቲካ" ብለዋል።
በዚሁ ኮንፈረንስ መጨረሻ በትላንትናው ዕለት ተሳታፊዎች የተግባቡባቸው የተባለ መግለጫ የተሰራጨ ሲሆን፥ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ለኢትዮጵያ መንግስት ጥሪ ቀርቧል። በርካታ ጉዳዮች የዳሰሰ የትላንቱ መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም ስምምነቱ እያከበራ እንዳልሆነ በማንሳት ይወቅሳል።
ጥሪ ለኤርትራ
አደገኛ የጦርነት ዳመና አንዣቦ እንዳለ በዚሁ መግለጫ የተቀመጠ ሲሆን፥ አለማቀፉ ማሕበረሰብ በተለይም የአሜሪካ መንግስት፣ አፍሪካ ሕብረት እና ሌሎች አካላት ለወቅታዊ ፖለቲካዊ ችግር ትኩረት እንዲሰጡም ያትታል።
የዚህ የትግራይ ህዝብ ኮንፈረንስ የተባለ መድረክ ተሳታፊዎች በትግራይ እና ኤርትራ መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጨመሩ በማንሳት አድናቆት ከመስጠቱ በተጨማሪ ለኤርትራ በተላለፈ መልእክት በአፍሪካ ቀንድ አንዣቦ ያለው ጦርነት ለማስቀረት በጋራ የመስራት ጥሪ አቅርቧል።
በኮንፈረንሱ በንባብ በቀረበ መግለጫ "በትግራይ እና ኤርትራ ህዝብ አንዣቦ ያለው እና የአፍሪካ ቀንድ ከመጥፎ ወደ ከፋ ችግር ልያስገባ የሚችል የጦርነት አደጋ በሩቁ ለማስቀረት፥ የሚቻለን እንደምናደርግ ስናረጋግጥ በእናንተ በኩልም ጮኽ ባላችሁ ድምፃችሁ በማሰማት ሚናችሁ እንድትወጡ እንዲሁም ለሰላም አብረን እንድንሰራ ጥርያችን እናቀርባለን" ተብሏል።
እርምጃ በሚድያዎች ላይ
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ የተለያዩ ጉዳዮች በዚህ ቅዳሜ እና እሁድ የተደረገ ስብሰባ ተነስተዋል። በትግራይ ያሉ ሚድያዎች በፕረስ ነፃነት ስም ህዝብን ለአደጋ እያጋለጡ ነው ተብሎ የተገለፀ ሲሆን በእነዚህ ሚድያዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ እንደሚደግፉም የዚህ ህዝባዊ የተባለ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች አስታውቀዋል።
"በጥፋት እና ነውረኛ ተግባር ተሰማርተው በሚድያ ነፃነት ስም አውዳሚ ተግባር ለመቀጠል በወሰኑ የሚድያ አካላት ላይ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የሚወስደው እርምጃ በመደገፍ፥ ሚናችን እንደምንወጣ የዚህ ብሔራዊ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ቃል እንገባለን" ተብሏል።
ይህ መድረክ በህወሓት የተጠራ ቢሆንም ስያሜው የትግራይ ህዝብ ኮንፈረንስ ተብሏል። በህወሓት እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ከፓርቲው ሕጋዊ እውቅና መመለስ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ጉዳዮች እርስ በርስ መወዛገባቸው እና መካሰሳቸው ቀጥለዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
እሸቴ በቀለ
ፀሀይ ጫኔ