በቅርቡ ይካሄዳል የተባለው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 1 2018
በትግራይ ይካሄዳል ያሉት የወጣቶች አስገድዶ የመመልመልና ያንዣበበው የጦርነት ዳመናን በመቃወም በአዲስ አበባና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ የሰልፉ አዘጋጆች ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። ሰልፉን የሚያስተባብሩት የትግራይ የሰላምና ለውጥ ምክርቤት የተባለው እና የተለያዩ የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረትና የስቪክ ማሕበራት ናቸው።
«በትግራይ አፈናው እንደቀጠለ ነው»
በትግራይ ክልል አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላና የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ተባብሰው እንደቀጠሉ የትግራይ የሰላምና የለውጥ ምክርቤት የሕዝብና የመገናኛ ብዙሃን ግኑኝነት ሃላፊ አቶ ከበደ አሰፋ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። ለጦርነት ምክንያት ነበረ ያሉትና በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የፈረሰውን ምክርቤት ወደሥራ የመለሰው ሕወሓት በምክርቤቱ በኩል አፋኝ ያሉት ሕግ ማውጣቱንና በዚህም ምክንያት በተለይም ወጣቱ ወደ አዲስ አበባና ወደ ስደት እየጎረፈ እንደሆነ ያክላሉ።
«ህወሓት ቀድሞውኑም ሕገወጥ በነበረ ምክርቤትና ኃላም በፕቶሪያ ስምምነት እንዲፈርስ የተደረገውን ምክርቤት ወደ ሥራ መልሶ አፋኝና ሕገወጥ ብቻ ሳይሆን ከወንጀል ሕግ ባሕሪ አንጻርም በዓለም ታይቶ የማይታወቅ ወደ ኃላ ሄዶ የሚቀጣ ሕግ በማውጣት ከዚህ በፊት የተቃወሙትን ለመቅጣት ያለመ ሕግ ነው ያጸደቀው።»
የሰላማዊ ሰልፉ ዓላማና ውጤት
ይህን አፋኝና ሕገወጥ ያሉት ሥርዓትን በመቃወም መጀመሪያ በአዲስ አበባ ቀጥሎም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎችየተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚካሄዱ ነው አቶ ከበደ የሚገልጹት።
«በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ቁጥር ያለው የትግራይ ተወላጅ አለ። ስለሆነም የትግራይ ማሕበረሰብ አባላትና ሌሎች ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት ሰላማዊ ሰልፍ በቅርቡ ይካሄዳል። በመቀጠልም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ሰላማዊ ሰልፎቹ ይደረጋሉ።»
የትግራይ የሰላምና ለውጥ ምክር ቤት አባል የሆነው የዓረና ትግራይ ሊቀ መንበር አቶ ዓንዶም ገብረስላሴ በበኩላቸው ከሰልፉ የሚገኘው ውጤት የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ በትግራይ ክልል ያንዣበበውን ጦርነት በማስቀረትና አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ በማድረግ ላይ ያሉ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ ጫና ማድረግ ነው በማለት አክሏል።
የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነው ወጣት ደስታ ፍጹም በበኩሉ በቅርቡ ይካሄዳል በተባለው ሰላማዊ ሰልፍ ድምጹን ለማሰማት ዝግጁ መሆኑን ገልጾልናል።
«በአዲስ አበባ በቅድቡ የትግራይ ወጣቶች አፈሳ ይቁም የሚል ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል። ለመውጣትም ዝግጁ ነኝ።»
ሰላማዊ ሰልፉ የሚደረግበት ቀንና ቦታ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ካለቁ በኃላ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ አዘጋጆቹ አክለዋል።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ታምራት ዲንሳ