1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የትግራይ የሽግግር መንግስት ምስረታ መጓተት

ዓርብ፣ መጋቢት 1 2015

ሳልሳይ ወያነ ትግራይ በምህጻሩ ሳወት አስቀድሞ በትግራይ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ሲወተውት እንደነበር ያስታውሳል። ያኔ ግን ባንዳ የሚል ስም እንደተሰጣቸው የገለጹልን የድርጅቱ የውጭ ጉዳይ ክፍል ኃላፊ አቶ ኃይሉ ከበደ ከሰላም ስምምነቱ እስከ ሽግግር መንግሥቱ ምስረታ አቃፊና አሳታፊ አይደለም ይላሉ።

Äthiopien Tigray-Provinz Mekele
ምስል፦ EDUARDO SOTERAS/AFP

የትግራይ የሽግግር መንግስት ምስረታ መጓተት

This browser does not support the audio element.

በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት በትግራይ ክልል ይቋቋማል የተባለው የሽግግር መንግሥት ምስረታ በመጓተቱ በሕዝቡ ኑሮ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ መሆኑን የትግራይ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ። የሽግግር መንግሥቱ አካታች ባለመሆኑ ከሂደቱ እራሳቸውን ማግለላቸውን  እንደሚቀጥሉበትም ተናግረዋል። 

በትግራይ ክልል የሽግግር መንግሥትን የሚያቋቁም ነው የተባለ ጉባኤ መካሄዱ እና  የሽግግሩን መንግሥት የሚመሩ የካቢኔ አባላት ድልድልም መደረጉ ተነግሯል። ኮሚቴውን ከማዋቀር ጀምሮ እስከ መንግሥት ምስረታው ህወሐት በሩን ቀርቅሮ ያለተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሳትፎ አካሂዶታል ያሉት የተቃዋሚ ፓርቲዎች በበኩላቸው ከሂደቱ እራሳቸውን አግልለናል እያሉ ነው። ሂደቱ በመጓተቱም በሕዝቡ የዕለተ ተዕለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና እያሳደረ እንደሆነም የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይናገራሉ። አቶ ዮሴፍ ሃይለስላሴ አርአያ የታላቋ  ትግራይ በምህጻሩ ባይቶና የሕግ አገልግሎት ኃላፊ ናቸው። " የነበረውን የህወሐት የአፈና ጉዞ እንዲቀጥል ነው እየተደረገ ያለው።  በፕሪቶርያ ውል መሰረትም እየተደረገ አይደለም። 30 ዓመት ሙሉ በህዝቡ ላይ የተጫነው ሥርዓት ሕዝቡ እስኪጠፋ ድረስ anንመራለን እያሉ ነው። የትግራይ ሕዝብ ወደ ባሰ ሁኔታ እየገባ ነው። "

የዓሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሐጎስ ወልዱ በበኩላቸው መንግሥት ተቋቁሞ መደበኛ የፖሊስ ሥራ ባለመጀመሩ  በመቐለ ከተማ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር እንዳለ በመጥቀስ እየደረሰ ነው ያሉትን ችግር አብራርተዋል።" በተደጋጋሚ እንደገለጽነው መቐለ የምድር ሲኦል የሆነችበት ሁኔታ ነው ያለው። ሥርዓት የለም! የመንግስት ሰራተኛ ለ2 ዓመት ደመወዝ አልተከፈለውም። ብዙ ችግሮች አሉ በመሆኑም የሽግግር መንግስቱከነችግሩም ቢሆን በአስቸኳይ መመስረት አለበት።"

ምስል፦ DW/M. Hailessilasie

የሽግግር መንግሥቱ ምስረታ መጓተቱ በተለይ በመንግሥት ሠራተኛው ላይ ከፍተኛ የኑሮ ጫና እንዳደረሰ የሚናገሩት የዓረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ለዲሞክራሲ የሕዝብ ግኑኝነት ኃላፊ አቶ ዓናዶም ገብረ ሥላሴም እንዲሁ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብና የአፍሪቃ ሕብረት በትግራይ ሁሉን ያቀፈ የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ሳልሳይ ወያነ ትግራይ በምህጻሩ ሳወት አስቀድሞ በትግራይ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ሲወተውት እንደነበር ያስታውሳል። ያኔ ግን ባንዳ የሚል ስም እንደተሰጣቸው የገለጹልን የድርጅቱ የውጭ ጉዳይ ክፍል ኃላፊ አቶ ኃይሉ ከበደ ከሰላም ስምምነቱ እስከ ሽግግር መንግሥቱ ምስረታ አቃፊና አሳታፊ አይደለም ይላሉ።

የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ አክለውም በትግራይ ክልል የሽግግር መንግሥቱ ሁሉንም ባካተተ መልኩ እንዲመሰረት በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

ሽዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW