የትግራይ የጤና አገልግሎት መሻሻል
ሐሙስ፣ መጋቢት 7 2015ከስላም ስምምነቱ በኃላ በትግራይ በጤና አገልግሎት ረገድ መሻሻሎች እንዳሉ የጤና ባለሙያዎች እና ተገልጋዮች ይገልፃሉ። ለረዥም ግዜ ተቋርጦ የነበረ የሕፃናት ክትባት እንዲሁም ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶች በሂደት እየተጀመሩ መሆኑን ተገልጿል። ከወራት በፊት ዶቼቬሌ የጎበኘው በመቐለ የሚገኝ ለህጻናት የጤና ክትትል የሚያደርግ አንድ ጤና ጣቢያ ያኔ የሕፃናት ክትባት አቋርጦ፣ አገልግሎት በማይሰጥበት ደረጃ ላይ ነበር ።አሁን ግን ከተለያዩ ዓለምአቀፍ ለጋሾች ባገኘው ግብዐት ዳግም አገልግሎት መስጠት መቻሉን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ ከመቀሌ ዘግቧል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በጦርነቱ ምክንያት 80 ከመቶ የሚሆኑ የትግራይ ጤና ተቋማት በተለያየ ደረጃ የሚገለፅ ውድመት ደርሶባቸዋል። ከውድመቱ በተጨማሪ በትግራይ ላይ ተጥሎ በነበረ ክልከላ ምክንያት የመድሃኒት እና የሕክምና ቁሶቁሶች እጥረት ተፈጥሮ በርካቶች ለሞትና ለተለያዩ ችግሮች ሲጋለጡ የቆዩ ሲሆን ከሰላም ስምምነቱ በኃላ ባለው ግዜ ግን መሻሻሎች እየተስተዋሉ ስለመሆኑ የጤና ባለሙያዎች እና ተገልጋዮች ይገልፃሉ።
ከወራት በፊት ዶቼቬሌ ተመልክቶት የነበረ በመቐለ የሚገኝ እና በተለይም በሕፃናት ክትትል ዙርያ የሚሰራው ካሰች አስፋው ጤና ጣብያ፥ በወቅቱ የሕፃናት ክትባት አቋርጦ፣ አገልግሎት በማይሰጥበት ደረጃ የነበረ ሲሆን፥ አሁን ላይ ግብአቶች ከተለያዩ ዓለምአቀፍ ለጋሾች አግኝቶ የተሻለ አገልግሎት ወደ መስጠት ተመልሷል።
ሲስተር አልማዝ ወልደስላሴ የካሰች ጤና ጣብያ ዳይሬክተር ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፣ ከረዥም ግዜ በኃላ ጤና ጣብያቸው የመድኃኒት እና ክትባት አቅርቦት በማግኘቱ ወደ አገልግሎት ተመልሷል። እንደ ሲስተር አልማዝ ገለፃ "ከወራት በፊት እንዳያችሁት ምንም ዓይነት መድሃኒት፣ ክትባት ይሁን የሕክምና ግብአት አልነበረንም። አሁን ግን ከሞላ ጎደል እያገኘን ነው። የሕፃናት ክትባት እየሰጠን ነው። አሁንም ግን ውስንነቶች አሉ" ባይ ናቸው።
እንደ የትግራይ ጤና ቢሮ ገለፃ ሙሉበሙሉ ከወደሙ የጤና ተቋማት ውጭ የተቀሩትን ወደ መደበኛ የጤና አገልግሎት ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በመድሃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት በኩል መሻሻሎች ቢኖሩም ከፍላጎት አንፃር ግን አሁንም ብዙ እንደሚቀር የክልሉ ጤና ቢሮ ይገልፃል። የትግራይ ጤና ቢሮ ሐላፊ ዶክተር አማኑኤል ሀይለ አሁንም ቢሆን የሕክምና ግብአቶች አቅርቦት ውሱንነት አለ ይላሉ። "በቀድሞ ግዜ በመቐለ ማከማቻ ለወራት የሚሆን ይዘን ነበር ለጤና ተቋማት መድሃኒት እና ሌሎች ግብአቶች የምናከፋፍለው። አሁን ይህ የለም። ለጤና ተቋማት ያዳረስነው ግብአት በቀናት አልቆ ተመልሶ የለም ሲባል ነው የሚስተዋለው" ይላሉ ዶክተር አማኑኤል ሀይለ።
የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ከአራት ወራት በላይ ቢያልፉም እስካሁን የትግራይ ጤና ዘርፍ መደበኛ በጀት አለማግኘቱ፣ የጤና ባለሙያዎች ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ሰራተኞች እስካሁን ደሞዝ የሚያገኙበት ዕድል ባለመፈጠሩ በክልሉ ችግሮች ተባብሰው እንዲቀጥሉ ማድረጉ ይገለፃል። የጤና ባለሙያዋ ሲስተር አልማዝ ወልደስላሴ "ከጦርነት ብናርፍም፣ የጠበቅነው መሻሻል ግን የለም" ይላሉ። "የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ አራት ወራት ቢያልፍም እስካሁን ደሞዝ አላገኘንም" የሚሉት ሲስተር አልማዝ የሚመለከታቸው አካላት መፍትሔ እንዲሰጡ ይጠይቃሉ።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ