የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፌድራል መንግሥት “አስፈላጊ ድጋፍ ማድረግ አለበት” አለ
ረቡዕ፣ መጋቢት 3 2017
በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ «አሳሳቢ ደረጃ» ላይ መድረሱን የገለፀው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፥ የፌደራል መንግስቱ «አስፈላጊ ድጋፍ ማድረግ አለበት» አለ ። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የትግራይ ኃይሎች እያደረጉት ባለው «ኃላፊነት የጎደለው እንቅስቃሴ ሰላማዊ ሰዎች መጎዳታቸውን እንዲሁም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለሥልጣናት መታፈናቸውን» አመልክቷል ።
በትግራይ ክልል «ባለስልጣናት መታፈናቸው»
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር «የሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች የአንድ የሕወሓት ክንፍ ፍላጎት ለማሟላት እያደረጉት ባለ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ሰዎች በጥይት ተኩስ መጎዳታቸውን» ዐሳወቀ። አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ «ባለስልጣናት መታፈናቸውን» አመልክቷል ። አስተዳደሩ ይህን ያለው ዛሬ ባሰራጨው ወቅታዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ መግለጫ ነው ። መግለጫው ይፋ የሆነው በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና በክልሉ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች መካከል ያለው ልዩነት በተካረረበት ወቅት ነው።
በትናንትናው ዕለት በትግራይ ክልል ደቡብ ምስራቅ ዞን ዓዲጉደም ከተማ እና ሳምረ ወረዳ በነበረው ሁኔታ የትግራይ ኃይሎች ተኩስ ከፍተው በአራት ሰዎች ላይ ከባድ፤ በሌሎች በርካቶች ደግሞ ቀላል ጉዳት መድረሱን የዞኑ አስተዳደር ዐሳውቋል ። አስተዳደሩ ትናንት ማታ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ባሰራጨው መረጃ በአጠቃላይ ዘጠኝ አመራሮች መታፈናቸው ገልጿል። አቶ ጌታቸው የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግስት «እነዚህ በፀጥታ ኃይሎች ስም እየተንቀሳቀሱ ያሉት አካላት የአንድ ኋላቀር እና ወንጀለኛ ቡድን ተላላኪ እንጂ የትግራይ ሕዝብ እና ጊዜያዊ አስተዳደር የማይወክሉ መሆኑን ተገንዝቦ አስፈላጊ ድጋፍ ማድረግ አለበት» የሚል መልዕክት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስተላልፏል ። በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር «የፕሪቶርያ ውል ሲፈርስ፤ የትግራይ ሕዝብ ወደ ዳግም ጥፋት ሲገባ ዝም ተብሎ መታየት የለበትም» ሲልም አክሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ ትናንት አመሻሽ ዐሥራ አንድ ሰዓት ገደማ ከመቐለ በስተደቡብ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዓዲጉደም ከተማ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተሾሙ አካላትን ለመያዝ ታጣቂዎች አደረጉት የተባለው እንቅስቃሴ ከነዋሪዎች ተቃውሞ እንደገጠመው የዐይን እማኞች ተናግረዋል ። ተቃውሞውን ለመበተን የትግራይ ኃይሎች አባላት የሆኑ ታጣቂዎች ከፈቱት በተባለው ተኩስ ሰዎች መጎዳታቸውን፣ በበርካቶች ላይ ድብደባ መፈፀሙን ከዓይን እማኞች ሰምተናል ። ስማቸው እንዳይገልፅ የጠየቁ የዓዲጉደም ነዋሪ፥ «በዓዲጉደም ከተማ የሰራዊት እንቅስቃሴ ስንመለከት ምን እንደተጠፈረ ለማወቅ ወደ አካባቢው ስንሄድ፥ በታጣቂዎች የተኩስ እሩምታ ተከፈተብን» ብለዋል ።
በዚሁ የታጣቂዎች ርምጃ ጉዳት ደርሶባቸው በዓዲጉደም በሚገኝ ሆስፒታል ሕክምና ላይ መሆኑ የነገረን ወጣት ሞገስ ኪዳኑ በበኩሉ፥ እሱን ጨምሮ በርካቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል። ሞገስ ኪዳኑ «እነሱ ብረት ይዘው እኛ ባዶ እጃችን፥ ተጨማሪ ደግሞ እኛጋ አብረው ብዙ ጊዜ በቆዩ ናቸው የተመታነው ። ያልጠበቅነው ነገር ነው እኛ ላይ የደረሰው ። በዱላ የተመታ መዓት ነው ። እኛ በመሣሪያ የተመታን ብቻ ነን ወደዚህ ሆስፒታል መጥተን ያለነው ። እኔ ባላገኛቸውም ሪፈር የተባሉም አሉ ። ይህ ነው የገጠመን» በማለት አስረድቷል። ከዚህ በተጨማሪ፦ በትናንቱ የዓዲጉደም ከተማ ሁነት ምክንያት በጥይት ጉዳት ደርሶባቸው የመጡ ሁለት ሰዎች በመቐለ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሕክምና እንደተደረገላቸው፥ ከሆስፒታሉ የድንገተኛ ሕክምና ክፍል ሠራተኞች ዛሬ ጠዋት አረጋግጠናል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ የፌደራሉ መንግስት በትግራይ ክልል ያለውን አሳሳሲ ሁኔታ በመገንዘብ አስፈላጊ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት በገለፀው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መግለጫ፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የፕሪቶርያን ውል እየጣሱ ናቸው በተባሉ አካላት ላይ ጫና እንዲፈጥር ጥሪ አቅርቧል ። «ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን የትግራይ ሕዝብ ሊወጣበት ወደማይችል ሌላ ዙር ጥፋት ሊገባ እንደሚችል» የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በመግለጫ አስጠንቅቋል ። በዚሁ በትግራይ ኃይሎች ተፈፀመ የተባለው ጥቃት ዙርያ ከሰራዊቱ አዛዦች ማብራሪያ ለማግኘት የተደረገ ጥረት አልተሳካም ።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ