የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር በኢትዮጵያ
ማክሰኞ፣ ጥር 2 2015በቅርቡ ኃላፊነት የተሰጣቸው የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚነስትር ለሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ተወያዩ። ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሺን ጋንግ ጋር ዛሬ መነጋገራቸውን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ «የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት አሁንም ጸንቶ ቀጥሏል» በማለት ጽፈዋል። ያደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ከቻይና «በልማት የምትጋራውን ስልታዊ የጋራ ዓላማ፣ እንዲሁም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን አጉልቶ ያሳየ» ስለመሆኑም ገልፀዋል።
በቻይና ድጋፍ የተገነባው የአፍሪቃ የበሽታ መከላከል ማዕከል ዋና ጽሕፈት ቤት ከሰሞኑ እንደሚመረቅና አዲስ አበባ የገቡት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኑስትር በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
የዓለም ሁለተኛው ግዙፉ ኢኮኖሚ ባለቤት የቻይና እና የአፍሪቃ አኅጉር ግንኙነት ሁለቱንም በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እያደረገ ያለ ስለመሆኑ ይነገርለታል።
ከ1990 ዎቹ መጨረሻ በተለይም ከ2000 ጀምሮ የቻይና አፍሪቃ የትብብር መድረክ መመስረትን ተከትሎ ቻይና እና አፍሪቃ በንግድ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በብድር እና በሰው ኃይል ዘርፎች የላቀ ደረጃ እየደረሰ የመጣ ግንኙነት ስለመመስረታቸው የምርምር ሥራ ላይ የሚያተኩሩት ዶክተር ጌድዮን ጃለታ ተናግረዋል።
ኃላፊነት በቅርቡ የተሰጣቸው የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚነስትር ለሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል። «ለምሳሌ ከ2015 ጀምሮ ቻይና 60 ቢሊዮን ዶላር ነው የሰጠችው ለአፍሪካ ሀገሮች» ብለዋል ባለሞያው። ይህም ገንዘብ ንግድን ለማቀላጠፍ፣ የኢንዱስትሪ መንደሮችን ለመገንባት፣ የግብርና ማዘመን ሥራዎችን ለማሳደግና ለሌሎችም የዋለ ስለመሆኑ ተገልጿል።
ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መነጋገራቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ከቻይና «በልማት የምትጋራውን ስልታዊ የጋራ ዓላማ፣ እንዲሁም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን አጉልቶ ያሳየ» ስለመሆኑም ገልፀዋል።
የአሜሪካ ቻይና እና ሩሲያ የአፍሪቃ ቀንድ የዲፕሎማሲ ጥረት አንድምታ
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጦኖስ በርኸ «ብዙ የአፍሪቃ ሀገሮች በዘመናቸው ያላዩት የመሰረተ ልማት እድገት ዕያሳዩ ነው» በማለት የቻይና አፍሪካ ግንኙነትን ደረጃ የት ላይነት ገልፀውታል።
ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ግን የሁለቱ አካላት ግንኙነት የላቀው የተጠቃሚነት ሚዛን ወደ ቻይና ያጋደለ ነው በሚል ይተቻል። ሀገራት በቻይና ምርት ከመጥለቅለቃቸው ባለፈ ለማይወጡት እዳ እየተዳረጉ ነው በሚል ጠንካራ መከራከሪያ ይነሳል። ዶክተር ጌድዮን ጃለታም ይሁን ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ይህ እውነት የለውም ማለት እንደማይቻል ግን ጥቅሙ እንደሚያመዝን ገልፀዋል።
ቻይና የአፍሪቃ ኅብረት ግዙፍ ግቢን ጨምሮ በርካታ ግንባታዎችን ለአፍሪካ አድርጋለች። አዲስ አበባ ላይ የተገነባው የአፍሪካ የበሽታ መከላከል ማዕከል ዋና ጽሕፈት ቤት ከሰሞኑ እንደሚመረቅና አዲስ አበባ የገቡት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኑስትር በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ