1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይና እና የታይዋን ዉጥረት

ሰኞ፣ ጥቅምት 1 2014

ታይዋን ----- የዩናይትድ ስቴትስ 51ኛ ግዛት የሆነች ያክል ከዋሽግተን የሚቆረጥ-የሚንቆረቆርላት ሁለንተናዊ ድጋፍ መቀጠሉ ቀዳሚዉ ነዉ።ታይዋን ከዋሽግተንና ከምዕራብ አዉሮጳ ከምታገኘዉ ድጋፍ በተጨማሪ ከጃፓን እስከ አዉስትሬሊያ፣ ከደቡብ ኮሪያ እስከ ሕንድ የሚገኙት የዩናይትድ ስቴትስ ታማኞች የቻይና ጠላቶች፣ በዉጤቱም የታይዋን ረዳቶች ናቸዉ።

China - Treffen zum Gedenken an den 110. Jahrestag der Xinhai-Revolution
ምስል Carlos Garcia Rawlins/REUTERS

የቻይና ፀረ-ንጉሳዊ አገዛዝ አመፅ 110ኛ ዓመትና የሲኖ-ታይዋን ጠብ

This browser does not support the audio element.

 

ሰኔ 1905 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ቶኪዮ-ጃፓን ላይ ተጠንስሶ፣ በስድስተኛ ዓመቱ ዉቻንግ-ሑቤይ ላይ የተቀጣጠለዉ አመፅ ለዘመናዊቱ ቻይና ትልቅ መሠረት መጣሉ አላነጋገረም።በቃለ-ነቢብ ወይም በይፋ አንድ፣ በገቢር ግን ሁለት ያዉም ተቃራኒ ሥርዓት የሚያራምዱት ትልቂቱ ኮሚንስታዊቱ፣ ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና እና ራስዋን የቻይና ሪፐብሊክ ብላ የምትጠራዉ ትንሽ ደሴት ታይዋን አመፁ የተቀጣጠለበትን 110ኛ ዓመት እኩል አከበሩት።ቅዳሜ።ትንኝም ለሆዷ፣ «ዝሆንም ለሆዱ፣ ዉኃ እንጠጣ ብለዉ ወደ ወንዝ ወረዱ።»-እንዳለዉ ባለቅኔዉ ይሆን ይሆን? ሆነም አልሆነ የታላቁ ሕዝባዊ አመፅ ታላቅ ክብረ-በዓል የቤጂንግና የታይፔ ጠብ ታላቅ ንረት ማንፀባረቂያ መሆኑ ነዉ ዚቁ።በዓሉ መነሻ፣ የአመፁ እንዴትነት ማጣቀሻ፣ የሁለቱ ዛቻ፣ አፀፋ-ዛቻ መድረሻችን ነዉ። 

                                                 

የቻይናና የታይዋንን ግዛቶች ከሚገምሰዉ የባሕር ወሽመጥ ግራ-ቀኝ የተመሠረቱት የበዓል አዛጋጅ ኮሚቴ መሪዎች በዓሉን በየፊናቸዉ ለማክበር ቤጂንግና ታይፔ ላይ ጠብ ርግፍ በሚሉበት ሰሞን የቻይና ምርጥ ተዋጊ ጄቶች ባሕሩን እያቋራጡ ታይዋን ሰማይ አጠገብ ያጉረመርሙ ነበር።የታይዋን ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት በዓሉ ከመከበሩ በፊት በነበረዉ አንድ ሳምንት ዉስጥ ብቻ የኑክሌር ቦምብ መሸከም የሚችሉ አዉሮፕላኖችን ጨምሮ የቻይና ተዋጊ ጄቶች 148 ጊዜ ታይዋን ዓየር አጠገብ ሲያናፍሩ ነበረ።

አብዛኞቹ አዉሮፕላኖች የታዋን የዓየር መከላከያ ቀጠና የሚቆጣጠረዉን አካባቢ ደፍረዋል።እንንደ ባለስልጣናቱ መግለጫ። የታይዋን የጦር ጄቶች የቻይና ጠላቶቻቸዉን በረራ ለማቋረጥ በተደጋጋሚ መብረራቸዉም ተዘግቧል።ይሁንና የቻይና ሕዝባዊ ነፃ አዉጪ ጦርን እርምጃ ታይዋንና ዩናይትድ ስቴትስ በተደጋጋሚ ከማዉገዛቸዉ በቀር የታይዋንም ሆነ፣ ባካባቢዉ የሠፈረዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የቻይናን ጦር በኃይል ለመጋፈጥ አልቃጡም።የታይዋን ፕሬዝደንት ፃይ ኢንግ-ዌን ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳሉት ግን ዓየር ኃይላቸዉ የደሴቲቱን የዓየር ክልል አያስደፍርም።

«የዓየር ኃይል ተዋጊ ጄቶቻችን የዓየር ክልልላችንን ሙሉ በሙሉ ሲያስከብሩ እናያለን።የዓየር ክልልላችን አደጋ በተቃጣበት ቁጥር ፓይለቶቻችን ፈጥነዉ እየበረሩ የዓየር ክልልላችን ደሕንነት ያስከብራሉ።»

 

ፕሬዝደንት ፃይ የሚመክቡት ዓየር ኃይል በአብዛኛዉ ከዩናይትድ ስቴትስ የሸመተና የቃረማቸዉን ጄቶች የታጠቀ 80 ሺሕ አባላት አሉት።ከአዉሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች-እስከ ኑክሌር ቦምብ ጣይ ጄቶች፣ ከድምፅ አልባ ተዋጊ እስከ ድሮን ወደ አራት ሺሕ በራሪዎችን የታጠቀዉ የቻይና ዓየር ኃይል በሰዉ ኃይል ብዛት ከዓለም ተወዳዳሪ የለዉም።የታይዋንንማ በአምስት እጥፍ ሊበልጥ ጥቂት ነዉ የሚቀረዉ።ከታይዋን አጠቃላይ ጦር ብዛትም ይበልጣል። ከ395 ሺሕ በላይ።

 

ባጠቃላይ የጦር ኃይል ብዛትም በዚች ምድር ቻይናን የሚስተካከል ሐገር የለም። 2.2 ሚሊዮን መደበኛ ጦር፣1.2 ሚሊዮን ተጠባባቂ ጦር አላት።ታይዋን ያላት አጠቃላይ ጦር ብዛት 290 ሺሕ ነዉ።በአጠቃላይ ሕዝብ ብዛት፤ በምጣኔ ሐብት አቅም፣በቴክኖሎጂ ዕድገትም ቻይናና ቻይና «አፈንጋጭ» የምትላት ግዛትዋ ጨርሶ አይመጣጠኑም።

ምስል picture alliance/Photoshot/L. Xiao

ይሁንና ታይዋን ከዋናዋ የቻይና ግዛት ካፈነገጠችበት ከ1949ኝ ጀምሮ እስካሁን የተፈራረቁት የቻይና መሪዎች ሆኑ ያሁኖቹ  ትንሺቱ ደሴት ጨርሶ እንዳትወበራ-በዲፕሎማሲ ቆንጠጥ፣ ገለል፣ በጦር ኃይል ጠጋ፣ ጫን፣ ከበብ ከማድረግ አልፈዉ በኃይል ሊያስገብሩ አልሞከሩም።ፕሬዝደንት ሺ ጂፒንግም ዓይር ኃይላቸዉን ታይዋን ድንበር ጥግ ቢያዘምቱም ባለፈዉ ቅዳሜ ባደረጉት ንግግር ነባሩ መርሕ አይታጠፍም ነዉ ያሉት።

                                         

«ብሔራዉ ዳግም ዉሕደት የታይዋን ወገኖቻችንን ጨምሮ ለመላዉ የቻይና ሕዝብ በጣም ጠቃሚ ነዉ።ሰላማዊ ዉሕደትን የሚያራምደዉን መሠረታዊ መርሐችንን እናከብራለን።ከ1992 ጀምሮ መግባባት የተደረሰበትን የአንድ ሐገር፣ ሁለት ሥርዓትን ደንብ እንጠብቃለን።በባሕር ማዶ-ለማዶዉ ሰላማዊ ግንኙነትን ለማዳበር እንጥራለን።»


የሕዝባዊት ቻይና ገዢዎች ኃይል፣ብዛትና ሐብት እንደ ጥቅም ማስከበሪያ ወይም ማስፈራሪያ ዋነኛ መሳሪያ በቀጥታ እንዳይጠቀሙ እንደ ምክንያት የሚጠቀሱት ብዙ ናቸዉ።ታይዋን ከዋናዋ ቻይና ከተገነጠለች ከ1949 ጀምሮ በእስያ  የዩናይትድ ስቴትስ 51ኛ ግዛት የሆነች ያክል ከዋሽግተን የሚቆረጥ-የሚንቆረቆርላት ሁለንተናዊ ድጋፍ መቀጠሉ ቀዳሚዉ ነዉ።ታይዋን ከዋሽግተንና ከምዕራብ አዉሮጳ ከምታገኘዉ ድጋፍ በተጨማሪ ከጃፓን እስከ አዉስትሬሊያ፣ ከደቡብ ኮሪያ እስከ ሕንድ የሚገኙት የዩናይትድ ስቴትስ ታማኞች የቻይና ጠላቶች፣ በዉጤቱም የታይዋን ረዳቶች ናቸዉ።

 

«ኢምፔሪያሊዝም የወረቀት ላይ ነብር ነዉ----» የሚለዉ የሊቀመንበር ማኦ ዜዱንግ ድንቅ መርሕም ሲገለበጥ የቻይናን ጉልበትን ሊጠቁም እንደሚችል የማኦ ተከታዮች አጢነዉት ሊሆን ይችላል።ሌላዉ ምክንያት ግን የቻይና ፖለቲካዊ ሥርዓት መረጋጋት፣ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገትና ወታደራዊ ጡንቻ መደርጀት ቤጂንጎች አንድም ጥይት ሳያጮኹ ማካዎን ከፖርቱጋል፣ ሆንግ ኮንግን ከብሪታንያ እንዲረከቡ ሥለረዳ፣ ታይዋንም የጊዜ ጉዳይ እንጂ ወደ «እናት ሐገሯ» መመለሷ አይቀርም ብለዉ እንዲያምኑ መሰረት ሆኗል።

 

ያም ሆኖ የታይፔ መሪዎች ከዩናይትድ ስቴትስና ከተከታዮችዋ በሚያገኙት ሁለንተናዊ ድጋፍ ተደፋፍረዉ የለየለት ነፃነት እንዳያዉጁ ቤጂንጎች ከማስጠንቀቅ ተዘናግተዉ አያዉቁም።ሺም ደገሙት-ቅዳሜ።

                                        

«የቻይና ሕዝብ ታላቅ እመርታ አሳይቷል።በሁለት ዕግሩ ከመቆም ሐብታም፣ እና ጠንካራ እስከ መሆን ደርሷል።የቻይና ሕዝብ የዳግም ታላቅነት ጉዞ ከማይቀለበስበት ደረጃ ደርሷል።ታይን ዳግም ከቻይና እንዳትዋሐድ ትልቅ እንቅፋትና ለዳግም ታላቅነት ድል ደንቃራ የሆነዉ ግን ታይዋን ዉስጥ የሚታየዉ የነፃነትና የተገንጣይነት ስሜት ነዉ።»

 

የሺ ጂፒንግ መልዕክት ግን በታይዋን መሪዎች ዘንድ ያዉ እንደተጠበቀዉ እንደ ማስፈራሪያ ነዉ የታየዉ።የፕሬዝደንት ፃይ ኢንግ-ዌን  አፀፋም ለሚደረግብን ግፊት አናጎበድድም የሚል ነዉ።

«በድጋሚ ማረጋገጥ የምፈልገዉ በጥድፊያ የምናደርገዉ ነገር የለም።የታይዋን ሕዝብ ለሚደረግበት ጫና ያጎበድዳል የሚል የተሳሰተ ግንዛቤ እንዳይኖር ማሳሰብ እፈልጋለሁ።ቻይና በዘረጋችልን ጎዳና እንድንጓ የሚያስገድደን እንደሌለ ለማረጋገጥ ብሔራዊ መከላከያ ኃይላችንን ማጠናከርና እራሳችንን መከላከል በፅናት መቆም አለብን።»

ምስል Reuters/J. Lee

ከራስ ወገን እራስን መከላከል።በ1905 ጃፓን-ቶኪዮ የነበሩት ዶክተር ያት-ሴን፣ ሶንግ ጂአሮን እና ብጤዎቻቸዉ የያኔዉን የቂንግ ንጉሳዊ አገዛዝ የሚቃወም ማሕበር በሕዕቡ ሲመሰርቱ «ሕዝቡን ከራሱ ገዢዎቹ ግፍ ለመከላከል» ብለዉ ነበር።በቻይንኛዉ ቱንግ ሜንግ ሁይ ይባል የነበረዉ ማሕበር አንዳዴ የቻይኖች ሕብረት፣ ሌላ ጊዜ የቻይና ሊግ፣ ደግሞ ሌላ ጊዜ የቻይና አብዮታዉያን ሕብረት እየተባለ ይተረጎም ነበር።

 

ከስሙ ጀምሮ ቅጥ የሌለዉ ይመስል የነበረዉ  ማሕበር እሩቅ መጓዙን የሩቆቹ ቀርተዉ ማሕበሩ እንዲደራጅ የደገፉት ጃፓኖች ራሳቸዉም ይጠራጠሩ ነበር።ይሁንና የማሕበሩ መስራቾች ከስድት ዓመት በኋላ ጥቅምት 10፣ 1911 ዉቻይንግ-ሁባይ ግዛት ያቀጣጠሉት የነፍጥ አመፅ  የ6 ዓመቱ ሕፃን ንጉሰ-ነገስት ፑይ የሚመሩትን ንጉሳዊ አገዛዝ መንቅሮ ለመጣል አንድ ዓመት ነበር የፈጀበት።ሺ ጂፒንግ የትክክለኛ ዴሞክራሲዊ አብዮት ጅምር አሉት በቀደም።

                                           

«ጥቅምት 19፣1911 ዉቻንግ ላይ የተተኮሰችዉ ጥይት ድምፅ በዘመናዊቱ ቻይና የትክክለኛ ዴሞክራሲ ሥርዓት ብስራት ነበረች።1911፣ ሕዝባችን ለዳግም ትንሳኤ በሚያደርገዉ ጉዞ  እንደ ታላቅ መለያ ማማ ይታያል።»

 

ንጉሱን ስልጣን  እንዲለቁ ያስገደደዉ ማሕበር እንዲመሰረት ድጋፍ ያደረገችዉ ጃፓን፣ ንጉሱ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ የንጉሱ ዋና ደጋፊ ሆና አረፈችዉ።ጃፓን የ1911 አብዮተኞች የመሰረቷትን ሪፐብሊካዊት ቻይናን በ1932 ወርራ ማንቹሪያ የተባለዉን ግዛት ስትቆጣጠር ደግሞ ከርታታዉን ንጉሰ-ነገስት እንደ አሻንጉሊት ከዙፋን አስቀምጣቸዉ ነበር።

ምስል Taiwan Presidential Office

የቻይና ኮሚንስቶች በ1949 ቤጂንግን ሲቆጣጠሩ ወደ ታይዋን የሸሸት የሐገሪቱ ገዢዎች በ1905 ጀፓን የተደራጁት፣በ1911 ንጉሳዊዉ አገዛዝ ላይ ሕዝብ ያሳመፁት፣ በ1932 ጃፓን የሾመቻቸዉን ንጉሳዊ አገዛዝ የሚቃወሙ ፖለቲከኞችን አስተሳሰብና መርሕ እንጋራለን የሚሉ ፖለቲከኞች ነበሩ።ቺያንግ ካይ-ሼክ የሚመሯቸዉ ኃይላት ከኮሚንስቶቹ ጋር ዉጊያ ከገጠሙበት ጊዜ ጀምሮ የዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ አልተለያቸዉም ነበርም።ታይዋን ሸምቀዉ በ1950ዎቹ ዳግም ቻይናን ለመዉረር ሲዘጋጁ ደግሞ በሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት ከትቢያ ተቀይጣ የነበረችዉ ጃፓን እንደገና አንሰራርታ ታይዋን ለሸመቁት የቤጂንግ ጠላቶችን ትረዳ ያዘች።ዛሬም ለተከታዮቻቸዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW