የኅልዉና አደጋ የተጋረጠበት የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር
ዓርብ፣ ጳጉሜን 5 2013
ከአንድ ምዕት ዓመት በፊት ለሀገሪቱም ለከተማይቱም ታሪክ ፈርጥ ሆኖ የሚነሳው የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት የታሪክ አሻራነቱ ሊጠፋ የቀሩት ነባራዊ እሴቶች አብሮት የተመሰረተው ቀዳሚው ሰፈር ከዚራ እና በዚያው የሚገኘው የድርጅቱ መ/ቤት ብቻ ናቸው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መስተዳድሩ ከድርጅቱ ጋር አብረው የተመሰረቱ የከዚራ ቤቶችን በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ማፍረስ አሊያም ለግለሰቦች እንዲተላለፉ የማድረግ ስራን እየሰራ ነው ፡፡ ምክንያቱ ግን ግልፅ አይደለም ብዙዎች እንደሚሉት፡፡
በዚሁ አግባብ ለግለሰብ ይዞታ ማስፋፊያነት እንዲሰጥ የተወሰነው መሬት አለመግባባት መፍጠሩን ተከትሎ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ሰራተኞች ማህበር ቅሬታ አቅርቧል፡፡ የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ዋሲሁን በላይ እንቅስቃሴው ዛሬ ላይ ጥቂት ቁጥር ያለውን የድርጅቱ ሰረታኛ ህልውና እና የቆየውን ታሪክ ለማጥፋት የታለመ ነው ሲሉ ለዶይቸ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
የሁለት ሀገራት ንብረት በሆነው ድርጅት ሀብት ላይ መስተዳድሩ የመወሰን ስልጣን የለውም የሚሉት የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አባይነህ በላይ እየተሰራ ያለው ህገወጥ ስራ ነው የድርጅቱን እና የቦታውን ታሪክ የማጥፋት ነው ብለዋል፡፡ ድርጊቱ አግባብ አለመሆኑን ለመግለፅ በሄዱበት ወቅት በፀጥታ ኃይል ቦታውን እንዲለቁ መታዘዛቸውን ጠቁመዋል፡፡
የድሬደዋ ከተማ ስራ አስኪያጅ ፅ/ቤት ምክትል ስራ አስኪጅ እና የደምብ ማስከበር አገልግሎት ኃላፊ አቶ ነጂብ ኢድሪስ በተሰራው ስራ የተፈፀመ ምንም ዓይነት አስተዳደራዊ እና የህግ ጥሰት የለም ብለዋል- የተቋሙ ኃላፊነት ውሰኔ ማስፈፀም መሆኑን በመጥቀስ፡፡ መስተዳድሩ ከከተማዋ ቀዳሚ አመሰራረት ጋር ስሙ በሚነሳው የከዚራ አካባቢ የሚከተለው አሰራር ግልፅ አለመሆን የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ በቅርቡም የዚሁ ድርጅት ንብረት የሆነውን በተለምዶ የምድር ባቡር ክለብ ሜዳን ለአንድ ግለሰብ ለመስጠት ያሳለፈው ውሳኔ ተቃውሞ ገጥሞት አፈፃፀሙ በሂደት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡
መሳይ ተክሉ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ