1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኅዳር 02 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 2 2017

የማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ነጥብ መጣል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የዋንጫ ግስጋሴ ለሊቨርፑል መልካም እድል ፈጥሯል ። ዳግም ድል የቀናው ሊቨርፑል የደረጃ ሰንጠረዡ በ5 ነጥብ ልዩነት እየመራ ነው፥ በሻምፒዮንስ ሊጉም የምድቡ መሪ ነው ።

Deutschland I Bundesliga - Borussia Dortmund vs RB Leipzig
ምስል Leon Kuegeler/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ነጥብ መጣል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የዋንጫ ግስጋሴ ለሊቨርፑል መልካም እድል ፈጥሯል ።   ዳግም ድል የቀናው ሊቨርፑል የደረጃ ሰንጠረዡ በ5 ነጥብ ልዩነት እየመራ ነው፥ በሻምፒዮንስ ሊጉም የምድቡ መሪ ነው ።  በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባዬር ሙይንሽን ሲያሸንፍ፥ ተከታዩ ኤርቤ ላይፕትሲሽ ነጥብ ጥሏል ። ቪንሺየንት ጁኒዮር ሔትትሪክ በሠራበት ግጥሚያ ሪያል ማድሪድ ዖሳሱናን 4 ለ 0 ድል አድርጓል ።  

አትሌቲክስ

በጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ2024 ከስታዲየም ውጭ በተደረጉ ውድድሮች የዓመቱ ምርጥ አትሌትን መምረጪያ ድምፅ አአሳጣጥ ተጠናቀቀ ።  የዓለም አትሌቲክስ ለፍጻሜው ለታጩት 12 አትሌቶች ደጋፊዎች ክፍት አድርጎት የነበረው የድምፅ አሰጣጥ ትናንት ተጠናቋል ።  ከ12ቱ የመጨረሺያ እጩዎች መካከል ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ ይገኝበታል ። አሸናፊው ከ20 ቀናት በኋላ እሁድ፤ ኅዳር 22 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ፈረንሣይ ሞናኮ በሚደረገው የሽልማት ሥነሥርዓት ይፋ ይሆናል ።

የ33 ዓመቱ የረዥም ርቀት አትሌት ታምራት ቶላ በ33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ 2:06:26 በመግባት ብቸኛዋን የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሩ ያስገኘ አትሌት ነው ። በዚህ በማኅበራዊ መገናኛ አውታር በሚሰጥ ድምፅ አሰጣጥ በሚለየው ፉክክር  ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሴትም በወንድም ተካተው ነበር ። በሴቶች ዘርፍ ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ሱቱሜ አሠፋ እና ትእግስት ከተማ ከአምስቱ እጩዎች ውስጥ ነበሩ ። በወንዶች ዘርፍ ደግሞ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ዮሚፍ ቀጀልቻ እና ታምራት ቶላ ነበሩ በእጩነት የተካተቱት ። በስተመጨረሻም በወንድም በሴትም ለፍጻሜ ከቀረቡ 12 አትሌቶች መካከል የቀረው ታምራት ነው ። ለአትሌት ታምራት ቶላ መልካም እድል እንመኛለን ።

ከአትሌቲክስ ዜና ሳንወጣ፦ የፀረ-ጉልበት ሰጪ ቅመሞች የሕግ ጥሰት በፈፀሙ አትሌቶች ላይ የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፉ ተሰምቷል ።  ቅጣት ከተጣለባቸው አትሌቶች መካከል ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ይገኙበታል ። ለመሆኑ ቅጣቱ የተላለፈባቸው አትሌቶች እነማን ናቸው ምንስ አደረጉ ተብሎ ነው የተቀጡት?  በኢትዮ ኤፍኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰ ጉዳዩን ተከታትሏል ።

ሦስቱ ቅጣቱ የተላለፈባቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች፦ ፀሐይ ገመቹ፤ ኅብስት ጥላሁን አስረስ እና ሳሙኤል አባተ ዘለቀ ናቸው ። ሳሙኤል ላይ እገዳ ያስተላለፈው የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን መሆኑ ታውቋል ። በሁለቱ ሴት አትሌቶች ላይ ቅጣት ያስተላለፈው ከአበረታች ቅመሞች ጋር በተያያዘ ምርመራዎችን የማድረግና እርምጃዎችን የመውሰድ ስልጣን ያለው "Athletics Integrity Unit (AIU)ነው ።

ከታሪክ ማኅደር፦ በቶኪዮ ማራን ወርቅ ያስገኘው ኢትዮጵያዊው አትሌት አበበ ቢቂላ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1964ምስል Keystone/Hulton Archive/Getty Images

ፀሐይ ገመቹ የተላለፈባት ቅጣት ከበድ ያለ ነው ። ፀሐይ በቶኪዮ ኦሎምፒክ በ10,000 ሜትር እንዲሁም በ2023ቱ የሀንጋሪ ቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና በማራቶን ኢትዮጵያን የወከለች አትሌት ናት ።   ለቅጣት የተጋለጠችው ከአበረታች ቅመሞች ጋር በተያያዘ ምርመራዎችን የማድረግና ርምጃዎችን የመውሰድ ስልጣን ያለው "Athletics Integrity Unit (AIU) ባደረገላት የባይሎጂካል ፓስፖርት ምርመራ ጉዳዩዋን ሲከታተል ቆይቶ ጥፋተኛ ናት በማለቱ ነው ።

ፀሐይ ላይ የተላለፈው ከበድ ያለ ቅጣት፦ 30/2024 አንስቶ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት በየትኛውም የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ እንዳትሳተፍ እገዳ የተጣለበት ነው ።  ከዚያም ባሻገር፦ ከማርች 22/2020 እስከ ኖቬምበር 30/2023 ድረስ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች በሙሉ እንዲሰረዙ ተወስኖባታል ። ከእነዚህም መካከል በ2026 የቶኪዮ ማራቶን ሁለተኛ የወጣችበት ውጤቷ ተጠቃሽ መሆኑን ምሥጋናው ታደሰ ገልጧል ። የጥቅምት 25 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሌላኛዋ እገዳ የተጣለባት አትሌት ኅብስት ጥላሁን አስረስ ናት ። የ24 ዓመቷ አትሌት ዲሴምበር 3/2023 በቻይና ናኒንግ ባደረገችው ውድድር በተደረገላት የሽንት ምርመራ (triamcinolone acetonide) የተባለውን የተከለከለ አበረታች ንጥረ ነገር መውሰዷ ተረጋግጧል ። ካለባት የአስም ህመም ለማገገም በተወጋችው መርፌ ውስጥ ንጥረ ነገሩ ሳይኖር እንዳልቀረ ብትናገርም ቅሉ (AIU) እሷ «መርፌውን ተወግቻለሁ» ባለችውና በምርመራ የተረጋገጠው መድኃኒቱን ወሰዳበታለች የሚለው የምርመራ ጊዜ ሊገጣጠሙ ባለመቻላቸው ከቅጣት ልታመልጥ አልቻለችም ሲል ምሥጋናው አክሏል ።

በዚህም መሠረት፦ ከጁን 3/2024 አንስቶ የሚታሰብ የሁለት ዓመታት የእገዳ ቅጣት ተጥሎባታል ። በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ የሽንት ምርመራ ካደረገችበት ዲሴምበር 3/2023 አንስቶ በተወዳደረችባቸው መድረኮች በሙሉ ያገኘቻቸውን ሜዳሊያዎች፣ ሽልማቶች፣ የአሸናፊነትና የመግቢያ ክፍያዎች እንድትነጠቅ ተወሰኖባታል።

የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በበኩሉ፦ በአትሌት ሳሙኤል አባተ ዘለቀ ላይ የእገዳ ርምጃ መውሰዱን ዐሳውቋል ። እንደ ባለስልጣኑ መግለጫ ከሆነ አትሌቱ February 29/2023 ከውድድር ውጪ በተወሰደለት የሽንት ናሙና EPO (Erythropoietin) የተባለው የተከለከለ ንጥረ ነገር በሰውነቱ ተገኝቷል ። በመሆኑም የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን በመጀመሪያ ደረጃ ዳኝነት ሰሚ ጉዳዩ ሲታይ ቆይቶ October 11/2024 በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ከApril 17/2024 ጀምሮ ለ2 ዓመት በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር እንዳይሳተፍ እገዳ ተጥሎበታል ሲል ምሥጋናው ታደሰ ገልጧል ።

በኢትዮ ኤፍኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰምስል DW

እግር ኳስ

የባሎን ደ ኦር ዋንጫን ያልወሰደው ከዘረኝነት ጋር በተያያዘ ነው በሚል ከፍተኛ መነጋገሪያ የነበረው ቪንሺየንት ጁኒዮር ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትትሪክ ሠራ ። ቪንሺየንት ጁኒዮር ሔትትሪክ በሠራበት የቅዳሜው ግጥሚያ ሪያል ማድሪድ ዖሳሱናን 4 ለ 0 ድል አድርጓል ። አንደኛው ግብ የጁድ ቤሊንግሀም ነው ። ሪያል ማድሪድ  የትናት በስትያ ድሉ ተደምሮለት በ27 ነጥቡ በላሊጋው የሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ትናንት በማዮካ የ1 ለ0 ሽንፈት የገጠመው አትሌቲኮ ማድሪድ በ26 ነጥብ ይሰልሳል።

ላሊጋውን በ33 ነጥብ የሚመራው ባርሴሎና ትናንት በሪያል ሶሲዬዳድ ሼራልዶ ቤከር ብቸኛ ግብ የ1 ለ0 ሽንፈት ደርሶበታል ። ባርሴሎና በላሊጋው የትናንት ግጥሚያ በሪያል ሶሲዬዳድ ሲሸነፍ ላሚኔ ያማል አልተሰለፈም ።

የባርሴሎና አጥቂዎች ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ እና ላሚኔ ያማል ፖላንድ እና ስፔን በሚያደርጓቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በጉዳት የተነሳ አይሳተፉም ። ላሚኔ በሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ወቅት ቀኝ ቁርጭምጭሚቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት የተነሳም ለሦስት ሳምንታት መጫወት አይችልም ። ስፔን ከዴንማርክ እና ከስዊትዘርላንድ ጋር በሚኖራት ጨዋታዎችም አይሰለፍም ።

ላሊጋ

የላሊጋው ኮከብ ግብ አግቢ የያማል ቡድን ተሰላፊ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በበኩሉ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ግድም መሰለፍ እንደማይችል ተዘግቧል ። ሌቫንዶቭስኪ ትናንት ጀርባው ላይ በደረሰበት ጉዳት የተነሳ ሀገሩ ፖላንድ በኔሽን ሊግ ከፖርቹጋል እና ስኮትላንድ ጋር በምታደርጋቸው ግጥሚያዎች አይሰለፍም ።

የባርሴሎናው ጀርመናዊ ግብ ጠባቂ ማርክ አንድሬ ቴር ሽቴገንምስል DeFodi/IMAGO

የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዛቦን አሰልጣኝ ሩበን አሞሪምን የሚተካ አሰልጣኝ አግኝቷል ። የ40 ዓመቱ አዲስ አሰልጣኝ ጆዋዎ ፔራይራ በፖርቹጋል ሊጋ የደረጃ ሰንጠረዡ መሪው ፖርቹጋል ሊዛቦንን ለማሰልጠን መፈራረሙ ተሰምቷል ። ጆዋዎ በአሰልጣኝነት የተፈራረመው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር እስከ 2027 ድረስ መሆኑን ቡድኑ ዛሬ ይፋ አድርጓል ። ለስፖርቲንግ 154 ጊዜያት ተሰልፎ የተጫወተ በቡድኑ የሚታወቅ አሰልጣኝ ነው ። የጥቅምት 18 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የቀድሞው የሊዘቦን አሰልጣኝ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ እንደሚሄዱ ይፋ የሆነው ከአንድ ሳምንት ከግማሽ በፊት ነበር ። ማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ቴሪክ ቴን ሐግን ለመተካት ለስፖርቲንግ ሊዘቦን 10 ሚሊዮን ዩሮ መክፈሉም ተሰምቷል ።   

በሩድ ቫን ኒስተልሮይ ጊዜያዊ አሰልጣኝነት በመመራት አራተኛ ግጥሚያውን ትናንት ያደረገው ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሬሚየር ሊጉ ሌስተር ሲቲን 3 ለ0 አሸንፏል ። ከስፖርቲንግ ሊዛቦን የተገኙት አዲሱ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ዛሬ ብሪታንያ ከገቡበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ችግሮች የገጠመው ማንቸስተር ዩናይትድን ይረከባሉ ተብሏል ። በርካቶች ከአዲሱ አሰልጣኝ ብዙ ይጠብቃሉ ። ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት በኦልድ ትራፎርድ ሜዳው ላይሰተር ሲቲን አስተናግዶ 3 ለ0 ባሸነፈበት ግጥሚያ ደጋፊዎቹን አስፈንጥዟል ። ብሩኖ ፈርናንዴዝ፤ ቪክቶር ክሪስታንሰን እና አሌሃንድሮ ጋርማቾ ግቦቹን አስቆጥረዋል ። 15 ነጥብ ያለው ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሬሚየር ሊጉ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።

ፕሬሚየ ርሊግ፦

ማንቸስተር ሲቲ በብራይተን 2 ለ1 ጉድ ሲሆን፥ ሊቨርፑል አስቶን ቪላን 2 ለ0 አሸንፏል ። የማሸነፊያዋን ግብ ያስቆጠረው ሞ ሳላህ የመጀመሪያው ግብ በዳርዊን ኑኔዝ እንዲቆጠር አመቻችቷል ። በዚህ የጨዋታ ዘመን 10 ግቦችን እና 10 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ማመቻቸት የቻለው ሞ ሳለህ የምሽቱ ኮከብ ሁኗል ። ዳርዊን ኑኔዝ ተቀይሮ ከመውጣቱ በፊት ሁለት ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ሙከራዎቹ ዒላማቸውን ስተዋል ። አስቶን ቪላ ብዙም በመከላከል ቢያተኩርም 9 የማእዘን ምቶችን አግኝቷል ። የጥቅምት 11 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ መሪው ባዬር ሙይንሽን ሳንክት ፓውሊን ገጥሞ 1 ለ0 አሸንፏል። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Alexandra Beier/AFP/Getty Images

1 ለ0 ሲመራ የነበረው ማንቸስተር ሲቲ ታሪካዊ የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል ።  ለማንቸስተር ሲቲ ብቸኛዋን ቀዳሚ ግብ ያስቆጠረው ኧርሊንግ ዖላንድ በፕሬሚየር ሊጉ እስካሁን 12 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ነው ።   ማንቸስተር ሲቲ በ23 ነጥብ ሊቨርፑልን ይከተላል ። ቸልሲ አርሰናልን አስተናግዶ አንድ እኩል ተለያይቷል ። በዚህም መሠረት ቸልሲ በ19 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል ። አርሰናል በተመሳሳይ 19 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።

በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ መሪው ባዬር ሙይንሽን ሳንክት ፓውሊን ገጥሞ 1 ለ0 አሸንፏል ፥ በ26 ነጥብ ቡንደስሊውን ይመራል ።   በ21 ነጥብ የሚከተለው ኤርቤ ላይፕትሲሽ ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር ትናንት ገጥሞ ያለምንም ግብ ተለያይቷል ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከላይፕትሲሽ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፥ ሽቱትጋርትን ትናንት 3 ለ0 ድል ማድረግ ችሏል ። ኤምሬ ቻንን በ27ኛ ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ያጣው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በማይንትስ የ3 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል ።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW