1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኅዳር 10 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 10 2016

አዲስ አበባ ውስጥ በታላቁ ሩጫ ዝግጅት ትናንት ታላቅ ተቃውሞ ተስተጋብቷል ። ኢትዮጵያዊው በሙሉ ድምፅ የአፍሪቃ ቡጢ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል። እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የማሊ አቻውን በደርሶ መልስ 6ለ0 ኩም አድርጓል ። የጀርመን ቡድን በቱርክ ተሸንፏል ። ተጨማሪ ዘገባዎች አካተናል ።

የጀርመን እና ቱርክ የወዳጅነት ጨዋታ ካለቀ በኋላ የአሸናፊው የቱርክ ቡድን ደጋፊዎች
የጀርመን ቡድንን ለወዳጅነት ቤርሊን ከተማ ውስጥ የቱርክ ብሔራዊ ቡድንን 3 ለ2 ካሸነፈ በኋላ ደጋፊዎች ደስታቸውን ሲገልጹምስል Federico Gambarini/dpa/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

አዲስ አበባ ውስጥ በታላቁ ሩጫ ዝግጅት ትናንት ታላቅ ተቃውሞ ተስተጋብቷል ። ኢትዮጵያዊው በሙሉ ድምፅ የአፍሪቃ ቡጢ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል።  ጨማሪ ዘገባዎች ይኖሩናል ። እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያሴቶች ብሔራዊ ቡድን የማሊ አቻውን በደርሶ መልስ 6ለ0 ኩም አድርጓል ። ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ አንድ ጨዋታ ብቻ ይቀረዋል ። የወንዶቹ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በነገው ዕለት ከቡርኪና ፋሶ ጋ ለዓለም ዋንጫየማጣሪያ ግጥሚያ ያከናውናል ። ሞሮኮ ውስጥ ከሴኔጋል ጋ ያደረገው ጨዋታ ተቋርጦ ነበር ። በሜዳ ቴኒስ ፉክክር የዓለማችን ምርጡ ተጋጣሚ ኖቫክ ጄኮቪች ትናንት አሸንፏል ። የዩሮ 2024 አዘጋጅ ጀርመን በሜዳዋ ባደረገችው የወዳጅነት ግጥሚያ ትናንት በቱርክ ተሸነፈች ። አብላጫ የቱርክ ደጋፊዎች የነበሩበት የቤርሊኑ ስታዲየም በቱርክ ድል በደስታ ተናውጧል ። ተጨማሪ የስፖርት ዘገባዎችንም አካተናል ።

አትሌቲክስ

ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው 23ኛው የታላቁ ሩጫ ውድድር ላይ የተቃውሞ ድምፆች መስተጋባታቸው ተዘገበ ። አዲስ አበባ በተዘጋጀው የታላቁ ሩጫ ተሳታፊዎች በተለያዩ ጭፈራዎች ታጅበው ሆታ እና መፈክሮችን አሰምተዋል ። ከመፈክሮቹ መካከል አዲስ አበባን የሚመለከት ይገኝበታል ። «እየመጡ ነው» የሚሉ መፈክሮችም ተስተጋብተዋል ። በየዓመቱ በሚዘጋጀው የዘንድሮ 23ኛው ታላቁ ሩጫ ውድድር፦ አትሌት ቢኒያም መሀሪ በወንዶች፣ አትሌት መልክናት ውዱ በሴቶች አሸናፊዎች ሆነዋል ።

ቡጢ

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን ለአራት ሰአታት ከፈጀ ስብሰባ በኋላ የአፍሪቃ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው ባለፈው ቅዳሜ በሙሉ ድምፅ ተመረጡ ። አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው 47ኛው የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከዐርባ በላይ የዓለም አቀፍ የቡጢ ማኅበር (IBA) ቡድኖች አመራር መገኘታቸው ታውቋል ። አቶ ኢያሱ እንዳይመረጡ ዛቻ እና ማስፈራሪያ የሚሰነዝሩ ብሎም በገንዘብ ጉቦ ከውድድሩ ለማስወጣት ሙከራ ያደረጉ እንደነበረም ተገልጿል ። አቶ ኢያሱ ካሜሮናዊው ዕጩ በርትራንድ ሜንዱጋ እና ሞሮኳዊው ሞሐመድ ቦድርን አሸንፈው ነው የተመረጡት ። 

የጥቅምት 27 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

አቶ ኢያሱ በአፍሪቃ ስፖርት አመራርነት ከፍተኛ ደረጃ በመድረስ ከዚህ ቀደም ከሚታወቁት ጥቂት ኢትዮጵያውያን መካከል  አንዱ ሆነዋል ። የካፍ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ምንጊዜም ስማቸው ሕያው ሆኖ ይነሳል ። ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ የአፍሪቃ ባድሜንተን ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚደንት እንዲሁም የዓለም ባድሜንተን ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚደንት ሆነው አገልግለዋል ። አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ደግሞ በካፍ የኢትዮጵያ ተወካይ እና የካፍ ፕሬዚደንት አማካሪ ሆነው በአፍሪቃ ስፖርትከፍተኛ ደረጃ ከደረሱ ኢትዮጵያውያን ይጠቀሳሉ ። አቶ ኢያሱ ከኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወደ አፍሪቃ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ከፍ ብለው በተለይ ደግሞ በሙሉ ድምፅ በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል ። ድሉ የመላው አፍሪቃውያን ነው ብለዋል።  

የአቶ ኢያሱ ወሰን የአፍሪቃ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጥ ለኢትዮጵያ ቡጢ ስፖርት ፋይዳው ከፍተኛ ነው ።ምስል Sergiy Tryapitsyn/PantherMedia/IMAGO

ከዚህ ባሻገር ዓለም አቀፉ የቡጢ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት እና የቦርድ አባላት አዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ላይ ቡጢ እና ቴኳንዶን ጨምሮ ሁሉንም ስፖርት ያካተተ የቤት ውስጥ ስፖርት ውድድር የሚካሄድበት የስፖርት ተቋም ለመገንባት ቃል መግባታቸውን አቶ ኢያሱ ገልጸውልናል።  ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ሕንጻን አካቶ ወደፊት አዲስ አበባ ውስጥ ይገነባል የተባለው የስፖርት ተቋም አንድ ሺህ አልጋ እና ጂም እንዲሁም ዋና እንደሚኖረው ተገልጿል ። ለዚህ አገልግሎትም ዓለም አቀፍ የስፖርት ቡድኑ አባላት 3,500 ካሬ ሜትር ቦታ ካርታ መረከባቸውን አቶ ኢያሱ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። ለተቋሙ ግንባታ የንድፍ ሥራ ውድድር ለማድረግም አቶ ኢያሱ የግንባታው የቦርድ አባል ሆነው ወደ ግብጽ በቅርቡ እንደሚጓዙ ዐሳውቀዋል።

እንደ አቶ ኢያሱ ገለጻ፦ ከውጭ የመጡት የስፖርት ፌሴሬሽን አባላት አዲስ አበባ ውስጥ ዓለም አቀፍ የቡጢ ውድድሮችን ለማድረግ ውሳኔ ማስተላለፋቸውን ይፋ አድርገዋል ። ወደፊት በኢትዮጵያ በእየ መንደሮች እና ትምህርት ቤቶች የቡጢ ስፖርት እንዲጎለብት እንደሚያደርጉ፤ ቡጢ ለጤና አስፈላጊ መሆኑ በአንዳንድ ሃገራት ስለተረጋገጠ በመላው አፍሪቃም በትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ ለማድረግ እንደሚጥሩ አክለዋል ። ከዚያ ባሻገር ለእያንዳንዱ የአፍሪቃ ቡጢ ፌዴሬሽን ሃምሳ ሃምሳ ሺህ ዶላር (ሃያ ሺህ በገንዘብ ሠላሳ ሺህ በቁሳቁስ)እንዲሰጥ ማስወሰናቸውን ተናግረዋል። 

ቀደም ሲል የኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪቃ ቡጢ ፌዴሬሽኖች ከውድድር ገቢ እንደማያገኙ ይልቁንስ በመሀል በከፍተና ደረጃ የተደራጁ ደላሎች ገንዘቡን ይቀራመቱት ነበር ብለዋል ። ይህ በሳቸው የሥልጣን ዘመን እንደሚቀር ቃል ገብተዋል ።

የጥቅምት 19 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ከአፍሪቃ ቡጢ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን ጋ የተደረገውን ሙሉ ቃለ መጠይቅ እዚህ የድምፅ ማጫወቻውን በመጠቀም  አለያም በፌስቡክ እና ቴሌግም ገጾቻችን ላይ ማድመጥ ይቻላል ።

ሙሉ ቃለ መጠይቅ የአፍሪቃ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡት አቶ ኢያሱ ወሰን ጋ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣርያ 3ኛ ዙር የመልስ ጨዋታ የማሊ አቻውን በደርሶ መልስ 6 ለ0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችሏል ። ትናንት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው ግጥሚያ ሁለቱን ግቦች በ35' እና 45' ደቂቃ ላይ እሙሽ ዳንኤል አስቆጥራለች ። በ65' መዓድን ሳህሉ፣ እንዲሁም በ69' መሳይ ተመስገን አስቆጥረዋል።  ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ የመጨረሻው ዙር ሞሮኮን ትገጥማለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ የወንዶች ቡድን በበኩሉ፦ ለቡርኪና ፋሶው የነገ ጨዋታ በሞሮኮ ካዛብላንካ ዝግጅቱን አጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል ። ትናንት በሞላይ ራሺድ ስታዲየም ልምምዱን ማከናወኑንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዐስታውቋል ። የኢትዮጵያ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣርያ 2ኛ የምድብ ጨዋታ ቡርኪና ፋሶን በኤል አብዲ ስታዲየም ማክሰኞ የሚገጥም ይሆናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረቡዕ ዕለት በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከሴራሊዮን ጋር ተጫውቶ ያለ ጎል አቻ መለያየቱ ይታወሳል ። ቡድናችን በሰው ሀገር ሩቅ ተጉዞ ለመጫወት የተገደደው የፊፋን መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ኢትዮጵያ ማዘጋጀት ስላልቻለች ነው ።

የጥቅምት 12 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የፊፋን መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ግንባታን ኢትዮጵያ እስካሁን ተግባራዊ አለማድረጓ ለተጨማሪ ወጪ፤ የስታዲየም ገቢ ወጪ፤ የተጨዋቾች የረዥም በረራ ጉዞ ድካም እንዲሁም ከሀገር ውስጥ ደጋፊዎች በሜዳ ሲጫወቱ የሚኖረውን የሞራል ስንቅ እንዲያጡ ተደርገዋል ። ይህን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ሆነ የስፖርት ሚኒስቴር በአስቸኳይ መፍትኄ ሊያገኙለት የሚገባ ጉዳይ ነው ሲሉ በርካቶች እየወተወቱ ነው።  ለእኛም ከአድማጮች ተመሳሳይ ጥያቄ ይቀርብልናል ። ወደፊት የሚመለከታቸው አካላት ሐሳባቸውን እና ምክንያታቸውን ለአድማጮች ለማካፈል ፈቃደኛ ከሆኑ ለማስተናገድ ዝግጁ ነን ። 

የአውሮጳ እግር ኳስ የማጣሪያ ውድድር

የአውሮጳ  ዋንጫ የእግር ኳስ የማጣሪያ ጨዋታዎች ቀጥለው ዛሬ እና ነገም ይከናወናሉ ። ዛሬ ማታ ሰሜን መቄዶኒያ ከእንግሊዝ፤ ቺቺኒያ ከሞልዶቫ፤ ዩክሬን ከጣሊያን፤ አልባኒያ ከፋራዖ ደሴቶች፤ ሰሜን አየርላንድ ከዴንማርክ ፤ እንዲሁም ስሎቫኒያ ከካዛክስታን ጋ ይጋጠማሉ ። በነገው እለት ደግሞ፦ ግሪክ ከፈረንሳይ፤ እሥራኤል ከፊንላንድ፤ ሩማንያ ከስዊትዘርላንድ፤ ጂብራልታር ከኔዘርላንድ፤ ኮሶቮ ከቤላሩስ፤ ክሮሺያ ከአርሜኒያ እንዲሁም ዌልስ ከቱርክ ጋ ሊጋጠሙ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል ።

በተለይ ቱርክ ቅዳሜ ዕለትቤርሊን ከተማ ውስጥ የጀርመን ብሔራዊ ቡድንን 3 ለ2 ድል ማድረጓ ከፍተኛ የሞራል ሥንቅ ሆኗታል ። ጀርመን ከቱርክ ጋ ባደረገችው የወዳጅነት ጨዋታ አብዛኛ ስታዲየሙ የቱርክ ዝርያ ባላቸው ተሞልቶ ነበር ። ቱርካውያን ከቱርክ ውጪ በብዛት የሚኖሩት ጀርመን ውስጥ ነው ።

የዶይቸ ቬለ የቤርሊኑ የስፖርት ጋዜጠኛ ሔኮ ፍሎሬስ የቅዳሜውን ግጥሚያ ቤርሊን ኦሎምፒክ ስታዲየም ተገኝቶ ተከታትሏል ። ጨዋታው ጀርመን በሀገሯ የምታደርገው ሳይሆን የመልስ ጨዋታ ቱርክ ውስጥ የምታደርግ ይመስል ነበር ሲልም አግራሞቱን ገልጿል ።

«በተለምዶ እንደዚያ ያለ ድባብ ሔርታ ቤርሊን ወይንም አሁን ለሻምፒዮንስ ሊግ ዑኒዮን ቤርሊን  በሜዳው ሲጫወት እንኳን አታገኝም የጀርመን እና የቱርክ ግጥሚያ ሙሉ ለሙሉ ሌላ አይነት ስሜት የነበረው ነው ስታዲየሙ ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር እንዳለመታደል ሆኖ ለጀርመን ቡድን ምናልባትም 90 በመቶው ስታዲየምየገባው ታዳሚ የቱርክ ቡድን ደጋፊ ነበር   ስለዚህ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ፤ በእያንዳንዱ ኳስ ማቀበል የቱርክ ቡድን ድጋፍ ነበረው ጀርመን ከሜዳዋ ውጪ ያደረገችው ጨዋታ አይነት ነበር ስሜቱ ውጤቱንም ስናይ ቱርክ 3 ያሸነፈችበት ታሪካዊ ድል ነው እናም ለዚያ ውጤት ታዳሚያኑ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ብዬ አስባለሁ »

የጀርመን እና የቱርክ የእግር ኳስ ቡድኖች ደጋፊዎች ቤርሊን ከተማ ስታዲየም ውስጥ። ቱርክ ጀርመንን በሜዳዋ ለወዳጅነት ገጥማ በማሸነፍ ታሪክ ሠርታለችምስል Markus Schreiber/AP/picture alliance

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በተደጋጋሚ መሸነፉን ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩት አዲሱ አሰልጣኝ ጁሊያን ናግልስማንም ማስቆም አለመቻላቸው ጥያቄዎችን አስነስቷል ። ጀርመን የአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫን ለማሰናዳት ከመንፈቅ ብዙም ያልገፋ ጊዜ ለቀራት ጀርመን ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ነው ።

የሜዳ ቴኒስ

በፕሮፌሽናል ቴኒስ ተጨዋቾች (ATP )የፍጻሜ ግጥሚያ የ36 ዓመቱ ሠርቢያዊ ኖቫክክ ጄኮቪች ለሰባተኛ ጊዜ ድል ተቀዳጅቷል ። ኖቫክ ትናንት ለድል የበቃው ጣሊያናዊ ተጋጣሚው ጃኒክ ሲነርን ሁለት ጊዜ 6 ለ3 በማሸነፍ ነው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW