1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኅዳር 12 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 12 2015

የዓለም ዋንጫው ከመጀመሩ አስቀድሞም አዘጋጇ ሀገር የሰብአዊ መብቶችን አታከብርም በሚል ላይ በተለይ አውሮጳውያን ቡድኖች ብርቱ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው። ውዝግቡ በቀጠር እና በእግር ኳስ ቡድኖቹ ብቻ ሳይወሰን ፊፋንም አካቷል።

Fußball-WM Katar 2022 | Senegal v Niederlande
ምስል Ulmer/Teamfoto/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ እሁድ በኧል ባይት ስታዲዬም በአዘጋጇ ሀገር ቀጠር እና ኢኳዶር ግጥሚያ ተጀምሯል።  የዓለም ዋንጫው ከመጀመሩ አስቀድሞም አዘጋጇ ሀገር የሰብአዊ መብቶችን አታከብርም በሚል ላይ በተለይ አውሮጳውያን ቡድኖች ብርቱ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው። ውዝግቡ በቀጠር እና በእግር ኳስ ቡድኖቹ ብቻ ሳይወሰን ፊፋንም አካቷል። 

የዓለም ዋንጫ

በየአራት ዓመቱ የሚካኼደው የዓለም ዋንጫ ትናንት በአዘጋጇ ኳታር እና ኤኳዶር የመክፈቻ ግጥሚያ ተጀምሯል። በትናንቱ የመክፈቻ ግጥሚያ በአብዛኛው በመከላከል ላይ ያተኮረችው አስተናጋጇ ቀጠር በኢኳዶር የ2 ለ0 ሽንፈት ገጥሟታል። የኢኳዶር አጥቂ ኤነር ቫለንሺያ ያገባው አንድ ግብ ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ባይሻርበት ኖሮ ሔትሪክ በመሥራት በመክፈቻው እለት ሦስት ግቦች ይመዘገቡለት ነበር። በጨዋታው ወቅት ጉዳት የደረሰበት ይኸው አጥቂ ቫለንሺያ ለቀጣዩ ጨዋታ ከጉዳቱ አገግሞ እንደሚደርስ አሰልጣኙ ተናግረዋል። የኢኳዶር አሰልጣኝ ጉስታቮ አልፋሮ ዐርብ ዕለት ከኔዘርላንድ ጋር በሚኖረው ግጥሚያ ቫለንሺያ እንደሚሰለፍ በእርግጠኝነት ዐስታውቀዋል።

የዓለም ዋንጫ ግጥሚያ ዛሬ ቀጥሎ እንግሊዝ ኢራንን 6 ለ2 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፋታለች። ለእንግሊዝ ጁድ ቤሊንግሀም በ35ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል። ሌሎቹን ግቦች ቡካዮ ሳካ በ43ኛ እና 62ኛ ደቂቃ ሲያስቆጥር፤ ራሒም ስተርሊንግ 45ኛው ደቂቃ አልቆ በጭማሪው አንድ ደቂቃ፤ ማርኩስ ራሽፎርድ በ71ኛው ደቂቃ ላይ፤ እንዲሁም ጃክ ግሪሊሽ በ90ኛው ደቂቃ ግቦቹን ከመረብ አሳርፈዋል። ለኢራን ሁለቱን ግቦች መህዲ ታረሚ 65ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታ እንዲሁም90 ደቂቃው አክትሞ በጭማሪው 13ኛ ደቂቃ ላይ በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል። ከሁለቱ ቡድኖች በተጨማሪ ሴኔጋል እና ኔዘርላንድም የመጀመሪያ ጨዋታቸውን እያካሄዱ ነው።

የዓለም ዋንጫ በአዘጋጇ ኳታር እና ኤኳዶር ግጥሚያ ከመጀመሩ በፊት የመክፈቻ ስነስርዓቱ በከፊልምስል Elsa/Getty Images

ለመሆኑ ሴኔጋልን ጨምሮ ዘንድሮ የአፍሪቃ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ይደርሱ ይሆን?

የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1930 ከተኪያሄደበት ጊዜ አንስቶ ለሩብ ፍጻሜ መድረስ የቻሉት ሦስት ሃገራት ብቻ ናቸው። ካሜሩን በ1990፤ ሴኔጋል በ2002 እንዲሁም ጋና በ2010 ዓ.ም። እንዲያም ሆኖ ከእነዚህ አፍሪቃን ከወከሉ ሃገራት መካከል ወደ ግማሽ ፍጻሜው የደረሰ አንድም ቡድን የለም።  በዓለም ዋንጫ ታሪክ በብዛት በመሳተፍ ከአፍሪቃ ሃገራት ካሜሩንን የሚስተካከል የለም። የካሜሩን ቡድን እንደ ስያሜያቸው «የማይደፈሩት አናብስት» በእርግጥም በዓለም ዋንጫ ክብረ ወሰን ከአጠገባቸው የሚደርስ አልተገኘም። የካሜሩን «የማይደፈሩት አናብስት» በዓለም ዋንጫ መድረክ ለስምንት ጊዜያት መሳተፍ ችለዋል። ግን ደግሞ እነሱም ቢሆኑ ለግማሽ ፍጻሜ መድረስ አልቻሉም።

ምናልባት ዘንድሮ እንደ ጀርመን ያሉ የአውሮጳ ቡድኖች የተጠበቁትን ያህል ጠንካራ አለመሆን አፍሪቃውያኑ ግማሽ ፍጻሜ የመድረስ እድላቸውን ያሰፋ ይሆን? ደካማ ተጋጣሚዎችን ሲያገኝ በትንሹ 6 ለ0 የማሸነፍ ልምድ ያለው የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ትናንት ከንዑሷ ዖማን ጋር ተጋጥሞ ያሸነፈው በአንዲት ብቸኛ ግብ ብቻ ነው። በእርግጥ እንደ ፈረንሳይ፤ ቤልጂየም፤ ስፔን እና ብራዚል ያሉ ቡድኖች ምንጊዜም አስተማማኝ ሆነው ነው ብቅ የሚሉት። ዘንድሮ በዓለም ዋንጫ አፍሪቃን የሚወክሉት፦ ካሜሩን፤ ሞሮኮ፤ ቱኒዝያ፤ ጋና እና ሴኔጋል ናቸው። ቡድኖቹ ወደ ግማሽ ፍጻሜ እንዲያልፉ ከወዲሁ እንመኛለን።

ከዚሁ ከዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ዘገባዎች ሳንወጣ፦ ቀጠር የምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ትናንት ሲከፈት በደማቅ ሁኔታ ነበር። በመክፈቻው የሙዚቃ ሥነስርዓት አውሮጳውያን አቀንቃኞች ቀጠር ሰብአዊ መብቶችን አታከብርም በሚል አልተገኙም። ሆኖም የደቡብ ኮሪያው ታዋቂ ወጣት አቀንቃኙ ዩንግ ኮክ ና በኧል ባይት ስታዲየም ውስጥ የመክፈቻ ሙዚቃውን ተጫውቷል። ቀጠር የሰብአዊ መብቶችንም ሆነ የሠራተኛ መብቶችን አታከብርም በሚል በርካታ የአውሮጳ ፖለቲከኞች እና የመብት ተሟጋቾች ተቃውሞዋቸውን ሲያሰሙ ሰንብተዋል።

የዓለም ዋንጫ በአዘጋጇ ኳታር እና ኤኳዶር ግጥሚያ ከመጀመሩ በፊት የመክፈቻ ስነስርዓቱ በከፊልምስል Elsa/Getty Images

ያም ብቻ አይደለም አንዳንድ የአውሮጳ ሃገራት እግር ኳስ ቡድኖች ሜዳ ውስጥ ጭምር ተጨዋቾቻቸው ክንዶቻቸው ላይ የሚጠለቁ ዓርማዎችን በማሰር ገብተው ተቃውሞ እንዲያደርጉ ቀደም ሲል ወስነው ነበር። በኋላ ላይ ግን ቡድናቱ ውሳኔያቸውን ማጠፋቸው ታውቋል። ሰባት የአውሮጳ ቡድኖች የቀስተ ደመና ምልክት ለማድረግ የነበራቸውን እቅድ መሰረዛቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ዛሬ ዘግቧል።

ብሪታንያ ጀርመን ከ7ቱ ሃገራት ውስጥ ይመደባሉ። ሰባቱ ቡድኖች ዛሬ ያወጡት መግለጫ፦ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፊፋ (FIFA) የቡድኖቻቸው አምበሎች በጨዋታ ሜዳ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት መብቶችን ለመደገፍ ምልክቱን እጃቸው ላይ ካደረጉ ስፖርታዊ ማዕቀብ እንደሚጥልባቸው «በጣም ግልጽ» ማድረጉን ጠቅሶ እንደ ብሔራዊ ፌደሬሽኖች ተጨዋቾቻችንን ለማዕቀብ በሚጋለጡበት ደረጃ ላይ እንዲሆኑ ማድረግ አንችልም ብሏል። በዚህ የተነሳም የእንግሊዝ፣ የዌልስ፣ የቤልጂግ፣ የዴንማርክ የጀርመን የኔዘርላንድስ እና የስዊትዘርላንድ ፌደሬሽኖች በፊፋ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች አምበሎቹ ምልክቱን እጃቸው ላይ ለማድረግ እንዳይሞክሩ  መጠየቃቸውን መግለጫው ዐስታውቋል። የቡድኖቹ ውሳኔ የተሰማው የእንግሊዝ  የኔዘርላንድስ እና የዌልስ ቡድኖች ዛሬ ያካሄዷቸው ግጥሚያዎች ከመጀመራቸው ከጥቂት ሰዓታት አስቀድሞ ነው።

ምንም እንኳን ፊፋ በቀጠር የዓለም ዋንጫ ምልክቱን በሚያደርጉ ተጫዋቾች ላይ ማዕቀብ እንደሚጥል ቢያሳውቅም፣ የጀርመኑ አንጋፋ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ለመደገፍ ክንድ ላይ የሚጠለቀውን የቀስተ ደመና ምልክት ለማድረግ ማቀዱን ተናግሮ ነበር።

የሴኔጋል እና የኔዘርላንድስ እግር ኳስ ቡድኖች በቀጠር የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ግጥሚያ 2022ምስል ODD ANDERSEN/AFP

የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚቃወሙት የቀጠር ሕግጋት ቀጠር ለዓለም እግር ኳስ ዋንጫ አዘጋጅነት ከተመረጠችበ ጊዜ አንስቶ ሲያወዛግብ የቆየ ጉዳይ ነው። በተለይ የቀጠር ዓለም አቀፍ እና የዓለም ዋንጫ አምባሳደር ካህሊድ ሣልማን በቅርቡ ከአንድ የጀርመን ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት «የአዕምሮ ውስጥ ጉዳት» ነው በማለታቸው ቁጣ አጭሯል ሲል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ጀርመን ኮሎኝ ከተማ ውስጥ ላለፉት 27 ዓመታት የተለያዩ እግር ኳስ ጨዋታዎችን በማሳየት የሚታወቀው «ሎታ» የተሰኘ መጠጥ ቤት እንደ የጀርመን እግር ኳስ ቡድን ተቃውሞውን አስተጋብቷል። መጠጥ ቤቱ ዘንድሮ ከቀጠር የሚተላለፈውን የእግር ኳስ ጨዋታ በቴሌቪዥን ላለማሳየት ወስኗል። ይኸው መጠጥ ቤት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 በነበረው የዓለም ዋንጫ በሁለት ቴሌቪዥኖች እና ተለቅ ባለ ስክሪን የእግር ኳስ ጨዋታዎቹን ለደንበኞቹ ሲያሳይ ነበር። የመጠጥ ቤቱ ባለቤቶች ከሆኑት መካከል አንዱ የሆኑት ፔተር ሲመርማን ዘንድሮ ጨዋታዎችን ለምን እንደማያሳዩ ምክንያታቸውን ለዶይቸ ቬለው ኦሊቨር ፒፐር ተናግረዋል።

«በዋናነት ተቃውሞዋችንን ማሰማት የፈለግነው ሙሉ ለሙሉ በሙስና የተጨማለቀው ፊፋ ላይ ነው። ለፊፋ ገንዘብ እንጂ የሰብአዊ መብት እና የእግር ኳስ ባሕል ደንታው አይደለም። ቀጠር የሰብአዊ መብት፣ የሴቶች መብት፤ ጾታቸውን የሚለዩበት ፍላጎታቸውን፤ን ወሲባዊ ፍላጎትንም ከተቃራኒ ጾታ ውጪ የሚመለከቱትን መብት የማታከብር የሥራ ኹኔታው የተበላሸባት ሀገር እንደሆነች ግልጽ ነው።»

ይኸው ኮሎኝ ከተማ ውስጥ የሚገኘው መጠጥ ቤት አስተናጋጇ ሀገር ቀጠር ከኢኳዶር ጋር የዓለም ዋንጫ እግር ኳስ መክፈቻ ስታደርግ እንደሚዘጋ ቀደም ሲል ገልጦ ነበር። ዛሬ ዩናይትድ ስቴትስ ከዌልስ ጋር ስትጋጠምም ሆነ በሌሎቹ ቀናት ከዓለም ዋንጫው የእግር ኳስ ጨዋታዎች ውጪ የሆኑ ጉዳዮች ላይ መጠጥ ቤቱ እንደሚያተኩር ባለቤቱ ተናግረዋል።   

የፊፋ ፕሬዚደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በቀጠር 2022 የዓለም ዋንጫ ምስል Robert Michael/dpa/picture alliance

የፊፋ ፕሬዚደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የሁሉም ስሜት ይሰማኛል በማለት ቅዳሜ ዕለት አውሮጳውያንን የሚተች ንግግር አሰምተዋል።  በዓለም ዋንጫ መክፈቻ ዋዜማ የፊፋው ፕሬዚደንት በተለይ አውሮጳውያንን በሞራል ጥያቄ ጉዳይ በብርቱ ተችተዋል።

«እኔ ራሴ አውሮጳዊ ነኝ። በእውነቱ አውሮጳዊነት ይሰማኛል ብቻ ሳይሆን አውሮጳዊ ነኝ። እንደሚመስለኝ እኛ አውሮጳውያን ለሌሎች ሕዝቦች የግብረገብ ትምህርት መስጠት ከመጀመራችን በፊት ላለፉት 3000 ዓመታት ለፈጸምነው ለሚቀጥሉት 3000 ዓመታት ይቅርታ መጠየቅ አለብን።»

አትሌቲክስ፦

ከ40 ሺሕ በላይ ተሳታፊዎች የተካፈሉበት የ2015 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እሁድ በአዲስ አበባ ተካሒዷል። በውድድሩ በወንዶች አቤ ጋሻው አሸናፊ ሲሆን ኃይለማርያም አማረ እና ገመቹ ዲዳ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ወጥተዋል። በሴቶች ትዕግስት ከተማ ውድድሩን በበላይነት ስታጠናቅቅ መስታወት ፍቅር እና ፎተ ተስፋይ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል።

በጁጂትሱ የአፍሪቃ ምክትል ሻምፒዮን የብር እና የነሐስ መዳሊያ ያገኘችው የመጀመሪያዋ ሴት ኢትዮጵያዊት ወጣት አትሌት መስከረም ዓለማየሁ  በ26 ዓመቷ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷን የጁዶ እና ጁጂትሱን ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡት ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ ተናግረዋል።  

ከልጅነቷ ጀምሮ ጁዶ እና ጁ-ጂትሱ ስፖርትን ለዓመታት የሠራችው መስከረም ዓለማየሁ በስተቀኝ የብር ሜዳይ አንጠልጥላምስል Tsegay Degneh

መስከረም በጁዶ እና ጁ-ጂትሱ ስፖርትን ለዓመታት ከልጅነቷ ጀምሮ የሠራች ሲሆን፤  እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2019 በሞሮኮ የብር እና የነሃስ ሚዳልያ በመውሰድ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊት በመሆን ታሪክ ሠርታለች። ለ2022 የወርልድ ጌምስ እጩ ሆናም እንደነበር ዶ/ር ጸጋዬ ገልጠዋል።  ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአቡ ዳህቢ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ላይም በብቃት ተሳትፋም ወደ አገሯ መመለሷንም አክለዋል። በዓለምቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን የሴቶች ክፍል በአገኘችው እድል የርቀት የማኔጅመንት ስልጠናም ጀምራ እንደነበር ተገልጧል።  በኢትዮጵያ ስፖርቱ እንዲያደግ እና ዕውቅና እንዲያገኝ በከፍተኛ ሁኔት ያለመታከት ስትሯሯጥ እና ስትደክም ነበር ሲሉ ዶ/ር ጸጋዬ አወድሰዋታል። UNHCR ጁዶ ለስደትኞች በሚል ፕሮግራም ስልጠና ለመስጠት ባቀረበው ፕሮግራም ላይ ስልጠና ለመስጠትም እየተዘጋጀች ነበር። በተጨማሪም ዩናይትድ ኔሽን የስፖርት ለከባቢ አየር Call for action እንቅስቅሴ ላይም ስፖርቷን በመወከል መሳተፏን የደረሰን ዘገባ ይጠቁማል።  

ወጣት አትሌት መስከረም ዓለማየሁ  ቀብር ሥነስርዓት አዲስ አበባ ውስጥ ትናንት ቅዳሜ መፈጸሙም ተገልጧል።  

ጀርመናዊው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም አሽከርካሪ ሰባስቲያን ቬትልምስል Andy Hone/Motorsport Images/IMAGO

ጀርመናዊው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም አሽከርካሪ ሰባስቲያን ቬትል ከውድድር ዓለም መሰናበቱን ዐስታውቋል። የሬድ ቡል አሽከርካሪው ሰባስቲያን ከውድድር መሰናበቱን በገለጠበት የትናንቱ ሽቅድምድም 10ኛ ደረጃን አግኝቷል። በዚሁ ሽቅድምድም ማማክስ ፈርሽታፐን አሸንፏል። የፌራሪው ሻርል ሌክሌር እንዲሁም የሬድ ቡል አሽከርካሪው ሠርጂዮ ፔሬዝ 2ኛ እና 3ኛ ወጥተዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW