1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኅዳር 17 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 17 2016

የፊታችን እሁድ ስፔን ውስጥ ለሚካሄደው የቫለንሺያ ማራቶን አትሌት ቀነኒሳ እና ዓልማዝ አያና እጅግ ከሚጠበቁት አትሌቶች መካከል ናቸው ።ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ከሊቨርፑል ጋ ባደረገው ወሳኝ ግጥሚያ ሳያሸነፍ ቀርቷል ። ሁለቱም ነጥብ ተጋርተዋል ። አርሰናል በ1 ነጥብ ልዩነት ብቻ የመሪነቱን ስፍራ ተቆናጧል ። ሙሉ ዝግጅቱን ከታች መከታተል ይቻላል።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 4 ለ2 ባሸነፈበት ግጥሚያ
ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 4 ለ2 ባሸነፈበት ግጥሚያ ማኑ ኮኔ ግብ ካስቆጠረ በኋላምስል Uwe Kraft/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የፊታችን እሁድ ስፔን ውስጥ ለሚካሄደው የቫለንሺያ ማራቶን ኢትዮጵያውያኑአትሌት ቀነኒሳ እና ዓልማዝ አያና እጅግ ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል ናቸው ። የዩጋንዳ እና የኬንያ አትሌቶችም ዋነኛ ተፎካካሪዎች ሆነው ዘንድሮም ብቅ ብለዋል ። ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ከሊቨርፑል ጋ ባደረገው ወሳኝ ግጥሚያ ሳያሸነፍ ቀርቷል ። ሁለቱም ነጥብ ተጋርተዋል ። አርሰናል በአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ የመሪነቱን ስፍራ ተቆናጧል ። የአይንትራኅት ፍራንክፉርት ደጋፊዎች ከሜዳ ውጪ ከፖሊሶች ጋ የተጋጩበት እና የመሀል ዳኛ ጉልበታቸው ተጎድቶ የወጡበት የጀርመን ቡንደስሊጋ ፉክክር ተጠናክሮ ቀጥሏል ። የደረጃ ሰንጠረዡን ባዬር ሌቨርኩሰን እየመራ ነው ።  

የቫለንሺያ ማራቶን የፊታችን እሁድ ስፔን ውስጥ ሲከናወን ኢትዮጵያዊው ምርጥ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና የዩጋንዳው አትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጊ እጅግ ከሚጠበቁት መካከል ዋነኞቹ ናቸው ። በሴቶቹ ዘርፍ ደግሞ የሪዮ 2016 ዓ.ም የ10,000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለድሏ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዓልማዝ አያና ትጠበቃለች ።

የኅዳር 10 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የአምስት ጊዜያት የኦሎምፒክ ሜዳሊያ ባለድሉ ቀነኒሳ በቀለ፤ ባለፉት 25 ዓመታት ግድም የሩጫ ዘመኑ 19 ዓለም አቀፍ ድሎችን ተጎናጽፏል ። በተደጋጋሚ የእግር ጉዳት የሚቸገረው ቀነኒሳ በቀለ በማራቶን የሩጫ ዘርፍ ገና ብዙ ሊያደርግ እንደሚችል በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ድረ ገጽ ላይ ከአንድ ወር በፊት ጠቁሟል ። «በማራቶን ዘርፍ ከፍተኛውን አቅሜ የሚፈቅደውን ጥረት ገና አላሳካሁም» ብሏል ። «ለረዥም ጊዜያት በዘለቀ የእግር ጉዳት እየታገልሁ ነው» ሲልም ያሉበትን ተግዳሮቶች በዚህ መልኩ ጠቁሟል ። በእየጊዜው ልምምዱን በትጋት ቢፈጽምም በእግር ጉዳት የተነሳ ግን ሁሉኑም ልምምዶቹን ማጠናቀቅ አልቻለም ።

የአምስት ጊዜያት የኦሎምፒክ ሜዳሊያ ባለድሉ ቀነኒሳ በቀለምስል AP

 ለመሆኑ በእሁዱ የቫለንሺያ ማራቶን የሚጠበቁት እነማን ናቸው? የቀነኒሳ በቀለ እና የዓልማዝ አያናስ ልምምድ እና አቋም ምን ይመስላል?  በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት መርኃ ግብር ዋና አዘጋጅ ምስጋናው ታደሰ አትሌቶቹን ከረዥም ጊዜ አንስቶ በቅርበት ይከታተላል ። ፉክክሩ ብርቱ ይሆናል ብሏል ። 

ከምስጋናው ጋ የተደረገው ሙሉ ቃለ መጠይቅ እዚህ ይገኛል

This browser does not support the audio element.

የዩጋንዳው አትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጊም ከሚጠበቁት ጥቂት አትሌቶች መካከል አንዱ ነው ። ጆሹዋ የሚሰለጥንበት ጎዳናዎች ምንም እንኳን ጭቃማ ቢሆኑም ለባለንሺያው ማራቶን በሳምንት ከ140 እስከ 160 ኪሎ ሜትሮች ርቀት በመሮጥ እየተለማመደ መሆኑ ተገልጿል ። ልምምዱን የሚያደርገውም ከምዕራብ ኬንያ ድንበር 33 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የካፕቾሩዋ የልምምድ ማእከል መሆኑም ታውቋል ። ይህ አትሌት ለቀነኒሳ ምን ያህል ተግዳሮት ሊሆን ይችላል? በእርግጥ ሌሎችም አትሌቶች አሉ ። ኬኒያዊው አሌክሳንደር ሙቲሶ 2:03:29 በመሮጥ ፈጣን ሰአት አለው ።  ሲሳይ ለማ እና ልዑል ገብረ ሥላሴም በለንደን እና ፃለንኂያ ማራቶኖች ልምድ ያላቸው አትሌቶች ናቸው ።

በዜቶቹ ዘርፍ ደግሞ የሪዮ 2016 ዓም የ10,000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለድሏ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዓልማዝ አያና ትጠበቃለች ። በኦሎምፒክ ውድድር እጅግ የሚታወቁት ኢትዮጵያውያቱ ዓልማዝ አያና እና አትሌት ፀሓይ ገመቹ እንዲሁም በሱውል ማራቶን ባለፈው ዓመት ለድል የበቃችው ትውልደ ኬኒያዊ ሮማኒያዊቷ ሯጭ ጁዋን ቼሊሞ በቫለንሺያ ማራቶን የበርካቶች ዐይኖች ያረፉባቸው ናቸው ። 

የጥቅምት 27 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሁሉም አትሌቶች በዋናነት ዘንድሮ ግብ አድርገው የሚወዳደሩት የፓሪሱ ኦሎምፒክ ላይ ድል ለማስመዝገብ ነው ። የቫለንሺያ ማራቶንን ጨምሮ ዘንድሮ በዓለም ዙሪያ ዋነና ከተባሉት የማራቶን ውድድሮች መካከል የቤርሊን፤ ለንደን፤ ኒውዮርክ እና ቦስተን ማራቶኖች በዋናነት ይጠቀሳሉ ። በነዚህ ውድድሮች ክብረ ወሰኖችም ተመዝግበዋል ። አትሌቶቻችን ለፓሪሱ ኦሎምፒክ በጥሩ ሁኔታ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ምስጋናው ተናግሯል ። 

ቻይና ውስጥ ትናንት በተከናወነው የሻንጋይ ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሥራነሽ ይርጋ አሸነፈች ። ሥራነሽ ለድል የበቃችው ርቀቱን 2:21:28 በመሮጥ ነው ። በውድድሩ ከተሳተፉት መካከል አምስት አትሌቶች ከእሁዱ ውድድር በፊት በአማካይ ከ2:21ደቂቃ በታች ሰአት ያስመዘገቡ ነበሩ።

ቻይና ውስጥ በተከናወነው የሻንጋይ ማራቶን ያሸነፈችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሥራነሽ ይርጋ ምስል Getty Images

በሌላ የአትሌቲክስ ዜና፦ ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ውስጥ ኀዳር 15ቀን፣ 2016 ዓ.ም   በሁለቱም ፆታዎች ድብልቅ በተደረገው 19ኛው የኢትዮጽያ ማራቶን ሪሌ ውድድር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  1ኛ ወጥቶ አሸንፏል ። ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ኛ፤ እንዲሁም  ፌደራል ማረሚያ   ቤቶች 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል ። ለአሸናፊ የአትሌት ቡድኖች  የወርቅ፣ የብር፣ የነሐስ ሜዳሊያ ሽልማት እንዲሁም 1ኛ ለወጡት 40 ሺ፣ 2ኛ  ለወጡት 20 ሺ እና 3ኛ ደረጃ ላገኙት  15 ሺ  ብር የገንዘብ ሽልማት መሰጠቱም ተጠቁሟል ። በውድድሩ ከስድስት ክልሎችና ከተማ መሥተዳደሮች እንዲሁም ከዘጠኝ ቡድኖች የተውጣጡ 84 ወንድ እና ሴት አትሌቶች ተሳትፈዋል ።

የጥቅምት 19 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የአትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን  ከኅዳር 15-16 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በትግራይ ክልል በመቐለ ከተማ  አክሱም  ሆቴል መሰብሰቢያ  አዳራሽ ማካሄዱንም ፌዴሬሽኑ ዐስታውቋል ።

ፕሪሚዬር ሊግ

ቅዳሜ ዕለት ብሬንትፎርድን በካይ ሐቫርትስ 1 ብቸኛ ግን ደግሞ ወሳኝ ግብ ያሸነፈው አርሰናል በ30 ነጥብ የእንግሊዝ ፕሬሚየ ሊጉን በመሪነት ተቆናጧል ። በበርካቶች ዘንድ በከፍተና ደረጃ ሲጠበቅ የነበረው የማንቸስተር ሲቲ እና የሊቨርፑል ጨዋታ አንድ እኩል ተጠናቆ ነጥብ ተጋርተዋል ። በሜዳው የጨዋታ ብልጫ ዐሳይቶ ለነበረው ማንቸስተር ሲቲ ነጥብ መጣሉ ለደጋፊዎቹ እጅግ የሚያስቆጭ ነው ።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ ከሊቨርፑል ጋ ሲጋጠም። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Jason Cairnduff/AFP/Getty Images

በዚህም መሠረት ማንቸስተር ሲቲ ሊቨርፑልን በአንድ ነጥብ ብቻ በልጦ የ2ኛ ደረጃ ይዟል ። እጅግ መሻሻል ላሳየው ሊቨርፑል በ28 ነጥብ የ3ኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ ወደፊት ፕሬሚየር ሊጉ ላይ ብርቱ ፉክክር እንዲጠበቅ አድርጓል ። አስቶን ቪላም እንደ ሊቨርፑል 28 ነጥብ አለው ። ከስሩ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሀም በ26 እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ በ24 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ይዘው ይከታተላሉ ። ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት የበላይነትን ባሳየበት ጨዋታ ኤቨርተንን በሜዳው 3 ለ0 ኩም አድርጎ ተመልሷል ። ለማንቸስተር ዩናይትድ አሌሀንድሮ ጋርማቾ፤ ማርኩስ ራሽፎርድ እና አንቶኒ ማርሺያል አስቆጥረዋል ።  በርንሌይ እና ኤቨርተን በ4 ነጥብ እንዲሁም ሼፊልድ ዩናይትድ በ5 ነጥብ ከ18ኛ እስከ 20ኛ ደረጃ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ ። ዛሬ ማታ ፉልሀም ከዎልቨርሀምፕተን ጋ ተስተካካይ 13ኛ ጨዋታውን ያከናውናል ።

የጥቅምት 12 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ቡንደስ ሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ 344ኛ ጨዋታ በመዳኘት ክብረ ወሰን የሰበሩት የ48 ዓመቱ የመሀል ዳኛ ፌሊክስ ብሪች ሽቱትጋርት አይንትራኅት ፍራንክፉርትን በሜዳው 2 ለ1 በረታበት ጨዋታ ጉልበታቸው ተጎድቶ ከሜዳ ወጥተዋል።   ከዚህ ባሻገር የአይንትራኅት ፍራንክፉርት ደጋፊዎች ከጨዋታው በፊት ከሜዳ ውጪ ከፖሊሶች ጋ በመጋጨታቸው ሌሎች ደጋፊዎችም ከስታዲየሙ  ሲወጡ ታይተዋል።

ቅዳሜ በነበሩ ሌሎች ግጥሚያዎች፦ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 4 ለ2፤ ባዬር ሌቨርኩሰን ቬርደር ብሬመንን 3 ለ0 እንዲሁም ቮልፍስቡርግ ላይፕትሲሽን 2 ለ1 አሸንፈዋል ። ፍራይቡርግ ከዳርምሽታድት፤ ዑኒዮን ቤርሊን ከአውግስቡርግ ጋ አንድ እኩል ነጥብ ተጋርተዋል ።  ኮሎኝን የጎበኘው ባዬር ሙይንሽን በሔሪ ኬን ብቸኛ ግብ እንደ። ምንም አሸንፏል ።  ትናንት ሆፈንሀይም ከማይንትስ ጋ አንድ እኩል እንዲሁም ሀይደንሀይም ከቦሁም ጋ ያለምንም ግብ ተለያይቷል ።

ጉልበታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው የ48 ዓመቱ የመሀል ዳኛ ፌሊክስ ብሪች ምስል Arne Dedert/dpa/picture alliance

የደረጃ ሰንጠረዡን ባዬር ሌቨርኩሰን በ34 ነጥብ ይመራል ። ባዬር ሙይንሽን በ32 ይከተላል ። ሽቱትጋርት በ27 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃ ይዟል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ24 እንዲሁም ላይፕትሲሽ በ23 ነጥብ 4ኛ እና 5ና ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። ኮሎኝ በ6 ነጥብ የመጨረሻ ደረጃ 18ኛ ነው ። ዑኒዮን ቤርሊን እና ማይንትስ በ7 እና 8 ነጥብ የመጨረሻዎቹ ተርታ ተሰልፈዋል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW