የኅዳር 26 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ኅዳር 26 2015ስፔን ቫለንሺያ ከተማ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የማራቶን ሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ለድል ሲበቁ በወንዶች ውድድር ኬንያውያን እና የታንዛኒያ ሯጭ ቀንቷቸዋል። የዓለም ዋንጫ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ የተደረጉ ጨዋታዎች በምድብ የዙር ጨዋታዎች እንደነበሩት ብዙም ሳያጓጉ አሸናፊዎቹ ጨዋታዎቹ በተጀመሩ ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ታውቀው ተጠናቀዋል። ከአፍሪቃ ብዙ ተጠብቆ የነበረው የዘንድሮ የአፍሪቃ ዋንጫ ባለድሉ የሴኔጋል ቡድን ይህ ነው የሚባል የማሸነፍ እልህ ሳይታይበት በሰፋ የግብ ልዩነት ከውድድሩ ተሰናብቷል በአንጻሩ የሞሮኮ ቡድን ብርቱ ፉክክር ዐሳይቶ ወደ ቀጣዩ የሩብ ፍጻሜ ውድድር በማለፍ ዘንድሮ ብቸኛው የአፍሪቃ ቡድን መሆን ችሏል። በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት የነበሩትን እና የዛሬ የመጨረሻ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችንም እንቃኛለን።
አትሌቲክስ፥
በቫሌንሺያ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል በተለይ በሴቶች ውድድር አንደኛ፤ ሁለተኛ እና አራተኛ ደረጃ የኢትዮጵያውያቱ ሆኗል። በዚሁ ውድድር፦ የሀገሯን ክብረ ወሰን በመቆጣጠር አትሌት አማኔ በሪሶ የ1ኛ ደረጃን አግኝታለች። አማኔ በውድድሩ የግሏ ምርጥ የተባለውን 2:14:58 አስመዝግባለች። በዓለም የ10,000 ሜትር የሩጫ ፉክክር የወርቅ ሜዳይ አሸናፊዋ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ለተሰንበት ግደይ የመጀመሪያዋ በሆነው በዚሁ የቫለንሺያ የማራቶን ፉክክር 2:16:49 በመሮጥ የ2ኛ ደረጃን በማግኘት ውጤታማነቷን አስመስክራለች። በማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ሌላኛዋ ኬንያዊት ሯጭ ሻይላ ቼፕኪሩይ 2:17:29 ሮጣ የ3ኛ ደረጃን ይዛለች። ታዱ ተሾመ 2:17:36 ሮጣ በመግባት የ4ኛ ደረጃን አግኝታለች።
በቫሌንሽያውን 2022 የማራቶን ሩጫ የወንዶች ፉክክር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ኬንያውያን እና የታንዛኒያ ሯጭ ተቆጣጥረውታል። የትናንቱ ውድድርን ኬልቪን ኪፕቱም 2 ሰአት ከ1 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ በመሮጥ አሸንፏል። የኤሊውድ ኪፕቾጌ ክብረወሰንንም ለመስበር ለጥቂት በ44 ሰከንድ ሳይሳካለት ቀርቷል። የታንዛኒያው ሯጭ የ2ኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ የፈጀበት 2:03:00 ነው። በማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈው ኬኒያዊው አትሌት አሌክሳንደር ሙቲሶ ከ29 ሰከንዶች በኋላ ተከትሎ በመግባት የ3ኛ ደረጃን አግኝቷል። የ4ኛውን ደረጃ ታምራት ቶላ 2:03:40 በመሮጥ ይዟል። ደሱ ጫሉ እና ሚልኬሳ መንገሻ የ6ኛ እና የ7ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። የገቡበትም ሰአት ከታምራት የ1 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ እና የ109 ሰከንዶች ልዩነት አለው።
የዛሬ ወር በሚካሄደው ዐርባኛው የጃንሜዳ ዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ ውድድር የግል ተሳታፊዎችን መመዝገብ መጀመሩን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዐስታወቀ። ታኅሣስ 23 ቀን፣ 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ በሚካኼው ውድድር ተሳታፊ ለመሆን ከሰኞ እስከ ዐርብ በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት በመገኘት መመዝገብ እንደሚቻልም ተገልጧል።
እግር ኳስ
በዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ የደረሱ ሃገራት
በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፋቸውን ያረጋገጡ አራት ሃገራት ኔዘርላንድ፤ አርጀንቲና፤ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ናቸው። በዛሬ እና ነገ አራት ግጥሚያዎች ደግሞ ቀሪዎቹ አራት ቡድኖች ተለይተው ይታወቃሉ። ጃፓን ከክሮሺያ ጋር እየተጋጠሙ ነው። ምሽቱን ብራዚል ከደቡብ ኮሪያ ጋር ይጋጠማሉ። ነገ ደግሞ አፍሪቃዊቷ ሞሮኮ ከስፔን ተጫውታ፤ ምሽት ላይ ፖርቹጋል ከስዊትዘርላንድ ጋር ትጋጠማለች። ወደ ሩብ ፍጻሜ የሚገቡት አራቱ አሸናፊዎችም ይታወቃሉ።
ኔዘርላንድ ወደ ሩብ ፍጻሜ የገባችው በጥሎ ማለፉ ዩናይትድ ስቴትስን 3 ለ1 አሸንፋ ነው። አርጀንቲና በበኩሏ አውስትራሊያን 2 ለ1 ረትታ ነው ለሩብ ፍጻሜው ኔዘርላንድን የፊታችን ዐርብ የምትገጥመው። ቅዳሜ ዕለት ማታ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ይጋጠማሉ። በጥሎ ማለፉ ፈረንሳይ ፖላንድን ትናንት 3 ለ1 አሸንፋ ነው ወደ ሩብ ፍጻሜ የገባችው። እንግሊዝም በበኩሏ ትናንት ማታ ሴኔጋልን በጨዋታ ቴክኒክ በልጣ 3 ለ0 ማሸነፍ በመቻሏ ወደ ሩብ ፍጻሜ አልፋለች። የቡድናቸው ትናንት ተሸንፎ ከውድድሩ መውጣት ቅር ያሰኛቸው የሴኔጋል ቡድን ደጋፊዎች ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፍ ለቻለችው ብቸኛዋ የአፍሪቃ ሀገር ሞሮኮ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ገልጠዋል። አብዱላዬ የሞሮኮ ቡድን ገና ብዙ ይጓዛል የሚል እምነት አለው።
«የአፍሪቃ ቡድን ሞሮኮ ስላለች ሁላችንም እሷን እንደግፋለን። አጨዋወታቸውን፤ ብሎም ያሸነፉትን ለተመለከተ ሞሮኮ የመጀመሪያው ዙር አስደናቂዎች ነበሩ ማለት ይቻላል። እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ወደሚቀጥለው ዙር ያልፋሉ። እኛም ይሄን ቡድን እንደግፋለን።»
ሌላኛዋ የሴኔጋል ቡድን ደጋፊ ቢንቶውም ከእንግዲህ ድጋፏን ለሰሜን አፍሪቃዊቷ ሞሮኮ እንደምታደርግ ተናግራለች።
«አሁን ሞሮኮን እስከ መጨረሻው እንደግፋለን። መላው ሴኔጋል፤ መላው አፍሪቃ ከሞሮኮ ጋር ነው። በውድድሩ የቀረን ብቸኛ ቡድን ሞሮኮ ነው፤ የምንደግፈውም እሱኑ ነው። ለእኛ ዋናው ነገር አፍሪቃ ናት። በዚህም የተነሳ ሞሮኮን እንደግፋለን። እስከ ፍጻሜው ይደርሳሉም ብለን ተስፋ እናደርጋለን።»
የሞሮኮ አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊም፦ «ለሀገራችን እና ለአፍሪቃ እንጫወታለን» ሲሉ የ«አትላስ አናብስት» የተሰኘው ቡድናቸው ከስፔን ጋር ነጋ ሲጋጠም የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። በተለይ አፍሪቃውያን እና የዓረቡ ዓለም ድጋፍ ከሞሮኮ ጋር እንደሚሆንም ገልጠዋል። ሞሮኮ ከ36 ዓመት በኋላ በድጋሚ በዓለም ዋንጫ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ጥሎ ማለፍ ላይ ደርሳለች። ከሦስት ዐሥርተ ዓመት በፊት ያኔ 87ኛው ደቂቃ ላይ የጀርመኑ አማካይና ተከላካይ ሎታር ማቲያስ በቅጣት ምት ባስቆጠራት ግብ የሞሮኮ ግስጋሴ ባይገታ ኖሮ ሌላ ታሪክ በሠራችም ነበር።
በዶይቸ ቬለ የተጠየቁ የሴኔጋል ደጋፊዎች ቡድናቸው በትናንቱ ግጥሚያ ብዙም ብርቱ ትግል አለማድረጉን በመጥቀስ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። የሴኔጋል ቡድን አጠቃላዩ ማለት በሚቻል መልኩ የሚጫወቱት በአውሮጳ ትልልቅ ሊጎች ውስጥ ነው። ምናልባትም በአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታ ጉዳት ገጥሟቸው በአውሮጳ ቡድኖቻቸው ላይ ተጽእኖ እንዳይፈጥርባቸው ሳይሠጉ የቀሩም አይመስሉም አጨዋወታቸው። በተለይ በትናንቱ ጨዋታ ከአቅም በታች ሲንቀሳሱ ላስተዋለ እንደዚያ ማሰቡ አይቀርም።
ለትናንቱ የሴኔጋል ቡድን ሽንፈት ከተጨዋቾቹ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና እጦት ባሻገር አሰልጣኝ አሊዮ ሲሴን ተጠያቂ አድርገዋል ደጋፊዎች። ኢብራሒም ሴኔጋል ከውድድሩ የወጣችው በአሰልጣኝ ስህተት ነው ባይ ነው።
«አሰልጣኙ ናቸው። ማንም እንደዚያ አልጠበቅንም። 11ዱ ተሰላፊዎች እነዚያ ይሆናሉ ብለን አልጠበቅንም። ሌሎች ተጨዋቾችን ነበር የጠበቅነው። ይሄኛው ተጨዋች ማለት አልፈልግም፤ ግን 11 የመጀመሪያ የተሻሉ ተሰላፊዎችን ጠብቀን ነበር። የሚያበሳጭ ነው። እስከ ፍጻሜው እንደርሳለን ብለን ተስፋ ሰንቀን ተሰናበትን፤ ያሳዝናል።»
ቢንቱዎ በበኩሏ ወደ ሜዳ ቅድሚያ የገቡት 11ዱ የሴኔጋል ተጨዋቾች ላይ እንደ ኢብራሒም ጥያቄ አላት።
«ሴኔጋል ጨዋታውን ስትጀምር ወደ ሜዳ የገቡት 11 ተጨዋቾች…ያ የማይሆን ነው። 11ዱ ተሰላፊዎች የጠበቅናቸው አይደሉም። አሰልጣኙ ስህተት ሠርተዋል።»
አሰልጣኝ አሊዮ ሲሴ ኮስታሪካን 2 ለ1 ባሸነፉበት የ4-3-2-1 አሰላለፍ ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ቢገቡም፤ የአማካይ ቦታዎች ላይ ግን የተወሰነ ለውጥ አድርገው ነበር። የግራ ክንፍ ተመላላሹ የኦሎምፒክ ማርሴ አማካዩ ፓፔ ጉዬን በናምፓሊስ ሜንዲ ቀይረዋል። አሰልጣኙ ምናልባትም የላይስተር ሲቲው አማካይን ማሳለፋቸው የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታን በደንብ የሚያውቀው ተጨዋች ይሻለኛል በሚል ሳይሆን አይቀርም። የኤቨርተኑ አማካይ ኢድሪስ ጉዬን ተቀያሪ ወንበር ላይ አስቀምጠውም በእሱ ቦታ በኮስታሪካ ጨዋታ የቀኝ ተመላላሽ የነበረውን የሼፊልድ ዩናይትዱ አማካይ ኢሊማን ንዳዬን አሰልፈዋል። በኢሊማን ንዳዬ የአማካይ ቦታ ደግሞ የሞናኮው አጥቂን ክሬፒን ዲያታን አሰልፈዋል። የሴኔጋልን ደጋፊዎች ያበሳጨው የአሰልጣኝ አሊዮ ሲሴ የተጨዋቾች አሰላለፍ ይህን ይመስል ነበር።
አሰልጣኝ አሊዮ ሲሴ ቡድናቸውን ማድረስ የሚገባቸው ከፍታ ላይ ያደረሱ እና ከዚህ በላይ መዝለቅ የሚችሉ አይመስልም። የዛሬ 20 ዓመት ሴኔጋል ቡድንን በአምበልነት ወደ ሩብ ፍጻሜ ማድረስ ችለው ነበር። በ2018 እና በ2022 ዘንድሮ ቡድናቸውን ለዓለም ዋንጫ ቢያበቁምወደ ሩብ ፍጻሜ ማድረስ ግን አልቻሉም። ላለፉት 7 ዓመታት የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው የቆዩት አሊዮ ሲሴ ቡድናቸውን የዘንድሮ የአፍሪቃ ዋንጫ ባለድልም ማድረግ ችለዋል። ከእንግዲህ ግን ከዚህ በላይ መዝለቅ የሚችሉ አይመስልም። ለዚያም ሊሆን ይችላል ከትናንቱ «ሽንፈታቸው» በኋላ ሁሉን ነገር ሰከን ብለው ሊያጤኑበት እንደሚሹ የተናገሩት።
በአውሮጳ ምድር የሚጫወቱት የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች አብዛኞቹ ዕድሜያቸው 30 እና ከዚያ በላይ ናቸው። የቀሩትም በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ከ30 ዓመት በላይ ይሆናቸዋል። አምበሉ ካሊዱ ኩሊባሊ 31 ዓመቱ ነው፤ የቸልሲው ግብ ጠባቂ ኤድዋርድ ሜንዲ 30 ዓመቱን ደፍኗል። አማካዩ ኢድሪስ ጉዬ 33 ዓመት ሲሆነው፤ በጉዳት ዘንድሮ ለዓለም ዋንጫ ሳይሰለፍ የቀረው፤ በርካቶች ሲጠብቁት የነበረው የባየር ሙይንሽንኑ አጥቂ ሳዲዮ ማኔም 30 ዓመቱ ነው።
ለሴኔጋል ቡድን ለውጥ ሊያመጣ ይችል የነበረው እና የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግን በሚገባ የሚያውቀው ሳዲዮ ማኔ በዓለም ዋንጫ ማግስት መጎዳት ለሴኔጋል ቡድን አንዳች ደንቃራ ነው ማለት ይቻላል። እንዲህ ለእግር ኳስ ሲታይ እድሜያቸውን የገፉ ተጨዋቾች የተሰባሰቡበትን ቡድን ይዘው አሰልጣኝ አሊዮ ሲሴ በሚቀጥለው የዓለም ዋንጫ ቡድናቸውን ማድረስ እጅግ ይከብዳቸዋል። ምናልባትም አሰልጣኙን ካናዳ፤ ሜክሲኮ እና ዩናይትድ ስቴትስ በጋራ በሚያሰናዱት ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ከሌላ ቡድን ጋር እናያቸውም ይሆናል።
66 ሺህ ግድም ታዳሚዎች በተገኙበት የኧል-ቤይት ስታዲየም ውስጥ «ሦስቱ አናብስት» የሚል ስያሜ ያለው የእንግሊዝ ቡድን ትናንት የሴኔጋሎቹን «የቴራንጋ አናብስት»ን ሦስት ለባዶ ድል አድርገዋል። ለእንግሊዝ ሦስቱን ግቦች የሊቨርፑሉ ጆርዳን ሔንደርሰን በ38ኛው፤ ሐሪ ኬን 45ኛው ተገባዶ በባከነው 3ኛ ደቂቃ እንዲሁም ቡካዮ ሣካ በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ 57ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥረዋል።
የእንግሊዙ አጥቂ ራሒም ስተርሊንግ እንግሊዝ ውስጥ የሚገኘው ቤቱ ጦር መሣሪያ ባነገቡ ቤት ሠርሳሪዎች በመሰበሩ በትናንቱ ጨዋታ ሳይሰለፍ ወደ ሀገሩ መጓዙ ተጠቅሷል። ዘራፊዎቹ የብራሒም ስተርሊንግን የወርቅ ጌጦች እና ውድ ሰአቶች መዝረፋቸውም ተዘግቧል። ምናልባት ቅዳሜ ከፈረንሳይ ጋር ለሚኖረው ለቀጣዩ ጨዋታ ወደ ዶሐ ይመለስ ወይ አይመለስ ዐይታወቅም።
ዛሬ ማታ ብራዚል ከደቡብ ኮሪያ ጋር ለምታደርገው ወሳኝ ግጥሚያ ግን ጉዳት ደርሶበት የነበረው ኔይማር እንደሚሰለፍ ታውቋል። የ30 ዓመቱ ብዛሪሊያዊ ኮከብ አጥቂ ዛሬ መሰለፍ ለቡድኑ ወሳኝ ትርጉም ይኖረዋል። ነገ ማታ ፖርቹጋል ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ከከስዊትዘርላንድ ጋር ብርቱ ፍልሚያ ይገጥመዋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ