የኅዳር 7 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ኅዳር 7 2013የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከኒጀር አቻው ጋር ለአፍሪቃ ዋንጫ የማጣሪያ የመልስ ግጥሚያውን በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲያካኺድ ተወስኗል። ቀደም ሲል ጨዋታው ይካኼዳል ተብሎ ቀጠሮ ተይዞ የነበረው በባህር ዳር ከተማ ነበር። ባለፈው ሳምንት ወደ ኒጀር አቅንቶ በ1 ለ0 ሽንፈት የተመለሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከምድቡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ይገኛል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን ዳግም ክብረወሰን አስመዝግቧል። በአውሮጳ የኔሽን ሊግ ግጥሚያ በርካታ ውድድሮች ተከናውነዋል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ዩክሬንን በጨዋታ በልጦ ሲያሸንፍ፤ የእንግሊዝ ቡድን በቤልጂየም ብሔራዊ ቡድን ሽንፈት ገጥሞታል።
ኢትዮጵያ ከኒጀር እግር ኳስ ግጥሚያ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከኒጀር ጋር ያለውን የመልስ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲያካኺድ ተወሰነ። ጨዋታው ይካኼዳል ተብሎ የነበረው በባሕር ዳር ስታዲየም ነበር። ውድድሩን በታቀደለት መሠረት ባህር ዳር ስታዲየም ማከናወን ያልተቻለው የባህር ዳር ስታዲየም በደረሰበት ጥቃት በረራ ማካኼድ ስላልተቻለ ነው ተብሏል።
«የባህር ዳር አየር ማረፊያ በደረሰበት ጥቃት የአውሮፕላን በረራ የተቋረጠ በመሆኑ የጨዋታውን ቦታ ለመቀየር አስገዳጅ» መኾኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፌስቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል። አሁን በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ እና ባሳለፍነው ዓርብ የባህር ዳር አየር ማረፊያ አቅራቢያ የደረሰውን የሮኬት ጥቃት ተከትሎ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) አዲስ አበባ ላይ ጨዋታው እንዲደረግ መወሰኑም ተገልጧል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው እንደሚከተለው አስረድተዋል።
«የተፈጠረው ነገር ጠዋት ላይ ስለተሰማ የመነጋገር ዕድሎች ተፈጠሩ። በዚህም ላይ (የካፍ ፕሬዝደንት አህመድ አህመድ) ለዋና ጸሐፊውም ዐሳውቁ ለሌሎችም ዐሳውቁ በተቻለ መጠን ደግሞ ኒጀሮችን የማግባባት ሥራዎችን መሥራት አለባችሁ ባሉን መሰረት ፕሬዝዳንታችንም (አቶ ኢሳያስ ጂራ) ከኒጀር እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ጋር እንደዚሁ በስልክ ተወያይተዋል። እሳቸውም ችግር የለውም መፍታት እንችላለን እኛ ሁላችንም አፍሪካዊ እስከሆንን ድረስ ያለብንን ችግር እንረዳለን እንፈታዋለን የሚል ነገር ነበራቸው። በመሃከል ግን ግብፅም (ይካሄድ) የማለትም አዝማሚያዎች ነበሩ። መጨረሻ ላይ እኛም ኦፊሻል ደብዳቤ ለካፍ ልከን የአዲስ አበባ ስታዲየም በግዜያዊነት ለዚህ ጨዋታ ብቻ ለዚያውም ገደቦች ተቀምጠውበት ይካሄድ የሚል ነገር ነው የተወሰነው።»
አቶ ባህሩ ጨዋታው አዲስ አበባ ስታዲየም እንዲደረግ የተወሰነበትን ሂደት ባስረዱበት ወቅት ጨዋታው ከኢትዮጵያ ውጪ ሊካሄድ የሚችልባቸው ዕድሎች ተፈጥረው እንደነበር ጠቅሰዋል።
የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ዛሬ ከሰአት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ብሔራዊ ቡድኑ ከኒጀር ጋር ማክሰኞ ላለበት የአፍሪቃ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ በጥሩ መንፈስ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ዋልያዎቹ ኒያሜ ላይ 1-0 ሽንፈት ያጋጠማቸው ሲሆን የምድቡን ግርጌ ይዘው ነገ አዲስ አበባ የሚደረገውን ጨዋታ ይጠብቃሉ። እንዲያም ኾኖ አሰልጣኝ ውበቱ ኒያሜ ላይ ያየቱ ቡድናቸው ጥሩ እንደነበረ ተናግረዋል።
«የሦስተኛው ዙር ጨዋታችንን በኒጀር አንድ ለዜሮ ተሸንፈናል። ከጉዞ ጀምሮ እዛ የነበረን ቆይታ መልካም ነበር። ጨዋታውን አስመልክቶ እንግዲህ ባቀድነው መንገድ ለማከናወን ጥረት አድርገናል። በልጆቹ ሜዳ ላይ ያየሁት ጥረት ከጠበኩት በላይ ነው። ውጤት ይዞ ለመምጣት፤ ውጤት ብቻ ሳያሆን በምንፈልግበት መንገድ በአመንበት እና በተዘጋጀንበት መንገድ ላይ ልንሄድ የምንችለውን ርቀት ለማሳየት በታማኝነት የሚችሉትን ለማድረግ ሞክረዋል። ከምንግዜውም በተሻለ የተሻለ ልበ ሙሉነት እና እንዲሰማን የሚያስችል እንቅስቃሴ አድርገዋል ብዬ ነው ማስበው። ይህንን ዝምብሎ በሞራል ሳይሆን ከጨዋታ በኃላ የቪዲዮ ትንተናቸውን ካየን በኃላ የበለጠ ቁጥሮች የሚያሳዩት ይህንን ስለሆነ።»
የዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ በዋናነት በጨዋታው ዙሪያ ያጠነጠነ እንደነበር መግለጫውን ከስፍራው የተከታተለው ጋዜጠኛ ኦምና ታደለ የላከልን ዘገባ ይጠቋማል።
ነገ በሚደረገው ጨዋታ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም እንዲገቡ አልተፈቀደላቸውም። 20 ጋዜጠኞች ብቻ ጨዋታውን እንዲታደሙም የካፍ የጨዋታ ፀጥታ ቁጥጥር ኮሚቴ አባል መወሰናቸውም ታውቋል። የኢትዮጵያ እና የኒጀር ግጥሚያን ብቻ እንዲያስተናግድ ፍቃድ የተሰጠው የአዲስ አበባ ስታዲየም «በካፍ የታገደ» ነበር።
ባሳለፍነው ሳምንት ዐርብ ማታ ከኒጀር አቻው ጋር በኒያሚ ከተማ ጄኔራል ሴይኒ ኩንትቼ ስታዲየም ውስጥ የተጋጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተሸነፈው ከእረፍት መልስ በተገኘች ፍጹም ቅጣት ምት 1 ለ0 ነበር። ኒጀርን አሸናፊ ያደረገችውን ብቸኛ ግብ በ74ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ዩሱፍ ኦማሩ ነው። በዚህችም ብቸኛ ግብ ከምድቡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረው የኒጀር ቡድን ሦስት ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ በመብለጥ የመጨረሻ 4ኛ ቦታውን ለኢትዮጵያ አስረክቦ ሦስተኛ መኾን ችሏል። ምድቡን አይቮሪኮስት በ6 ነጥብ ትመራለች።
የአውሮጳ ኔሽን ሊግ
በአውሮጳ ኔሽን ሊግ ግጥሚያዎች በሳምንቱ ማሳረጊያ ላይ በርካታ ጨዋታዎች የተከናወኑ ሲኾን፤ የስፔኑ ተከላካይ ሠርጂዮ ራሞስ ኹለት ጊዜ ፍጹም ቅጣት ምት መሳቱ በርካቶችን አስደምሟል። አምበሉ ሠርጂዮ ራሞስ ለኹለት ጊዜያት የተገኙትን ፍጹም ቅጣት ምቶች ለስዊትዘርላንዱ ግብ ጠባቂ ያን ዞመር ነበር ያስታቀፈው።
የ34 ዓመቱ ሠርጂዮ ራሞስ ቅዳሜ ዕለት ለሀገሩ ስፔን ሲሰለፍ ለ177ኛ ጊዜ ነበር። ስዊትዘርላንድ ስፔንን 1 ለ0 እየመራች የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት በግብ ጠባቂው በስተቀን በኩል መትቶ ያን ሶመር ተወርውሮ ኳሷን ግብ ከመኾን አጨናግፏል። ኹለተኛውንም ፍጹም ቅጣት ምት በተመሳሳይ አቅጣጫ መትቶ ይኸው የስዊዘርላንድ ግብ ጠባቂ ተወርውሮ ይዞበታል። ለስፔን ቡድን 23 ጊዜ ግብ ማስቆጠር የቻለው ሠርጂዮ ራሞስ ሁለት ፍጹም ቅጣት ምቶችን በአንድ ጨዋታ ማምከኑ መነጋገሪያ ኾኗል። በዚም መሰረት ስፔን ከስዊትዘርላንድ ጋር አንድ እኩል ተለያይታለች።
ስፔን ዩክሬንን ቅዳሜ ዕለት 3 ለ1 ያሸነፈችው ጀርመንን ነገ ማታ ትገጥማለች። ምድቡን ጀርመን በ9 ነጥብ ትመራለች። ስፔን በ8 ነጥብ ትከተላለች። ዩክሬን በስድስት ነጥብ ሦስተኛ ናት። ስዊዘርላንድ 3 ነጥብ ይዛ በምድቡ ግርጌ ላይ ትገኛለች።
ትናንት ቤልጂየም እንግሊዝን 2 ለ0 አሸንፋለች። ኦስትሪያ ሰሜን አየርላንድን 2 ለ1 እንዲሁም ግሪክ ሞልዶቫን 2 ለ0 ድል አድርገዋል። ዴንማርክ አይስላንድን 2 ለ1፤ ቼክ ሪፐብሊክ እስራኤልን 1 ለ0 አሸንፈዋል። ፖላንድ በጣሊያን የ2 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። ሐንጋሪ እና ሠርቢያ አንድ እኩል ተለያይተዋል። ስሎቫኪያ ኮሶቮን 2 ለ 0 አሸንፋለች። ፖርቹጋል በፈረንሳይ 1 ለ 0 የተሸነፈችው ቅዳሜ ዕለት ነበር። ካለፈው ሳምንት አንስቶ ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ በርካታ ሃገራት ግጥሚያቸውን ያከናወኑ ሲኾን ግጥሚያዎቹ ነገም ይቀጥላሉ።
ፎርሙላ አንድ የሚካ ሽቅድምድም
በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ብሪታኒያዊው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን አዲስ ክብረ ወሰን መስበር ችሏል። ከዚህ ቀደም በጀርመናዊው ሚሻኤል ሹማኸር ተይዞ የቆየውን ለስድስት ጊዜያት የፎርሙላ አንድ የዓለም ክብረወሰን በመስበር ለሰባተኛ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል። ሌዊስ ሐሚልተን በቱርክ ግራንድ ፕሪ ሽቅድምድም በማሸነፍ በፎርሙላ አንድ የዓለም ውድድር ለሰባተኛ ጊዜ ባለድል መኾን ችሏል። ሌዊስ ሐሚልተን በውድድሩ መጀመሪያ ላይ ስድስተኛ የነበረ እና የአየር ኹኔታው ለሽቅድምድሙ ፈተና በኾነበት ውድድር በማሸነፉ እጥፍ ድርብ ደስታ ተሰምቶታል። «ቃላት ያጥረኛል» ብሏል በአጭሩ ከድሉ በኋላ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ደስታውን ሲገልጥ። በየጊዜው በድል ላይ ድል የሚጎናጸፈው ይኸው የመርሴዲስ ድንቅ አሽከርካሪ ገና ሌሎች ድሎች እንደሚጠብቁት እና በማሸነፍ እንደማይረካ ቀደም ሲል ገልጧል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ