1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነሐሴ 16 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 16 2014

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ስድስት ቡድኖች ተጋጣሚዎቻቸው ላይ ሦስት ሦስት ኳሶችን ከመረብ አሳርፈዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ ሦስተኛ ጨዋታውን ላለመሸነፍ ሊቨርፑል በሦስተኛ ግጥሚያው ሦስት ነጥብ ለመያዝ ዛሬ ማታ ይፋለማሉ። በደቡብ አሜሪካ የግማሽ ማራቶን ሁለት ግጥሚያዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለድል በቅተዋል።

Champions League |  Liverpool FC v FC Midtjylland
ምስል Phil Noble/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በሳምንቱ መጨረሻ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ስድስት ቡድኖች ተጋጣሚዎቻቸው ላይ ሦስት ሦስት ኳሶችን ከመረብ አሳርፈዋል። አርሰናል ሦስተኛ ግጥሚያውንም በድል ሲያጠናቅቅ፤ ማንቸስተር ሲቲ ትናንት በትግል ከኒውካስል ጋር አቻ ወጥቷል። ማንቸስተር ዩናይትድ ሦስተኛ ጨዋታውን ላለመሸነፍ ሊቨርፑል በሦስተኛ ግጥሚያው ሦስት ነጥብ ለመያዝ ዛሬ ማታ ይፋለማሉ። በብዙዎች ዘንድ ዛሬ ማታ በልዩ ትኩረት የሚጠበቅ ጨዋታ ነው። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ባየርን ሙይንሽን ትናንት ቦሁምን 7 ለ0 ድባቅ መትቶታል።  ሌሎች የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች በአንጻራዊነት በተቀራረበ የግብ ልዩነት ነው የተጠናቀቁት። በደቡብ አሜሪካ የግማሽ ማራቶን ሁለት ግጥሚያዎች ኢትዮፕያውያን አትሌቶች ለድል በቅተዋል። ሌሎች መረጃዎችንም አካተናል።

ፕሬሚየር ሊግ

ምስል Darren Staples/ZUMAPRESS.com/picture alliance

ዛሬ ማታ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የዘንድሮ ውድድር ወሳኝ ግጥሚያ ይከናወናል። በምሽቱ ግጥሚያ ላለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት የገጠመው ማንቸስተር ዩናይትድ ሊቨርፑልን ያስተናግዳል። ወደ ኦልድ ትራፎርድ ሜዳ አቅንቶ የሚጋጠመው ሊቨርፑል ያለፉት ሁለት ግጥሚያዎቹ ላይ አቻ በመውጣት ነጥብ ጥሏል። ሁለቱ ቡድኖች ላለፉት 12 ጊዜያት ባከናወኗቸው የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ማንቸስተር ዩናይትድ ሊቨርፑልን ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በመጋቢት 2018 ዓም ማንቸስተር ዩናይትድ 2 ለ1 ከማሸነፉ ውጪ ሁለቱ ቡድኖች ለስምንት ጊዜያት አቻ ተለያይተዋል።

ሊቨርፑል በአንጻሩ ላለፉት ዐሥር ዓመታት ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጋቸው ግጥሚያዎች በተከታታይ ለሦስት ጊዜያት አሸንፏል። ለአራተኛው ዛሬ ማማተሩ አይቀርም። በሁለቱ ቡድኖች ታሪክ በፕሬሚየር ሊጉ ከሜዳ ውጪ ባደረጋቸው የመጀመሪያ ግጥሚያዎች ዛሬ ከተሳካለት ሦስኛው ኾኖ ይመዘገብለታል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013-14 የውድድር ዘመን ሊቨርፑል አንፊልድ ሜዳው ላይ ማንቸስተር ዩናይትድን 1 ለ0 ካሸነፈ ወዲህ ሁለቱ ቡድኖች በፕሬሚየር ሊጉ ሦስተኛ ጨዋታ ሲገናኙ የዛሬው የመጀመሪያቸው ነው።  በተጨማሪም ሁለቱ ቡድኖች ያለፉት ሁለት ጨዋታዎቻቸውን ሳያሸንፉ የሚጋጠሙ መሆናቸውም ውድድሩን እጅግ አጓጊ ያደርገዋል።

ምስል Oli Scarff/AFP/Getty Images

አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ በሊቨርፑሉ አሰልጣኝነታቸው ዘመን ዛሬ ማታ የሚፋለሟቸው አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሐግ የማንቸስተር ዩናይትድ አምስተኛው አሰልጣኝ ናቸው። ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ በሊቨርፑል የአሰልጣኝነት ቆይታቸው አምስት የማንቸስተር ዩናይትድ የተለያዩ አሰልጣኞችን ሲገጥሙም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1898 እስከ 1915 በነበረው ዘመን ከነበሩት አሰልጣኝ ቶም ዋትሰን ወዲህ የመጀመሪያው ሰው ናቸው።  በነገራችን ላይ እኚሁ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሐግ ዛሬ ማታ ሽንፈት ከገጠማቸው በማንቸስተር ዩናይትድ የ100 ዓመት ታሪክ የመጀመሪያ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎችን በመሸነፍ ከጆን ቻፕማን ቀጥለው ሁለተኛው ሰው ይሆናሉ። ስኮትላንዳዊው ጆን ቻፕማን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1921 የመጀመሪያ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝነት በመሸነፋቸው በታሪክ ተመዝገዋል።  

ሌላ ሳይጠቀስ የማያልፍ ጉዳይ፦ የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሐመድ ሳላኅ ከቡድኑ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ባደረገው ያለፉት አራት ግጥሚያዎች ስምንት ኳሶችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ከስምንቱ ኳሶች ደግሞ ሔትትሪክን ጨምሮ ስድስቱ ከመረብ ያረፉት ኦልድ ትራፎርድ ሜዳ ውስጥ ነው።

ምስል DW

ከማንቸስተር ዩናይትድ ጉዳት ከደረሰባቸው ተጨዋቾች መካከል በታፋ ጡንቻ መሸማቀቅ የተጎዳው አንቶኒ ማርሺያል ዋነኛው ነው። ምናልባት ዛሬ ማታ ሊሰለፍ ይችል ይሆናል። ቪክቶር ሊንደሎይፍ፤ ብራንዶን ዊሊያምስ እና የቁርጭምጭሚት ጉዳት የገጠመው ፋኩንዶ ፔሊስትሪ ይገኑበታል። በአንጻሩ በርካታ የሊቨርፑል ወሳኝ ተጨዋቾች በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች ዛሬ ማታ አይሰለፉም።  አሌክስ ኦክሳሌድ ቻምበርላይን በታፋ ጡንቻ መሸማቀቅ የተጎዳ ሲሆን መቼ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ዐይታወቅም። ጆይል ማቲፕ፤ ቲያጎ አልካንታራ፤ ኩርቲስ ጆንስ፤ ናቢ ኬታ፤ ኢብራሒም ኮናቴ፤ ካልቪን ራምሴይ እና ባለፈው ጨዋታ ከብስለት ማነስ የተነሳ በቀይ ካር ከሜዳ የተሰናበተው አዲሱ አጥቂ ዳርዊን ኑኔዝ ዛሬ ከማይሰለፉት ውስጥ ይገኙበታል።

ሊቨርፑል በርካታ ወሳኝ ተጨዋቾቹን በጉዳት ቢያጣም፤ የማንቸስተር ዩናይትድ አጥቂ ማርኩስ ራሽፎርድ ባለፈው በብሬንትፎርድ 4 ለ0 የተሸነፈ ቡድኑን ሜዳ ላይ ኅብረት እንዲያሳይ ሲል አስጠንቅቋል። በፕሬሚየር ሊጉ ደካማ ኾኖ የጀመረው ማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ማሸነፉ ለመመለስም ሊቨርፑል ጥሩ አጋጣሚ ነው ሲል ራሽፎርድ አክሏል።

ምስል Mark Pain/empics/picture alliance

በሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች፦ ክሪስታል ፓላስ አስቶን ቪላን 3 ለ1፤ ፉልሀም ብሬንትፎርድን 3 ለ2፤ አርሰናል ቦርመስን 3 ለ0፤ ሊድስ ዩናይትድ ቸልሲን 3 ለ0 አሸንፈዋል። ትናንት በኒውካስል 3 ለ1 ሲመራ የነበረው ማንቸስተር ሲቲም የማታ ማታ ሦስት እኩል በመውጣት ነጥብ ከመጣል ተርፏል።   በተለይ የኒውካስትሉ የግራ ክንፍ አጥቂ ጸጉረጉዱሩ አላን ሶን ማክሲሚ የማንቸስተር ሲቲ አማካዮች እና ተከላካዮችን ሲያስጨንቅ ነበር። ከ25 ዓመቱ ፈረንሳዊ አጥቂ ባሻገር ግቦቹን ያስቆጠሩት አጥቂዎች ካሉም ዊልሰን እና የፓራጓዩ አጥቂ ሚጉዌል አልሚሮ ለሲቲ ፈተና ነበሩ። በትናንቱ ግጥሚያ ድንቅ ብቃታቸውን ያሳዩት ኧርሊንግ ኦላንድ፤ ኢልካይ ጉንዶዋን እና ፖርቹጋላዊው አማካይ ቤርናርዶ ሲልቫ ባስቆጠሯቸው ግቦች ማንቸስተር ሲቲን ከጉድ አውጥተዋል።

ቶትንሀም ዎልቨርሀምፕተንን 1 ለ0፤ ሳውዝሀምፕተን ላይስተር ሲቲን 2 ለ1 እንዲሁም ብራይተን ዌስት ሐም ዩናይትድን 2 ለ0 አሸንፈዋል። ኤቨርተን ከኖቲንግሀም ፎረስት ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል።

ቡንደስሊጋ፦

ምስል Maik Hölter/Team2/IMAGO

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙይንሽን ትናንት ቦሁምን በሜዳው 7 ለ0 ጉድ አድርጎታል። ለባየርን ሙይንሽን በ4ኛው ደቂቃ ሌሮይ ሳኔ የመጀመሪያዋን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ግቦቹ ተከታትለዋል። 25ኛው ደቂቃ ላይ ማቲያስ ዴ ሊግት፤ 33ኛው ላይ ኪንግስሌይ ኮማን ከዚያም ከእረፍት በፊት 43ኛው ደቂቃ ላይ የሊቨርፑል የቀድሞ አጥቂ ሳዲዮ ማኔ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ከእረፍት መልስ 55ኛው ደቂቃ ላይ ሳዲዮ ማኔ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አምስተና ግቡን ከመረብ አሳርፏል። 69ኛው ደቂቃ ላይ የቦሁም ተከላካይ ክሪስቲያን ጋምቦዋ የራሱ ቡድን ላይ አስቆጥሯል። የመጨረሻዋን እና የማሳረጊያዋን 7ኛ ግብ ያስቆጠረው ሰርጌ ግናብሬ ነው።  በእለቱ ኮሎኝ ከፍራንክፉርት ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል።

ቅዳሜ ዕለት በነበሩ ግጥሚያዎች ሆፈንሀይም ባየር ሌቨርኩሰንን 3 ለ0 እንዲሁም ቬርደር ብሬመን ቦሩስያ ዶርትሙንድን 3 ለ2 አሸንፈዋል። አውግስቡርግ በማይንትስ፤ ላይፕትሲሽ በዑኒዮን ቤርሊን የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሟቸዋል። ፍራይቡርግ ሽቱትጋርትን፤ እንዲሁም ሔርታ ቤርሊን ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 1 ለ0 አሸንፈዋል። ቮልፍስቡርግ ከሻልከ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተው ነጥብ ተጋርተዋል።

አትሌቲክስ

ትናንት ደቡብ አሜሪካ ውስጥ በተደረጉ የግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸንፈዋል።  በብራዚል የሪዮ ዴጄኔሮ 24ኛው ዓለም አቀፍ ግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ላይ ኢትዮጵያዊው አትሌት አሰፋ በቀለ አንደኛ በመውጣት ለድል በቅቷል። አሰፋ አንደኛ የወጣው ግማሽ ማራቶኑን በ1 ሰአት ከ3 ደቂቃ ከ47 ሰከንድ በመሮጥ ነው። በዚሁ ውድድር ብራዚላውያን አትሌቶች ጊልማር ሲልቨስትር ሎፔዝ እና ጂዮቫኒ ዶ ሻንቶስ ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመውጣት ተከታትለው ገብተዋል።  

ምስል TONY KARUMBA/AFP

በሪዮ ዴጄኔሮ ግማሽ ማራቶን የሴቶች ፉክክርም ድሉ ለኢትዮጵያውያት ኾኗል። በዚህ ዓመት ኮሪዳ ዴ ራይስ ውድድር ላይ አሸናፊ የኾነችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መስተዋት ጥሩነህ 1 ሰአት ከ13 ሰከንድ በመሮጥ ለድል በቅታለች። የውድድሩን አብዛኛውን ክፍል በጋራ አብራት ስትሮጥ የነበረችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊትአትሌት ፋንቱ ገለሳ በመስተዋት ለጥቂት በ4 ሰከንዶች ተቀድማ የሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። የ3ኛ ደረጃው ለኬኒያዊቷ ጃኔት ማሳይ ኾኗል።

በላቲን አሜሪካ የሩጫ ውድድር ታዋቂ በኾነው የአርጀንቲና ቦነስ አይረስ የግማሽ ማራቶን ፉክክርም ድል ከኢትዮጵያውያን እጅ አልወጣም። በኮቪድ ወረርሽኝ እና በሌሎች ምክንያቶች ላለፉት ሦስት ዓመታት ሳይካኼድ የቆየው ውድድር ዘንድሮ ሲካኼድ ኢትዮጵያዊው አትሌት ገርባ በያታ 1 ሰአት ከ29 ሰከንድ በመሮጥ አሸናፊ ኾኗል። ሁለተኛ ከወጣው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ድንቅ ዓለም አየለ ጋር ያደረጉት ፉክክርም አስደናቂ ነበር። በውድድሩ መጨረሻ ላይ ሁለቱ አትሌቶች አንገት ለአንገት ተያይዘው ባደረጉት ፉክክር የተቀዳደሙት ከአንድ ሰከንድ ባነሰ ጊዜ ብቻ ነው። በሴቶች ተመሳሳይ የሩጫ ፉክክር ድሉ ለኬኒያዊቷ ኢሬኔ ኪማይስ ኾኗል። ኢሬኔ በቦነስ አይረስ የግማሽ ማራቶን ፉክክር ለድል ስትበቃ ያጠናቀቀችው 1 ሰአት ከ7 ደቂቃ ከ59 ሰከንዶች በመሮጥ ነበር።

የሜዳ ቴኒስ

ምስል Jürgen Hasenkopf/IMAGO

በአሜሪካ የኒውዮርክ የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ጀርመናዊው ኮከብ አሌክሳንደር ዜቬሬቭ በቁርጭምጭሚት ጉዳት የተነሳ እንደማይሳተፍ ተገለጠ። ጀርመናዊው አትሌት ጉዳት የደረሰበት በፈረንሳይ የሜዳ ቴኒስ ውድድር ላይ ነበር። ከቁርጭምጭሚት ጉዳቱ በቅጡ ያላገገመው አሌክሳንደር ዜቬሬቭ መስከረም ወር ውስጥ በሚከናወነው የዳቪስ ካፕ ፉክክር ዳግም ወደ ውድድር እንደሚመለስ ዐስታውቋል። የ25 ዓመቱ የዓለማችን ቁጥር ሁለት ዕውቅ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች አሌክሳንደር ዜቬሬቭ ጉዳት የደረሰበት በሮላንድ ጋሮሽ ግማሽ ፍጻሜ ፉክክር ከራፋኤል ናዳል ጋር በሚፎካከርበት ወቅት ነበር።

ፎርሙላ አንድ 

ምስል Johann Groder/AFP/Getty Images

የፎርሙላ አንድ ዋና ኃላፊ በርኒ ኤክሌስቶን በውጭ ሃገራት ያላቸውን ከ473 ሚሊዮን ዶላር በላይ የኾነ ሐብት አላስመዘገቡም በሚል የቀረበባቸውን ክስ ካዱ። የ91 ዓመቱ ባለጸጋ ለንደን ከተማ በሚገኘው የንጉሣዊ ፍርድ ቤት ይግባኛቸውን አቅርበዋል። አቃቤ ሕግ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከሐምሌ 2013 እስከ ጥቅምት 2016 ድረስ የብሪታንያ የግብር ተቆጣጣሪዎች የበርኒ ኤክለስቶን ዓለም አቀፍ ሐብት ላይ የኦዲት ምርመራ ካደረጉ በኋላ ነበር ክሱን ያቀረበው። በርኒ ሳውዝ ፓርክ በሚገኘው የዘውዳዊ ፍርድ ቤት በሚቀጥለው ወር እስኪቀርቡ ድረስ ፍርድ ቤት የዋስትና መብት ሰጥቷቸዋል። በርኒ ኤክሌስቶን በዓለም ዙሪያ ተወዳጅ የኾነው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድምን ከ1970 እስከ 2017 ድረስ ባሉት አራት ዐሥርተ ዓመታት በመምራት ስፖርቱን ተቆጣጥረውት ቆይተዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW