1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነሐሴ 30 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 30 2014

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአልጄሪያው የቻን የአፍሪቃ ዋንጫ ማለፉን አረጋግጧል። ብሔራዊ ቡድናችን በቻን የአፍሪቃ ዋንጫ ሊኖረው የሚችለው የፉክክር ሚዛን ምን ይመስላል? ቃለ መጠይቅ አድርገናል። እጅግ አጓጊ እየሆነ በመጣው የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በአሸናፊነት ሲገሰግስ የነበረው አርሰናል በማንቸስተር ዩናይትድ ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል።

Alexander Isak, Newcastle United
ምስል Sportimage/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአልጄሪያው የቻን የአፍሪቃ ዋንጫ ማለፉን አረጋግጧል። ብሔራዊ ቡድናችን በቻን የአፍሪቃ ዋንጫ ሊኖረው የሚችለው የፉክክር ሚዛን ምን ይመስላል? ቃለ መጠይቅ አድርገናል። እጅግ አጓጊ እየሆነ በመጣው የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በአሸናፊነት ሲገሰግስ የነበረው አርሰናል በማንቸስተር ዩናይትድ ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል። ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ሊጉን በ15 ነጥብ ከሚመራው አርሰናል እና 9 ነጥብ ይዘው 7ኛ እና 8ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ሊቨርፑል እና ብሬንትፎርድ መካከል ልዩነቱ የሁለት ጨዋታዎች ውጤት ሆኗል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ መሪው ባየርን ሙይንሽን ነጥብ ጥሎ መሪነቱን አስረክቧል። ነገ እና ከነገ ወዲያ የሻምፖዮንስ ሊግ ፍልሚያ ይኖራል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የ7 ጊዜያት ባለድሉ ሌዊስ ሐሚልተን በመጀመሪያው ፉክክር መቀደሙ አበሳጭቶታል። በንዴት ለተናገረውም ይቅርታ ጠይቋል።

ምስል BackpagePix/empics/picture alliance

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሳምንቱ መጨረሻ የርዋንዳ አቻውን በማሸነፍ ለቻን የአፍሪቃ ዋንጫ ማለፉን አረጋግጧል። አፍሪቃ ውስጥ ባሉ የሀገር ውስጥ ቡድኖች ብቻ የሚሰለፉ ተጨዋቾችን የሚያሳትፈው ቻን የአፍሪቃ ዋንጫን ዘንድሮ የምታዘጋጀው አልጄሪያ ናት። ቅዳሜ ዕለት በነበረው ግጥሚያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዳዋ ሆቴሳ 22ኛ ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ነው ሩዋንዳን 1 ለ0 ያሸነፈው። ለአልጄርያው የቻን ውድድር ማለፉን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንት ምሽት 2፡30 ላይ አዲስ አበባ ሲገባ አቀባበል ተደርጎለታል።

የእግር ኳስ ተንታኝ እና «ከሜዳ ውጪ» የተሰኘውን ጨምሮ የተለያዩ ለኅትመት የበቁ መጽሐፍትን አዘጋጅ ዘርዓይ እያሱ ብሔራዊ ቡድናችን ያገኘው ድል አስደሳች ቢሆንም ብርቱ ፉክክር እንደሚገጥመው ገልጧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቻን ተሳትፎው ምን ሊመስል ይችላል የሚለውንም ያብራራል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በበርካቶች ዘንድ እጅግ በልዩ ሁኔታ ሲጠበቅ የነበረው የአርሰናል እና የማንቸስተር ዩናይትድ ግጥሚያ በማንቸስተር ዩናይትድ የ3 ለ1 ድል ተጠናቋል። የመድፈኞቹ ግስጋሴም በብርቱ ሽንፈት ተገትቷል። እንዲiaም ሆኖ እስካሁን በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች አርሰናል በ15 ነጥብ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ማንቸስተር ሲቲ በአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ አርሰናልን በዐይነ ቁራኛ እየተከታተለው ነው። ቅዳሜ ዕለት ከአስቶን ቪላ ጋር አንድ እኩል ቢለያይም እንደ አያያዙ ግን ማንቸስተር ሲቲ ዘንድሮም ለሌሎቹ የሚያሰጋ ነው።  ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በነጥብ እኩል ሆኖ በግብ ክፍያ ብቻ የሚበለጠው ቶትንሀም ፉልሀምን 2 ለ1 አሸንፎ በፕሬሚየር ሊጉ የሦስተኛ ደረጃን ተቆናጧል።  ትናንት ላይስተር ሲቲን አርበድብዶ 5 ለ2 ድባቅ የመታው ብራይተን በ13 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 12 ነጥብ ያለው ማንቸስተር ዩናይትድን በመከተል ቸልሲ በ10 ነጥብ ደረጃው ስድስተኛ ነው። ቅዳሜ ዕለት ዌስትሀም ዩናይትድን 2 ለ1 ማሸነፉ ጠቅሞታል። ከኤቨርተን ጋር ያለምንም ግብ የተለያየው ሊቨርፑልንም በአንድ ነጥብ ይበልጠዋል። ብሬንትፎርድም እንደ ሊቨርፑል 9 ነጥብ ይዞ ደረጃው 8ኛ ነው። በአጠቃላይ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ስምንተኛ ደረጃ የነጥብ ልዩነቱ በሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት እና ድል የሚለይ መሆኑ ፕሬሚየር ሊጉን ይበልጥ አጓጊ አድርጎታል። ዌስትሀም ዩናይትድ፤ ኖቲንግሀም ፎረስትእና ላይስተር ሲቲ ወራጅ ቀጠናው ውስጥ ሰፍረዋል

ምስል Martin Rickett/PA Images/IMAGO

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ 5ኛ ዙር ግጥሚያ ባየርን ሙይንሽን የመሪነት ስፍራውን ለፍራይቡርግ አስረክቧል። ቅዳሜ ዕለት ባዬርን ሌቨርኩሰንን 3 ለ2 የረታው ፍራይቡርግ በአምስት ጨዋታዎች 12 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል። ባየርን ሙይንሽን በአንጻሩ ከዑኒዮን ቤርሊን ጋር አንድ እኩል በመለያየቱ በ11 ነጥብ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ተንሸራቷል። ሆፈንሀይምን 1 ለ0 ያሸነፈው ቦሩስያ ዶርትሙንድ እንደፍራይቡርግ 12 ነጥብ ይዞ በቡንደስሊጋው የሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሪያል ማድሪድ ዛሬ ማታ ከአልሜሪያ ጋር የላሊጋው አምስተኛ ጨዋታውን ያደርጋል። ሪiaል ማድሪድ እስካሁን ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች በሙሉ አሸንፎ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አልሜሪያ በሦስት ጨዋታዎች 4 ነጥብ ብቻ ይዞ ታች 12ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል።

ምስል Antonio Calanni/AP/picture alliance

የሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ማክሰኞ እና ረቡዕ ይከናወናሉ። በነገው እለት የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በሲግናል ኤዱና ፓርክ ስታዲየሙ የዴንማርኩ ኮፐንሀገንን ያስተናግዳል። ሌላኛው የጀርመን ቡድን ላይፕትሲሽም ሬድ ቡል አሬና ስታዲየሙ ውስጥ የዩክሬኑ ሻካታር ዶኒዬትስክን ጋብዟል።

ከነገ ወዲያ ምሽት ሦስት የጀርመን ቡድኖች ጨዋታዎች ይኖራሉ። የጀርመኑ ፍራንክፉርት የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዛቦንን ይገጥማል። የጀርመኑ ባየር ሌቨርኩሰን በተመሳሳይ ቀን ረቡዕ ከጥቂት ሰአታት ልዩነት በኋላ ቤልጂየም ውስጥ ክሉብ ብሩይጅን ይገጥማል። ረቡዕ ማታ ባየር ሌቨርኩሰን በሚጫወትበት ሰአት ባየርን ሙይንሽን ጣሊያን ውስጥ ኢንተር ሚላንን ይፋለማል። በአጠቃላይ በነገው ዕለት የማንቸስተር ሲቲ ከሴቪያ፤ ፓሪስ ሳንጃርሞ ከጁቬንቱስ፤ ሪያል ማድሪድ ከሴልቲክ፤ ቸልሲ ከዛግሬብን ጨምሮ ስምንት ጨዋታዎች ይኖራሉ። ረቡዕ ማታም የባርሴሎና ከቼክ ሪፐብሊኩ ቪክቶሪያ ፒልሰን፤ ሊቨርፑል ከናፖሊ እንዲሁም አትሌቲኮ ማድሪድ ከፖርቶ ጋር ያለውን ጨምሮ ስምንት ጨዋታዎች ይኖራሉ።

ምስል Emrah Gurel/AP Photo/picture alliance

አጫጭር የስፖርት መረጃዎች፦

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በ10ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ ተሸላሚ ሆኑ። በኢንተር ሌግዤሪ ሆቴል ትናንት በተከናወነው መርሐግብር ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ለሽልማት የበቁት በአትሌቲክሱ አመራር ላይ ባሳዩት የጎላ አስተዋጽኦ መሆኑ ተገልጧል። በእለቱ በሌሎች ዘርፎችም የተለያዩ ሽልማቶች ተሰጥተዋል።

የጀርመን የሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የቱርክ አቻውን ድል በማድረግ ለዓለም ዋንጫ ተሳታፊነት ቲኬቱን ቆርጧል። የጀርመን ቡድን ቅዳሜ ዕለት በነበረው ግጥሚያ የቱርክ ቡድንን 3 ለ0 ድል በማድረግ ነው ማለፉን ያረጋገጠው።

ምስል Christian Bruna/Pool via AP/picture alliance

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ትናንት ኔዘርላንድ ዛንድፎርት ውስጥ የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን በአንደኛነት አጠናቆ ለድል በቅቷል። የፎርሙላ አንድ የ7 ጊዜያት የዓለም ባለድሉ ሌዊስ ሀሚልተን በዘንድሮ የመጀመሪያ ውድድሩ የማሸነፍ ተስፋው ሲመነምን ከተሽከርካሪው ውስጥ በራዲዮ ጮሆ በመናገሩ ይቅርታ ጠይቋል። ሌዊስ ሐሚልተን በዚህ ፉክክር የ4ኛ ደረጃን አግኝቷል። የመርሴዲስ ቡድን አጋሩ ጆርጅ ሩሴል የ2ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። የ3ኛ ደረጃው የፌራሪ አሽከርካሪው ሻርል ሌክሌር ሆኗል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW